የአፍሪቃ አንድነትና ኤኮኖሚዋ | ኤኮኖሚ | DW | 22.05.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአፍሪቃ አንድነትና ኤኮኖሚዋ

የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት የተቋቋመበት 50ኛ ዓመት በፊታችን ቅዳሜ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኝ መቀመጫው ይከበራል።

አፍሪቃ ዛሬ አሕጉራዊ ድርጅቷን ከመሠረተች ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በኋላ በፖለቲካ ብቻ ሣይሆን በኤኮኖሚ ረገድም ለብዙ ስኬት መብቃቷ በበዓሉ ዋዜማ እየተነገረ ነው። ክፍለ-ዓለሚቱ ለውጭ መዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች ማራኪ እየሆነች መሄዷም በየጊዜው ሲጠቀስ ቆይቷል።                                          

ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ጠበብት ያለፉትን ዓመታት ያልተቋረጠ የኤኮኖሚ ዕድገት መሠረት በማድረግ አፍሪቃ የተፋጠነ ዕድገት ባሣዩት ነብር ተብዬ የእሢያ ሃገራት ጫማ መተካቷን በማመልከት ላይ ናቸው። የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ከዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ተጽዕኖም በፍጥነት ሲላቀቅ በዚህ በያዝነው ዓመት ከሣሃራ በስተደቡብ ካሉት ሃገራት ሩቡ  ሰባት ከመቶና ከዚያም በላይ ዕድገት እንደሚያደርጉ ነው የሚገመተው።              

ከነዚሁ ብዙዎቹም በዓለም ላይ ፈጣን ዕድገት እያሳዩ ነው ከሚባሉት ሃገራት መካከል ይመደባሉ። ይሁን እንጂ ዛሬ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ከተቋቋመ ከ 50 ዓመት በኋላ የክፍለ-ዓለሚቱ አወንታዊ ገጽታ ይህን ብቻ የሚያንጸባርቅ አይደለም። በየጊዜው የሚሰማው የዕድገትና የምጥቀት ወሬ እንደ ዕውነቱ ግማሹ ሃቅ ነው ሊባል ይችላል። ይሁን እንጂ በሌላ በኩል የአፍሪቃ ገጽታ እየተቀየረ መምጣቱ ጎልቶ የሚታይ ነገር ነው።

ዛሬ ሥልጣኔ ካሉት ከሶሥት ሁለት አፍሪቃዊ የሞባይል ስልክ ባለቤት ነው። በክፍለ-ዓለሚቱ የተወሰነው የሕብረተሰብ ክፍል የመግዛት አቅም እየጨመረ መሄዱም አልቀረም። እንዴት ይባል እንደሆን እንጂ በሚሊያርድ የካበቱ ሰዎች ብቅ ብቅ ማለታቸውም ይታያል። ይህ የአፍሪቃ የስኬት ተረት ደግሞ ዛሬ በክፍለ-ዓለሚቱ ፖለቲከኞችና መገናኛ ዘዴዎቻቸው ብቻ ሣይሆን በምዕራቡ ዓለም የኤኮኖሚ ጠበብትና ዓለምአቀፍ የፊናንስ ተቋማት ጭምር ማስተጋባት የያዘ ጉዳይ ነው።                                

ለንደን ላይ እየታተመ የሚወጣው African Business Magazine የተሰኘ መጽሄት ኬንያዊ አዘጋጅ አንቨር ቨርሢም አፍሪቃ በመደረብ ጉዞ ላይ እንደምትገኝ ነው የሚናገረው። ጋዜጠናው የቻይናን ዕርምጃም በንጽጽር  ይመለከታል።

«አፍሪቃ የመጪዎቹ 50 ዓመታት ዋነኛ የዕድገት ገበያ እንደምትሆን ለመናገር በቂ ምክንያት አለ። ይህም አሕጉሪቱ ለዕድገት አስፈላጊ የሆነው የጥሬ ሃብትና ሰፊ የሥራ ጉልበት ባለቤት መሆኗ ነው። በቀላሉ አፍሪቃ በወቅቱ የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶችን የምትማርክ አካባቢ ናት ለማለት ይቻላል። በነገራችን ላይ ቻይና ከአሥርና ከአሥራ አምሥት ዓመታት በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ነበረች። እና አሁን የጀርመንና በአጠቃላይም የአውሮፓ ኩባንያዎች ከተኙበት መንቃትና ይህን ለይተው ማወቅ ይኖርባቸዋል»

በዓለም ባንክ ግምት መሠረት ከሣሃራ በስተደቡብ የሚገኘው የአፍሪቃ ክፍል በፊታችን ሶሥት ዓመታት ውስጥ በአማካይ 5 ከመቶ ዕድገት የሚታይበት ይሆናል። የዓለም ኤኮኖሚ በተመሳሳይ ጊዜ ከያዝነው የጎርጎሮሳውያኑ 2013 እስከ 2015 በሶሥት ከመቶ ገደማ እንደሚያድግ ነው የሚጠበቀው። የአፍሪቃው ዕድገት አሃዝ እንግዲህ በአውሮፓ ወይም በምዕራቡ ዓለም ሊታሰብ ቀርቶ የሚታለምም አይደለም።                                

እርግጥ በአፍሪቃ ከፍተኛ የኤኮኖሚ  ዕድገት አሃዝ መመዝገቡ በድፍኑ የፌስታ መንስዔ ሊሆን አይገባውም። በሰሜናዊው ጀርመን በሃምቡርግ የአፍሪቃ ጥናት ኢንስቲቲዩት ተመራማሪ ሮበርት ካፐል የ 42 ከሣሃራ በስተደቡብ አፍሪቃ ሃገራትን የወደፊት ልማት ሁኔታ ሲመረምሩ እነዚሁ በዓለምአቀፍ ንጽጽር ደካማ ሆነው መገኘታቸውን ነው የሚያስረዱት።

«ዕድገቱ የተመሠረተው ከሁሉም በላይ ባለፉት ዓመታት በጨመረው የጥሬ ሃብትና የእርሻ ምርቶች ተፈላጊነት፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞም በዋጋው መናር ላይ ነው። ማለት የውጭ ንግዱ ለአፍሪቃ ዕድገት ታላቅ ድርሻ ነበረው። ይህ ደግሞ በተመሳሳይ ጊዜ የድክመት ምልክትም ነው»

አፍሪቃ ከውጭው ዓለም በሚደረግ ንግድ ላይ ጥገኛ ናት። ጥገኝነቱ ጎታች መሆኑን ደግሞ የዓለም ባንክና ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም ጭምር በየጊዜው የሚናገሩት ነው። የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናንም በቅርቡ ኬፕታውን ላይ ተካሄዶ በነበረው የዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ጉባዔ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸገው ዓለም ከአፍሪቃ ጋር በሚያካሂደው የጥሬ ሃብት ንግድ ጥብቅ ደምቦችን እንዲከተል ማሳሰባቸው አይዘነጋም።

አናን ሙስናና የግብር ገንዘብ መሸሽ የአፍሪቃን የብልጽግና ዕድል ክፉና እያዳከመ መሆኑን አስገንዝበዋል። በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም የኢንዱስትሪው ዕድገትም ጨርሶ የለም ካልተባለ እንኳ እጅጉን ተጎታች ነው። የእርሻው ዘርፍ የራሱን ሕዝብ ፍላጎት ለመሸፈን እንኳ በሚችልበት ሁኔታ አይገኝም። የስራ ገበያው ሁኔታም የዚያኑ ያህል ደካማ ነው። ሌላው ቀርቶ ራመድ ባለችው በደቡብ አፍሪቃ እንኳ ዛሬ 25 በመቶው ሕዝብ ስራ የለውም። የስራ አጥነቱ ሰለቦች ደግሞ በተለይም በገጠር አካባቢዎች የሚገኙት ወጣቶች ናቸው።

ዕድገቱ ጉልህ ሆኖ የሚታየው ምናልባትም የኤኮኖሚ ማዕከላት በሆኑት እንበል ሉዋንዳን፣ ጆሃንስበርግን ወይም ናይሮቢን በመሳሰሉት ታላላቅ ከተሞች ነው። በነዚህ ከተሞች የግንቢያው፣ የቴሌሎሙኒኬሽኑ፣ የንግዱና የባንኩ ዘርፎች እያበቡ ሲሆን የአፍሪቃ መካከለኛ ሕብረተሰብ መደብም በነዚሁ ስፍራዎች እያደገ በመሄድ ላይ ይገኛል። እነዚህ ደግሞ ለምሳሌ ኤኮኔት-ዋየርለስ በመባል ለሚታወቀው ኩባንያና ሌሎች የአገልግሎት ሰጪዎች ደምበኞች ናቸው።

የአፍሪቃዊው ቴሌኮሙኒኬሽን  ኩባንያ መሥራች የዚምባብዌው ተወላጅ ስትራይቭ ማሢዪዋ ሲሆን ዛሬ በ 17 የአፍሪቃ ሃገራት፣ በአውሮፓ፣ በደቡብ አሜሪካና በእሢያ ለመነገድ የበቃ የአገሩ ቀደምት ባለጸጋ ነው። ታዲያ እርሱም ቢሆን የአፍሪቃን የዕድገት ውዳሴ በተመለከተ ቆጠብ ማለቱን ነው የሚመርጠው።

