የአፍሪቃ እና የአዉሮጳ መሪዎች ጉባኤ | አፍሪቃ | DW | 01.04.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የአፍሪቃ እና የአዉሮጳ መሪዎች ጉባኤ

የአፍሪቃ መሪዎች ስምምነቱን ላለመቀበል የሚያቅማሙበት ብዙ ምክንያት አላቸዉ።ቀድሞ የሚጠቀሰዉ ግን ማርቲን እንደሚሉት አዉሮፖች ለአፍሪቃ ምርቶች ቀረጥ ሳይጠይቁ ገበያቸዉን ክፍት ካደረጉ፤ አፍሪቃዎችም በምላሹ ለአዉሮጳ ሸቀጦች ቀረጥ ሳያስከፍሉ ገበያቸዉን ክፍት እንዲያደርጉ መጠየቃቸዉ ነዉ።

የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት መሪዎች እና የአፍሪቃ ሕብረት አቻዎቸዉ ነገ ብራስልስ-ቤልጅግ ዉስጥ በጋራ ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ።እስከ ሐሙስ የሚቀጥለዉ መሪዎች ጉባኤ በተለይ በአዉሮጳና በአፍሪቃ መካከል ባለዉ የንግድ ልዉዉጥና የምጣኔ ሐብት ትብብር ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይነጋገራል።ለአራተኛ ጊዜ የሚደረገዉ ጉባኤ በሁለቱ ወገኖች መካከል ነፃ የንግድ ቀጠና ለመመሥረት ከዚሕ ቀደም የተደረሰዉን ሥምምነት ገቢራዊ የሚያደርግ ዉሳኔ ይተላለፍበታል ተብሎ ግን አይጠበቅም።በጉባኤዉ አንዳድ የአፍሪቃ ሐገራት አልተጋበዙም፤ ሌሎች የአዉሮጳ ሕብረትን አቋም በመቃወም በጉባኤዉ አይሳተፉም።

የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በተገኙበት እንዲያዙ-የእስር ዋራንት የቆረጠባቸዉ የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦመር ሐሰን አል በሽር ቢጋበዙ እንኳን ካቴናዉን ፈትቶ ከሚጠብቃቸዉ ፖሊስ እጅ-ለመግባት ብራስልስ ይመጣሉ ተብሎ አይታሰብም።የኤርትራዉ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ዛራ ሽቴፋን-«በሀገሪቱ በሚደርሰዉ የሰብአዊ መብት ጥሰት»- ባለቸዉ ሰበብ በጉባኤዉ እንዲካፈሉ ወትሮም አልተጋበዙም።

የዚምባቡዌዉ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ-ተጋብዘዉ ነበር ፤ ግን-ባለቤታቸዉ ቤልጅግ እንዳይገቡ ፍቃድ (ቪዛ) በመከልከላቸዉ ቅር ተሰኝተዉ «ብራስልስ አልመጣም» ብለዋል አሉ።የደቡብ አፍሪቃዉ ፕሬዝዳንት ጄኮብ ዙማ ሥራ ሥለሚበዛብኝ የሚል ይፋዊ ምክንያት ሰጥተዉ ቀርተዋል።ትክክለኛ ምክንያተቸዉ ግን የአዉሮጳ ሕብረት በአፍሪቃ ሕብረት ጣልቃ-እየገባ እገሌ-ይምጣ አበሉ ይቅር ማለቱ አስቆጥቷቸዉ ነዉ-ነዉ የሚባለዉ።

Afrikanische Union

ከተቀሩት-መጪ ቀሪዉን በትክክል ለማወቅ-እስከ ነገ መጠበቅ ይኖርብናል።የሚመጡት ግን ከአዉሮጳ አስተናጋጆቻቸዉ ጋር «የሰዎችን ኑሮ ለማሻሽል፤ ለብልፅግናና ለሠላም መወረት» ባሉት አብይ ርዕሥ ላይ ይነጋገራሉ።ዞሮ-ዞሮ ንግግር ዉይይቱ የምጣኔ ሐብት ሽርክናን ማጠናከር፤ በተለይም ሸቀጦችን ካንዱ ክፍለ-ዓለም ወደ ሌላዉ ካለቀረጥ ማስገባት ወይም ነፃ የንግድ ቀጠና መመሥረት ነዉ- ትኩረቱ።

