የአፍሪቃ -እስያ ጉባኤና ህልም | አፍሪቃ | DW | 24.04.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የአፍሪቃ -እስያ ጉባኤና ህልም

የአፍሪቃና የእስያ መሪዎች በኢንዶኔዥያዋ ጃካርታ ጉባኤያቸው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ስርዓት አዳዲሶቹን ኢኮኖሚዎች በሚጠቅም መንገድ ፍትሃዊነት ይስፈንበት የሚል ጥሪ አቅርበዋል። የሁለቱ ክፍለ ዓለማት ግንኙነት ባለፉት ሁለት አመታት መሻሻል ታይቶበታል ቢባልም በተመጣጣኝ ኢኮኖሚዎች መካከል የተመሰረተ የመሆኑ ጉዳይ ግን አጠራጣሪ ነው።

የ30 አገራት መሪዎች የተሳተፉበት የአፍሪቃ- እስያ ጉባኤ ሚያዝያ 14 ቀን2007 ዓ.ም. የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ የኢንዶኔዥያው ፕሬዝዳንት ጆኮ ዊዶዶ «የዓለም የኢኮኖሚ ችግር የሚፈታው በዓለም ባንክ፤ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋምና የእስያ ልማት ባንክ ነው-የሚለው አሳብ ያረጀና ሊወገድ የሚገባ ነው።» ሲሉ ተናገሩ። የአፍሪቃ እና የእስያ ግንኙነት ስድሳኛ አመት በተዘከረበት ጉባኤ የዊዶዶ ሃሳብ በቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግም ድጋፍ አግኝቷል። ፕሬዚዳንቱ የአፍሪቃና እስያ አገራትን ግንኙነት ለማጠናከር «አዲስ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ያሻል» ሲሉ ተደምጠዋል። የሁለቱ ባለስልጣናት አሳብ በቀጥታ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በዩ.ኤስ. አሜሪካና የአውሮጳ አገራት የተመሰረቱትና ለመስራቾቹ ጥቅም ብቻ የቆሙ የሚባሉትን የገንዘብ ተቋማት በመተቸት ላይ ያተኮሩ ናቸው። የእስያ ልማት ባንክም ቢሆን በጃፓን ተጽዕኖ ስር የወደቀ እየተባለ ይተቻል። ከጉባኤው ተሳታፊዎች መካከል የዚምባብዌው ፕሬዝዳንት የሮበርት ሙጋቤ ንግግርም ከዚህ መንፈስ የራቀ አይደለም። «አፍሪቃና እስያ ችላ የማይባሉ ጠንካራ ሃይሎች ቢሆኑም» አሉ የአፍሪቃው ህብረት ሊቀ-መንበር«የቁጥር ብልጫው በዓለም አቀፍ መድረክ እዚህ ግባ የሚባል ዋጋ የለውም።» አሉ።

ስድሳ አመታት ያስቆጠረው የሁለቱ አህጉራት ግንኙነት በኢኮኖሚው ዘርፍ ፍሬ ማፍራት የጀመረው ካለፉት ሁለት አስርት አመታት ወዲህ ነው። የኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ጌታቸው ተ/ማርያም የሁለቱን አህጉራት ግንኙነት «አፍሪቃ ከምትቀናበት ኤስያ ደግሞ ከተሳካላት የመነጨ ግንኙነት» ሲሉ ይገልጹታል።« እነ ሲንጋፖር፣ደቡብ ኮሪያ፣ቻይናና ታይዋን ያስመዘገቡት እድገት በልማት ሞዴል እጦት ሲባዝኑ ለነበሩት የአፍሪቃ አስተዳዳሪዎች በተወሰ መልኩም አማራጭ የልማት ሞዴል በመሆን እየጠቀመ ይመስላል።» የሚሉት አቶ ጌታቸው የንግድ ሚዛኑ ግን ወደ እስያ ያደላ መሆኑን ያስረግጣሉ።