«አፍሪቃ እርግጥ በጥሩ ሁኔታ ላይ ናት!በተለይ ባለፉት ሁለት አሠርተ-ዓመታት ታላቅ ዕርምጃ አድርገናል። ነገር ግን በዚሁ ሂደት መቀጠልና ማደግ ፍላጎታችን ከሆነ ለወጣቱ ትውልድ የሥራ ቦታዎች እንዲከፈቱ፣ የሕብረተሰቡ ጸጋ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲከፋፈል፣ ቢሮክራሲ እንዲቀንስና ግልጽነት እንዲሰፍን ማድረጋችን ግድ ነው»

ይህ በዕውነትም ዛሬ በአብዛኞቹ የአፍሪቃ ሃገራት ገና ስር ያልሰደደ አጣዳፊ ጉዳይ ሆኖ ይገኛል። የሃምቡርጉ የአፍሪቃ ጥናት ኢንስቲቲዩት ተመራማሪ ሮበርት ካፐል እንደሚያስረዱት የተጠቀሱት ነጥቦች ገቢር የሆኑት የአፍሪቃ ዕድገት አርአያ ሆነው በሚመደቡት ጥቂት ሃገራት እንበል ሞሪሺየስን፣ ሤይሼልስንና ካፕ ቬርዴን ወይም ቦትሱዋናን በመሳሰሉት ሃገራት ነው። ጋናና ደቡብ አፍሪቃም ከነዚሁ መካከል ይመደባሉ።

«ጥራ ሃብት ሁልጊዜ ጥሩው የኤኮኖሚ ዕድገት ምንጭ አይደለም። አብዛኞቹ መልካም ዕድገት ያሣዩ ሃገራት ነዳጅ ዘይት ወይም ሌላ ትልቅ የተፈጥሮ ሃብት ክምችት የላቸውም። በመሆኑም አተኩረው የሚገኙት በአገልግሎት ሰጭና በእርሻ ልማት ዘርፎች ላይ ነው»

ታዲያ በአፍሪቃ ዕድገቱ  ጽኑ መሠረት ያለው ሆኖ ወደፊት እንዲራመድ ምን ለውጥ ያስፈልጋል? የለንደኑ የአፍሪቃ ኤኮኖሚ መጽሄት አዘጋጅ አንቨር ቨርሢ እንደሚለው አፍሪቃ በመዋቅራዊ ግንባታ ላይ የበለጠ መዋዕለ-ነዋይ ማድረጓ ግድ ነው። እንደርሱ ከሆነ የንግድ ተግባር ማካሄድ በዓለም ላይ እንደ አፍሪቃ ውድ የሆነበት ቦታ የለም።

«ችግሩ ለምሳሌ  ኬንያ ወይም ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የሚገኙ የምርት ማዕከላት ፍላጎታቸው በነርሱ ላይ ጥገኛ ከሆነው ውስጣዊ አካባቢዎች በቀላሉ መገናኘት አይችሉም። መንደጎቹና ሃዲዶቹ በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኙ አይደሉም። እናም ምርቱን ማመላለሱ በጣሙን ውድ ነው»         

እንግዲህ የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ዕድገት ዕድሜ እንዲኖረውና በተለይም ብልጽግናው በብዙሃኑ የኑሮ ሁኔታ መሻሻል እንዲከሰት በፖለቲካ፣ በኤኮኖሚና በማሕበራዊ ተሃድሶ ረገድ መደረግ የሚኖርበት ብዙ ነው። መሟላት የሚኖርባቸው ቅድመ-ግዴታዎች ጥቂቶች አይደሉም።

«ተጨማሪ ወይም ቀጣይ የኤኮኖሚ ለውጦችና የገበዮች መከፈት በጣሙን ያስፈልጋሉ። የውስጥና የውጭ ኩባንያዎች መዋዕለ-ነዋይ እንዲያደርጉ ለዚሁ የተሻለ ሕግ መስፈኑም ግድ ነው። ከዚህ በመያያዝ የትምሕርቱ ስርዓትና መዋቅራዊው ይዞታ ከተሻሻለ አፍሪቃ በዕድገቷ ልትቀጥልና የተሥፋ ክፍለ-ዓለም ልትሆን ትችላለች»

የተዘረዘረው ቢሟል አዘውትሮ ሲነገርለት የቆየው የአፍሪቃ የዕድገት ታሪክ ከመልካም ተረትነት ያለፈ ሊሆን የሚችል ነው። እርግጥ የአፍሪቃ ሕብረት ቀዳሚ አካሉ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት የተቋቋመበትን 50ኛ ዓመት በሚያከብርበት ወቅት ክፍለ-ዓለሚቱ ከቆርቋሪዎቿ የአንድነትና የልማት ህልም ብዙ ርቃ ነው የምትገኘው። አፍሪቃ አደገች ተመነደገች ይባል እንጂ ብዙሃን ሕዝቧ ዛሬ በከፋ ድህነት መኖሩን እንደቀጠለ ነው።