«በሁለት ሺሕ ዶሐ-በተደረገዉ ሥምምነት ከዓለም እጅግ ደሐ የሚባሉ 40 ሐገራት-ከነዚሕ ሰላሳ ሰወስቱ የአፍሪቃ ናቸዉ፤- ቀረጥ ሳይከፍሉ ምርቶቻቸዉን ለአዉሮጳ ገበያ እንዲያቀርቡ የአዉሮጳ ሕብረት ፈቅዷል።ይሕንን የዓለም ንግድ ድርጅትም ተቀብሎታል።»

ይላሉ ብሮት ፊር ዲ ቬልት የሰኘዉ የጀርመን የርዳታ ድርጅት ባልደረባ ፍራንስሲኮ ማሪ።ይሕን የአዉሮጳ ሕብረትን ሰነድ (EPA-በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) እስካሁን ተቀበለዉ ያፀደቁት አራት ሐገራት ብቻ ናቸዉ።የተቀሩት የአፍሪቃ፤ የካይራቢክ እንና የፓስፊክ አካባቢ ሐገራት ሐሳቡን እስከ መጪዉ ጥቅምት ድረስ እንዲያፀድቁት ሕብረቱ ቀን ቆርጧል።

እስካሁን ግን ድሆቹ ሐገራት ሰነዱን ያፅድቃሉ የሚል ተስፋ ብዙም አይታይም።የሚችጋን-ዩናይትድ ስቴትስ ዩኒቨርሲ የአፍሪቃ ጥናት ተቋም ባልደረባ ፕሮፌስር ጃክ ማንጋል ግን ስምምነቱ አፍሪቃዉያን ማጽደቅ አለባቸዉ ባይ ናቸዉ።

«ይሕን የEPAን ን ጉዳይ የፖለቲካ ድርድራቸዉ ዋና ትኩረት ማድረግ አለባቸዉ።የአፍሪቃ መሪዎች እስከ ጥቅምት ድረስ ስምምነቱን ካላጸደቁ እንደ ፖለቲካ ዉድቀት ማየት አለባቸዉ።»

የአፍሪቃ መሪዎች ስምምነቱን ላለመቀበል የሚያቅማሙበት ብዙ ምክንያት አላቸዉ።ቀድሞ የሚጠቀሰዉ ግን ማርቲን እንደሚሉት አዉሮፖች ለአፍሪቃ ምርቶች ቀረጥ ሳይጠይቁ ገበያቸዉን ክፍት ካደረጉ፤ አፍሪቃዎችም በምላሹ ለአዉሮጳ ሸቀጦች ቀረጥ ሳያስከፍሉ ገበያቸዉን ክፍት እንዲያደርጉ መጠየቃቸዉ ነዉ። «አዉሮጶች ማሺኖቻቸዉን እና መለዋወጫዎቻቸዉን ቀረጥ ሳይከፍሉ አፍሪቃ ዉስጥ መሽጥ ይፈልጋሉ።ምንም እንኳ በይፋ አንሻማም ቢሉም (አላማቸዉ) ሸቀጦቻቸዉን ያለቀረጥ ለአፍሪቃ ገበያ ካቀረቡ፤ ቀረጥ ከሚከፍሉት ከቻይና ወይም ከዩናትድ ስቴትስ ሸቀጦች የበለጠ ገበያ ለማግኘት ነዉ።»

ጉዳዩ በነገዉ ጉባኤ መነሳቱ አይቀርም። ልዩነቱ ግን ይፈታል ተብሎ አይጠበቅም።ምክንያት? ቻተም ሐዉስ የተሰኘዉ የብሪታንያዉ ጥናት ተቋም የአፍሪቃ መምሪያ ሐላፊ አሌክስ ቫኔስ «ምርጫ።» ይላሉ።

ይኽ ጉባኤ ልዩነቱን ሊያስወግድ ቀርቶ ጉባኤዉ ራሱ የተሟላ አይሆንም።ምክንያቱም በቅርቡ የአዉሮጳ ሕብረት ምክር ቤት አባላት ምርጫ አለ።አዲስ ኮሚሽንም ይሰየማል።ሥለዚሕ በአዉሮጳ በኩል ብራስልስ ዉስጥ ሙሉ በሙሉ ለዉጥ ይደረጋል።አፍሪቃዉያንም ይሕን ያዉቃሉ።»

ድርድሩ ቫኔስ እንደሚሉት ይቀጥላል።

ዛራ ሽቴፋን

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic