1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሕንድ ጠቅላይ ሚንስትር የአፍሪቃ ጉብኝት

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 5 2008

የሕንድ ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ ባለፉት አምስት ቀናት አራት የአፍሪቃ ሀገራትን ጎብኝተዋል። በሞዛምቢክ፣ ደቡብ አፍሪቃ፣ ታንዛንያ እና ኬንያ ያደረጉትን ጉብኝት ትናንት ያጠናቀቁት የሕንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ከአፍሪቃ ጋር ያለውን የሀገራቸውን፣ በተለይም፣ ኤኮኖሚያዊ እና ሕዝባዊ ግንኙነቱን ማጠናከር የጉብኝታቸው ዋነኛ ዓላማ አድርገዋል።

https://p.dw.com/p/1JNgH
Mosambik besuch Modi bei Nyusi
ምስል picture-alliance/dpa/AP Photo/S. van Zuydam

[No title]

የዶይቸ ቬለ ባልደረባ ሉድገር ሻዶምስኪ እንደሚለው፣ ጀርመን ከአፍሪቃ ጋር ግንኙነቷን በሁሉም ዘርፎች ማሳደግ የምትችልበት ሰፊ እድል እንዳለ መናገር ብቻ በቀጠለችበት ባሁኑ ጊዜ፣ ሕንድ ራሷን የዚሁ እድል ተጠቃሚ እያደረገች ነው።


ትናንት ባበቃው የሕንድ ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ የአፍሪቃ ጉብኝት ወቅት፣ አፍሪቃ እና ሕንድ፣ ምንም እንኳን በመልክአ ምድራዊ አቀማመጣቸው ቢራራቁም፣ ሁሌም የተቀራረበ ግንኙነት አላቸው የሚለው መልዕክት በጉልህ ተሰምቶዋል። ሕንዳዊው ጠቅላይ ሚንስትር ከስድስት ወራት በፊት በኒው ዴሊ በተካሄደው ዓቢዩ የሕንድ እና የአፍሪቃ ጉባዔ የተቀመጠውን አዲሱን የሁለቱ ቡድኖች የውጭ ስልታዊ ግንኙነት አተረጓጎም በአራት የአፍሪቃ ሀገራት ሰሞኑን ባደረጉት ጉብኝታቸው በተግባር በመተርጎም፣ አዳዲስ አጋሮች ለመፍጠር ከመሞከራቸው ጎን፣ በርካታ የንግድ ትብብር ስምምነቶች ተፈራርመዋል። ሞዲ አለምክንያት አልነበረም ወደ ምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪቃ የተጓዙት፣ በነዚህ አካባቢዎች እጅግ ብዙ የሕንድ ዝርዮች ይኖራሉ፣ በደቡብ አፍሪቃ ብቻ እንኳን ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡ ዝርያቸው ከሕንድ የሆነ ደቡብ አፍሪቃውያን ይገኛሉ። እርግጥ፣ በሞዲ ጉዞ ወቅት በጆሀንስበርግ በተካሄዱ ዓይነት ዝግጅቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ትውልደ ሕንዳውያን ቢገኙም፣ ከአፍሪቃ ጋር ንግድን እና ኢንቬስትመንትን ማሳደግ ቅድሚያ የተሰጠው ጉዳይ ነበር። ሕንዳዊው ጠቅላይ ሚንስትር ግማሽ ቢልዮን ዶላር የሚገመት ኢንቬስትመንት ይዘው ነበር የተጓዙት። በምላሹ ሕንድ በተፈጥሮ ሀብት ከታደለችው አፍሪቃ ጋዝ እና ነዳጅ ዘይት የመግዛት ዓላማ አላት። ይህንኑ ፍላጎትዋን ለማሟላትም ስትል፣ ምንም እንኳን የሱዳን ፕሬዚደንት ኦማር ሀሰን ኤል በሺር በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ ቢተላለፍባቸውም ፣ ከሱዳን ጋር ሳይቀር የጠበቀ የንግድ ግንኙነት ከመፍጠር ወደኋላ አላለችም። ይሁን እንጂ፣ ሕንድ በአፍሪቃ የጥሬ አላባ ንግድ እና ገበያዎች ላይ ሰፊ ተሳትፎ በማግኘቱ ረገድ ከቻይና ጋር ከጀመረችው ፉክክሯ ጎን፣ ከአህጉሩ ጋር ግንኙነቷን ማጠናከር የፈለገችበት ሌላ ፖለቲካዊ ምክንያት አላት።

ሕንድ፣ ልክ እንደ አንዳንድ የአፍሪቃ አካባቢዎች፣ ፈረንሳይ፣ ብሪታንያ፣ ቻይና፣ ሩስያ እና ዩኤስ አሜሪካ ብቻ ቋሚ መንበር የያዙበት የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ተሀድሶ ያስፈልገዋል ባይ ናት። የአቶም ጦር መሳሪያ ባለቤት የሆነችው ሕንድ በፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ውስጥ ቋሚ መንበር ለመያዝ ያላትን ፍላጎት እውን በማድረጉ ረገድ አፍሪቃን ጠቃሚ ሚና የምትጫወት አጋር አድርጋ ትመለከታለች። ደቡብ አፍሪቃም ይህንን የሕንድን ፍላጎት በተደጋጋሚ በመደገፍዋ፣ ምንም እንኳን ብራዚል፣ ሩስያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪቃ ያቋቋሙት በምህፃሩ «ብሪክስ» በመባል የሚታወቀው የኤኮኖሚ ቡድን ብዙም ወደፊት ባይራመድም፣ ከሕንድ ጋር ግንኑነቷ የጠበቀ ነው። ሕንዳውያኑ የባህር ጉዞን ግንኙነት ወይም ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነትን በመታገሉ ረገድ ከአፍሪቃውያን ጋር በቅርብ ተባብረው መስራት ይፈልጋሉ። በኤኮኖሚ ቀውስ የተነሳ የቻይና ታታሪነት በመጠኑ በቀነሰበት ባሁኑ ጊዜ ሕንዳውያኑ በአፍሪቃ ተሳትፏቸውን ለማጠናከር ከጀመሩት ጥረታቸው ፣ ከሁለት ዓመት በፊት አፍሪቃን ግዙፍ የገበያ እድል እንዳላት አህጉር በመመልከት ከአህጉሩ ጋር ይበልጥ የሚያገናኝ አዲስ የአፍሪቃ ፖለቲካ የቀየሰችው ጀርመን አንድ ትምህርት ልትቀስም በተገባ ነበር። ይሁንና፣ ዛሬ ጥቂት መቶ ሺህ አፍሪቃውያን ስደተኞች ወደ ጀርመን ከመጡ በኋላ የጀርመን የአፍሪቃ ፖሊሲ ተቀይሮዋል። ጀርመናውያን የሀገር ውስጥ እና የልማት ትብብር ሚንስትሮችም የኢንቬስትመንት እድሉ ከፍተኛ ወደሆነባቸው ሀገራት ሳይሆን አስተማማኝ ወደሚሏቸው አፍሪቃውያት ሀገራት ተጉዘዋል። ቻይና እና ሕንድ በአፍሪቃ ተሳትፏቸውን ለማሳደግ የሚያደርጉትን ጥረት መተቸት ትርጉም አልባ ነው። በዚህ ፈንታ የሚበጀው አፍሪቃውያን በጀርመን እና በጀርመን ምርቶች ላይ ያላቸውን እምነት፣ ለሁለቱም ወገኖች ጥቅም ላይ ማዋል እና አዳዲስ የስራ ቦታዎችን በመፍጠርም አፍሪቃውያን በሀገራቸው እንዲቆዩ ማድረግ ይሆናል።

Symbolbild UN-Sicherheitsrat
ምስል picture-alliance/dpa/A. Gombert


ሉድገር ሻዶምስኪ
አርያም ተክሌ
አዜብ ታደሰ