አፍሪቃ ለእስያ አገሮች የጥሬ እቃ ግብዓት ስታቀርብ ያለቀላቸው ምርቶችን ደግሞ ከተቃራኒው ታስገባለች። ከእስያ አገራት ቻይና ከአፍሪቃ አገራት ጋር ያላት ግንኙነት እንኳ በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር 1955 ዓ.ም. ከነበረበት12 ቢሊዮን ዶላር በ2014 ወደ200 ቢሊዮን ዶላር አድጓል። ህንድ ከአፍሪቃ አገሮች ጋር ያላት የንግድ ልውውጥ በ2014 ዓ.ም. 70 ቢሊዮን ዶላር የኢንዶኔዥያ ደግሞ 11 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። የመዋዕለ ንዋይ ፍሰቱ ግን አንድ አቅጣጫ ብቻ የያዘ ነው። ከእስያ ወደ አፍሪቃ።

የአፍሪቃ አገሮች ከእስያ ጋር ያላቸው የመዋዕለ-ንዋይ እና ኢኮኖሚ ግንኙነት በተጠናከረ ቁጥር ከቅድመ ሁኔታ ጋር ከሚመጣው የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ተቋም ብድርና እርዳታ የተለየ አማራጭ አቅርቧል።አቶ ጌታቸው «አፍሪቃ ለረጅም አመታት ሲያንገላታት ለነበረው የመሰረተ ልማት ገንዘብ እጥረት አሁን በተሻለ ደረጃ አማራጮችን ማግኘት መቻሏ ከእስያ ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖር ረድቷታል።» የሚል እምነት አላቸው። ከዚህ በተጨማሪ በዩ.ኤስ አሜሪካና አውሮጳ ተወስኖ የነበረውን የአፍሪቃ የውጭ ንግድ መዳረሻ በማስፋት ረገድ እስያ የተጫወተችው ሚና ላቅ ያለ እንደሆነ የኢኮኖሚ ተንታኙ አስረድተዋል።

ቻይናና በፍጥነት በማደግ ላይ ናቸው የሚባሉ አገራት የምዕራባውያኑን ጥቅም ለማስጠበቅ የቆሙ ናቸው የሚሏቸውን የገንዘብ ተቋማት የሚቀናቀኑ ባንኮች የመመስረት ሃሳብ ሰንቀዋል። አንደኛው በብራዚል፣ሩሲያ፣ህንድ፣ቻይናና ደቡብ አፍሪቃ ይመሰረታል የተባለው አዲስ የልማት ባንክ(The New Development Bank (NDB) ሲሆን የእስያ የመሰረተ-ልማት መዋዕለ-ንዋይ አክሲዮን ባንክ (Asian Infrastructure Investment Bank) ደግሞ ሁለተኛው ነው። የአውሮጳ አገራት ጭምር ድርሻ በመግዛት የተሳተፉባቸው ሁለቱ ባንኮች ግን ከዓለም ባንክም ይሁን ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የተለየ አደረጃጀትና አሰራር ይዘው አልመጡም። አቶ ጌታቸው በዋናነት የቻይና ድምጽ ጎልቶ የሚሰማባቸው ሁለቱ አዲስ ባንኮች ለአፍሪቃ የሚያመጡት እድል ውስን መሆኑን ይናገራሉ።

«በዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ረገድ የተሻለ ተወዳዳሪነት ይኖራል። የተሻለ ተወዳዳሪነት ኖረ ማለት ደግሞ ቢያንስ ብድር ለማግኘት ለአፍሪቃ የተሻሉ አማራጮች ይፈጠሩላታል ማለት ነው።አፍሪቃ የሚቻል ከሆነ አዲስ ከሚመሰረቱት ባንኮች ድርሻ በመግዛት ካልሆነ ደግሞ እነዚህ ባንኮች በሚያመጧቸው የብድር ስርዓቶች ተጠቃሚ የምትሆንበት እድል መኖሩ አይቀርም።»

የአፍሪቃና እስያ አገራት ከቅኝ አገዛዝ ነጻ በወጡባቸው አመታት ማግስት የተመሰረተውና ስድሳ አመታት የዘለቀው ግንኙነት በመዋዕለ ንዋይ ፍሰትና ኢኮኖሚ ጠንካራ ደረጃ ላይ ደረሰ ቢባልም እኩል ጉልበት፤ተደማጭነትና ፍላጎት ያለው አይመስልም። የእስያ አገራት ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት በዓለም ገበያ ያላቸውን ድርሻ በፍጥነት ባሳደጉባቸው ያለፉት ስድሳ አመታት አፍሪቃውያን ጥሬ እቃ ወደ ውጭ ሲልኩ ከርመዋል። ዛሬም የተለወጠ ነገር የለም።

እሸቴ በቀለ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic