የአፍሪቃ ኤኮኖሚና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ዘገባ | ኤኮኖሚ | DW | 22.11.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአፍሪቃ ኤኮኖሚና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ዘገባ

አፍሪቃ ባለፈው አንድ አሠርተ-ዓመት ያልተቋረጠ የኤኮኖሚ ዕድገት በማድረግ ተሥፋ ሰጭ ዕርምጃ እያደረገች መሆኗ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተደጋጋጊ ሲሰማ የቆየ ጉዳይ ነው። የዓለም ባንክም በቅርቡ በጉዳዩ ባወጣው ዓመታዊ ዘገባ አፍሪቃ ከሰላሣ ዓመታት መጎተት በኋላ ከተቀረው ዓለም ጋር አብራ ለመራመድ እየበቃች መሆኗን አመልክቷል።

የዓለም ባንክ

የዓለም ባንክ

እርግጥ አዝማሚያው የዕድገት መሆኑ ጭብጥና የማይታበል ሃቅ ቢሆንም ዘገባው በብዙ የኤኮኖሚ ጠበብት ዘንድ ቅራኔ-አዘል ሆኖ መታየቱ አልቀረም። ዕድገቱ በዕውነት ከዚህ ደረጃ ደርሷል ለማለት ይቻላል? ማሕበራዊ ለውጥን እያስከተለ ነው ወይ? ቀጣይ የመሆኑስ አስተማማኝነት ምን ያህል ነው? የዓለም ባንክ በቅርቡ ጆሃንስበርግ ላይ ያወጣው ዓመታዊ ዘገባ እንዳመለከተው ከሣሃራ በስተደቡብ የሚገኙት የአፍሪቃ አገሮች የኤኮኖሚ ዕድገት ለሶሥት አሠርተ-ዓመት ሲጎተት ከቆየ በኋላ አሁን ከተቀረው ዓለም ጋር አብሮ መራመድ እየያዘ ነው።

በባንኩ ዘገባ መሠረት የ 70ኛ 80ኛና 90ኛዎቹ ዓመታት ቀውስ ክፍለ-ዓለሚቱ ድህነትን ለመታገል በምታደርገው ትግል በሚረዳ ያልተቋረጠ ዕድገት ተተክቷል። የባንኩ የአፍሪካ ዘርፍ ዋና የኤኮኖሚ ጉዳይ ባለሥልጣን ጆን ፔጅ ያለፉት ዓመታት ዕድገት ከዕድል ይልቅ የጥሩ ፖሊሲ ውጤት ነው ባይ ናቸው። እንደርሳቸው ከሆነ የውጩ ንግድ መስፋፋት፣ የግሉ ዘርፍ የኤኮኖሚ ተሳትፎ መጨመርና የተለያዩ ዓቢይ ቀውሶች መለዘብ በጣሙን ረድቷል።

ጆን ፔጅ አያይዘው እንደጠቆሙት እርግጥ ዕድገቱ ከፍተኛ ሆኖ የሚገኘው ነዳጅ ዘይት አምራች በሆኑ አገሮች ነው። ኤኩዋቶሪያል ጊኒ ለምሳሌ በዚሁ ሃብቷ ከሰላሣ በመቶ የላቀ ዕድገት አሳይታለች። ይህን ሃብት በሚገባ መጠቀም መቻሉ ታዲያ ወደፊት ለአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ወሣኝ ጉዳይ ነው የሚሆነው። በተመሳሳይ ሁኔታ የሌሎች የተፈጥሮ ሃብቶች ዋጋም ከፍ ብሏል። ሆኖም ነዳጅ ዘይት ያላቸው አሥር አገሮች ናቸው። 35 ና 40 የሚሆኑት ግን ይህን ምርት ከውጭ ነው የሚያስገቡት። እና እነዚሁ ዕድገታቸውን ለመጠበቅ ጥሩ የኤኮኖሚ ፖሊሲ ያስፈልጋቸዋል፤ የዓለም ባንክ ዘገባ እንዳመለከተው።

አፍሪቃ ውስጥ ባለፉት ዓመታት ያልተቋረጠ ዕድገት ሲደረግ መቆየቱ አነሰም በዛም በየአገሩ የታየ ሃቅ ነው። አዝማሚያው አበረታች መሆኑም አያጠያይቅም። ሆኖም ዕርምጃው በማሕበራዊ ዕድገት መንጸባረቅ መቻሉ፤ ድህነትንም ለመቀነስ መርዳት-አለመርዳቱ የሁሉም ነገር መመዘኛ እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም። ምን ዓይነት? ወይም ማንን የጠቀመ ዕድገት የሚል ጥያቄ መነሣቱም የማይቀር ነው። የክፍለ-ዓለሚቱን የኤኮኖሚ ዕድገት ባሕርይ በአጭሩ በተጨባጭ መልክ ለማስቀመጥ ያህል፤ የአፍሪቃ የውጭ ንግድ ከ 2004 እስከ 2005, 26 በመቶ ሲጨምር ከዚህም ከግማሽ የሚበልጠው ገቢ የተገኘው ከነዳጅ ዘይት ሽያጭ ነበር።

በዚያው ጊዜ ወደ አፍሪቃ ከተሻገረው ቀጥተኛ የውጭ መዋዕለ-ነዋይ ከግማሽ የሚበልጠውም ወደነዚሁ ጥቂት አገሮች ነበር የገባው። ከሣሃራ በስተደቡብ አፍሪቃ ከጠቅላላው ብሄራዊ ምርት ከ 54 በመቶ የሚበልጠውም የደቡብ አፍሪቃና የናይጄሪያ ነበር። የሁለት ሶሥተኛው የአካባቢው አገሮች የውጭ ንግድ በአንጻሩ 60 በመቶ በሚሆን መጠን በሁለት ምርቶች ላይ ተወስኖ ይገኛል። እንግዲህ የብዙሃኑ አገሮች የኤኮኖሚ ዕድገት የዓለም ባንክ የአፍሪቃ አካባቢ የኤኮኖሚ ባለሥልጣን ሣባ አርባቼ እንደሚሉት ከቀውስ አደጋ ጨርሶ የተላቀቀ አይደለም።