በብዙዎች የአፍሪቃ ሃገራት በነጻነት ማግሥት ከዛሬው የተሻለ የኑሮ ሁኔታ እንደነበር ይታወቃል። አፍሪቃ ዛሬ በዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስና ቻይናን በመሳሰሉት በተፋጠነ ዕድገት የሚራመዱ ሃገራት የጥሬ ሃብት ፍላጎት ማየል የተነሣ በድህነት ፈንታ ሃብታም፣ አዳጊ መባል ይዛለች። የአብዛኛው ሕዝቧ የኑሮ መከራ ግን ቀድሞ ድሃ፤ ተመጽዋች ትባል እንደነበበት ጊዜ ባለበት እንደቀጠለ ነው። ስለዚህም ዕድገቱ ሁሉ ፍሬ እንዲሰጥ የኤኮኖሚ ለውጥ ብቻ ሣይሆን የፖለቲካ ለውጥም መስፈኑ አማራጭ የሌለው ነገር ነው።                                                             

በጎ አስተዳደር በሌለበት፣ የዜጎች መሠረታዊ መብቶች ተረግጠውና ታፍነው በተያዙበት፣ ሙስና በተንሰራፋበት ሕብረተሰብ ለብዙሃኑ የሚበጅ አንዳች ዕርምጃ ሊደረግ አይችልም። ባለፉት ሁለት አሠርተ ዓመታት ተደረገ የተባለው የኤኮኖሚ ዕርምጃ እነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች መፍትሄ አግኝተው ቢሆን ነሮ ዛሬ በዕውነት የአፍሪቃን ብልጽግና ሃቀኛ ገጽታ ቢቀር ዳር ዳሩን እንኳ ማየት በጀመርን ነበር። ግን ይህ አልሆነም።

የአፍሪቃው መንግሥታት ድርጅት በአውሮፓው ሕብረት አርአያ የክፍለ-ዓለሚቱን ትስስር ለማጠናከር ራሱን ሕብረት ብሎ ከሰየመ አንድ አሠርተ-ዓመት አልፎታል። ነገር ግን ለኤኮኖሚ ዕድገት አስፈላጊ የሆኑት የአሕጉሪቱ የአካባቢ ገበዮች ከኤኮዋስ እስከ ሣዴክ ከድርጅትነት አልፈው ነጻ የገበያ ይዞታን አስፍነዋል ለማለት አይቻልም። ሃቁ በአፍሪቃ በጎረቤት ሃገራት መካከል እንኳ ግልጽ የንግድና የታክስ ደምብ ባለመኖሩ፤ እንዲሁም የትራንስፖርት ችግርም ከባድ በመሆኑ የምርት እንቅስቃሴው ከባድ መሆኑ ነው።               

አንድ የአፍሪቃ አገር አንዳንዴ ከጎረቤት አገር ከመነገድ ይልቅ ባሕር ማዶ ተሻግሮ ከአውሮፓውያን ጋር መነገድ የሚቀለው ጊዜ አለ። እንግዲህ የሚቀጥሉት 50 ዓመታት የአፍሪቃ ጉዞ ያለፈውን ግማሽ ምዕተ-ዓመት መሰል እንዳይሆን ብዙ መሠራት ይኖርበታል። የአፍሪቃ ሕብረት ባልሥልጣናት ከጥሩ ጉርብትና በፊት አሕጉራዊ አንድነት፤ ከመሠረታዊ ብሄራዊ የምጣኔ ሐብት ይዞታ ስነ ምግባር አስፍኖት በፊት አሕጉራዊ የፊናንስ ውሕደት ወዘተ- ከሚል ጋሪውን ከፈረሱ ካስቀደመ ከንቱ የፖለቲካ ውይይት ወደ ተጨባጩ አጀንጋ ተመልሰው መሠረታዊ የቤት ስራቸውን በቅድሚያ ማከናወን ይጠበቅባቸዋል።                                                                                                               

አፍሪቃን በቀደምትነት ሊያለማ የሚችለው የራሷ ሕዝብ ነው። ይህ ሕዝብ ደግሞ ሰብዓዊ መብቱ ተረጋግጦ ለልማት እንዲነሳሳ ካልተደረገ የውጭ መዋዕለ-ነዋይ ቢንጋጋ እምብዛም ፍሬ አይኖረውም። የአፍሪቃ መሪዎች በፊታችን ቅዳሜ ይህን መሪ መፈክራቸው ለማድረግ ከልብ ቢነሱ ምንና በበጀ!

መሥፍን መኮንን

Audios and videos on the topic