የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ | አፍሪቃ | DW | 08.02.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ

የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ በአይቮሪኮስትና አስተናጋጇ ጋና ተሸናፊነት ተጠናቓል።ካሜሮንና ግብጽ በማለፋቸው ዕሁድ ለፍፃሜው ይፋለማሉ።በጨዋታው ያልተጠበቁ ነገሮችም ተከስተው ነበር።

ግጥሚያው በከፊል

ግጥሚያው በከፊል

በሐሙሱ የፍፃሜ ግጥሚያ፤ግብፅ አይቮሪኮስትን አራት ለአንድ፣ካሜሮን ደግሞ አስተናጋጇ ጋናን ስታዲየም ሙሉ ደጋፊ በተገኘበት ግጥሚያ አንድ ለዜሮ ረትታለች።በውጤቱ ኳስ አፍቃሪው የጋና ሕዝብ የሐዘን ድባብ ላይ እንደወደቀ የዶቸ ቬለ እንግሊዘኛው ክፍል ዘጋቢ ዊሊያም ዴስቦዴስ ከቦታው ዘግቧል።

አሰልጣኝ ክላውድ ለ ረዋ ለሮይተር እንደሰጡት መግለጫ ደግሞ፤የትላንቱን ጨዋታ አስመልክተው ለዝግጅት በጣም አስቸጋሪ ነበር ብለዋል።ቁልፍ ተከላካዬ ጆን ሜንሻ በቀይ ተባሮብኛል፣አሳማኦ ጊያን በጉሮሮ ህመም ምክንያት በስተመጨረሻ ሊሰለፍ እደማይችል ገለፀልኝ።ጨዋታው ከመጀመሩ አስር ደቂቃ በፊት ደግሞ ላሬያ ኪንግስተን ተጎዳብኝ በማለት አማረዋል።

ሆኖም ግን የጋና ጋዜጦችና ራዲዮኖች እንደተቹት ከሆነ አሰልጣኙ ማይክል ኤሴንን በቀይ በተባረረው ጆን ሜንሻ ቦታ ማሰለፍ አልነበረባቸውም።ከዛ ይልቅ ለሮማ ኢታሊ የሚጫወተውን ባሮስ በቦታው ቢተኩ ኤሲያን ወጣ እያለ የመጫወት ዕድል ይኖረው ነበር ብለዋል።በውጤቱ የጋና ደጋፊዎች ቢያዝኑም፤በቀጣዩ የግብፅና አይቮሪኮስት ጨዋታ ግን ከስታዲየም አልጠፉም።

ከካሜሮንና ጋና ቀጥሎ በተወሰኑ የሠዓታት ልዩነት የተደረገው የግብፅና የአይቮሪኮስት ግጥሚያ ደግሞ በግብፅ አራት ለአንድ አሸናፊነት ተጠናቓል።ለግብፅ አህመድ ፋታ በአስራሁለተኛው፣አሚር ዛኪ ደግሞ በተከታታይ በስልሳ ሁለተኛውና ስልሳ ሰባተኛው ደቂቃ፣ሞሐመድ አቡትሪካ ደግሞ በባከነ ሰዓት ግብ ሲያስቆጥሩ፤የማካካሻዋን ግብ ለዝሆኖቹ ያስቆጠረው አብድልቃድር ኬይታ በስልሳ ሶስተኛው ደቂቃ ነበር።

ጨዋታውን ከቦታው ሲከታተል የነበረው የዶቸቬለ ጋዜጠኛ ግን ያልተጠበቀ ውጤት ነው ብሏል።ምክንያቱንም ሲያቀርብ ግብፅ በኩማሲ ስታዲየም ከዛምቢያ ጋር ያደረገችው ትንቅንቅ መጨረሻው ነጥብ መጣል ነበር ብሏል።በአንጻሩ አይቮሪኮስቶች ግን ሁሉንም ግጥሚያ አሸንፈው ነበር።ማሊን አሸንፈዋል፣ናይጀሪያን አሸንፈዋል፣ቤኒንን አሸንፈዋል፣ጊኒንም አሸንፈዋል በማለት ጥንካሬያቸውን ለማስቀመጥ ሞክሯል።

የግብ ጠባቂው ባሪ መጎዳትና የተጠባባቂው ግብ ጠባቂ ሎቡዌ ደካማ ይዞታ ለአይቮሪኮስት ሽንፈት መንስኤ እንደሆነም ተገልጿል።በትላንቱ ጨዋታ የመጀመሪያ ዕርዳታ ሰጪውን ባለቀ ሰዓት የገፈተረውና በቀይ ካርድ የተሰናበተው ካሜሮናዊው ተከላካይ አንድሬ ቢኬይ የካፍ ቅጣት እንደሚጣልበት ይጠበቃል።

በሌላ ጎኑ የግብፁ ግብ ጠባቂ ኤሳም አል ሀዳሪ የተደነቀ ሲሆን፤ በቀጣዩ የካሜሮን ግጥሚያ ወሳኝ ሰው እንደሆነ ተገልጿል።ድሮግባም በበኩሉ የትላንቱን ጨዋታ በተመለከተ ግብፆች ይገባቸዋል፣በጣም አደገኛ በረኛ አላቸው፣መልካም ዕድል እመኝላቸዋለሁ ሲል ገልጿል።እንግዲህ የዋንጫውን ጨዋታ አሸናፊ አብረን የምናየው ይሆናል።

Audios and videos on the topic