የአፍሪቃ አባት- የመጨረሻዉ ንጉሰ ነገሥት | ባህል | DW | 05.06.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የአፍሪቃ አባት- የመጨረሻዉ ንጉሰ ነገሥት

« አፄ- ኃይለሥላሴ የኔ ዘመድ ብቻ ሳይሆኑ፤ የኢትዮጵያዉያን አባት ናቸዉ። የራሱን ዘመድ ለማሞገስ ብቻ ነዉ እንዳይባል እንኳ፤ የጃንሆይን ድላቸዉን ብቻ ሳይሆን ደካምነታቸዉንም፤ ስህተታቸዉንም ለማስነበብ ሞክሪያለሁ» ይላሉ ዶ/ር ልጅ አስፋዉ ወሰን አስራተ ። ጀርመናዉያን ጃንሆይን አሁንም ቢሆን በጥሩ መንፈስ ነዉ የሚያስቡአቸዉ።

ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት አብቅቶና ጀርመን ሪፐብሊክ ተመስርቶ ከዓለም መንግሥታት ጀርመንን የጎበኙ የመጀመርያዉ በመሆናቸዉም ጃንሆይ ጀርመንን ከሌላዉ ዓለም ያዋኃዱ ፈርቀዳጅ እድርገዉ የሚቆጥሩዋቸዉም ጥቂቶች አይደሉም።

Autorenlesung- Prinz Asfa-Wossen Asserate

ዶ/ር ልጅ አስፋዉ ወሰን በቦን ከተማ በተዘጋጀላቸዉ የስነ-ፅሁፍ ፊስቲቫል ላይ


«ሥነ-ጽሑፍ በከተማዋ በሚገኙ ቤቶች» በተሰኘ ባለፈዉ ሰሞን በዚህ ራድዮ ጣብያችን በሚገኝበት በቦን ከተማ፤ ልጅ አስፋዉ ወሰን በተዘጋጀላቸዉ ደማቅ የስነ-ፅሁፍ ፊስቲቫል ላይ «የአፍሪቃ የመጨረሻዉ ንጉሰ ነገሥት» በሚል በጀርመንኛ ቋንቋ ለአንባብያን ያቀረቡትን የአፄ ኃይለስላሴን ታሪክ በአካል ተገኝተዉ በመተረክ እና የክብር ፊርማቸዉን በማኖር ታዳሚዉን ማስደመማቸዉን ባለፈዉ ባቀረብነዉ ዝግጅት ማዉሳታችን ይታወቃል። ዛሬም ካለፈዉ ዉይይታችን በመቀጠል መጽሐፋቸዉን በተመለከተ ላቀረብንላቸዉ ጥያቄዎች የሰጡንን መልስ ይዘን፤ በፊስቲቫሉ ላይ ከተገኙች እድምተኞች መካከል፤ የአንዳንዶቹ አስተያየት አካተን ይዘን ቀርበናል፤
አፄ ኃይለስላሴ ከስልጣን ከወረዱ ከአርባ ዓመት በኃላ ዶ/ር ልጅ አስፋዉ ወሰን አስራተ፤ በጀርመንኛ ቋንቋ «የአፍሪቃ የመጨረሻዉ ንጉሰ ነገሥት» በሚል ለአንባብያን ያቀረቡት መጽሐፋቸዉ ሰሞኑን በመፅሐፍ ሽያጭ መዘርዝር ከፍተኛዉን ቦታ መያዙ ተነግሮለታል። አፄ ኃይለስላሴ የመንፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ከተካሄደባቸዉ በኃላ፤ ለሀገር ለመሥራት የነበራቸዉ ኃሞት መፍሰሱ ተተርኮል። በርግጥ ይህ የሆነበት በመፈንቅለ መንግሥቱ ምክንያት ይሆን? ልጅ አስፋወሰን አስራተ፤ አይደለም ባይ ናቸዉ፤
ሌሎች የአፍሪቃ ሀገራት በአንጻሩ ጃንሆይን የአፍሪቃ አባት አድርገዉ ነዉ የሚያዩዋቸዉ፤ እንደዉም አንድ የናይጀርያ ጋዜጠኛ ንጉሱ ከስልጣን እንደወረዱ ባስቀመጠዉ ጽሑፉ « ከአሁኑ ትዉልድ ይልቅ ታሪክ በራሱ ግዜዉን ጠብቆ ይመሰክርላቸዋል» ሲል አስቀምጦ ነበር፤ በዚህ ላይ ልጅ አስፋወስን አስራተ አስተያየትም ልክ ነዉ። በቅርቡ የአፄ ኃይለስላሴን ታሪክ የሚያስነብበዉ መጽሐፋቸዉንም ህንኑ ሐሳብ በመዘርዘር መደምደማቸዉን ነግረዉናል።
« መጽሐፊ የመዝግያ ምዕራፍም ይህንኑ ሃሳብ ይዞ ነዉ የሚያበቃዉ። ከኛ በኃላ የሚመጣዉ ትዉልድ አፄ ኃይለስላሴን ምናልባት በሌላ ዓይን ያያቸዋል።እንድያም ሆኖ እዚህ ላይ ማወቅ ያለብን የአፄ ኃይለስላሴ የዉጭ ፖሊሲ እንከን የሌለዉ ነዉ። የአፍሪቃ አባት ናቸዉ፤ ሌላዉ ይቅርና በኮሚኒስት ሀገር ፤ እንደ ሞስኮብ እና ቻይና የመሰሉት መንግስታት፤

Buchcover - Prinz Asfa-Wossen Asserate

«የአፍሪቃ የመጨረሻዉ ንጉሰ ነገሥት» የተሰኘዉ በጀርመንኛ ቋንቋ የወጣዉ መጽሐፍ

የመጀመርያዉ ፀረ-ፋሺስት ንጉስ ሲሉ ነበር የሚጠርዋቸዉ እንጂ ያ ፊዉዳሉ ንጉስ አልነበረም የሚሉዋቸዉ። በዉጭ የነበራቸዉ ፍቅርና ክብር ሀገራቸዉ ዉስጥ አላዩትም። ከመንግሥቱ ንዋይ መፈንቅለ መንግሥት በኃላ፤ አስራ አራት ዓመት፤ ንጉሰ ነገሥቱ ጥረታቸዉን በብዛት ያሳዩት የዉጭ ፖሊስያቸዉ ላይ ነዉ»
«የአፍሪቃ የመጨረሻዉ ንጉሰ ነገሥት» በሚል ዳጎስ ያለ ወደ 420 ገፆችን የያዘ መጽሐፍ ነዉ ለአንባብያን ያቀረቡት እንደዉም በአፍ መፍቻ ቋንቋ ሳይሆን፤ ጥራቱን በጠበቀ ጀርመንኛ ቋንቋ ነዉ፤ ይህ ብዙ ግዜ ሳይጠይቅዎት አልቀረም፤ እንዴት ተሳካሎት? ለሚለዉ ጥያቄ፤
« እንዲህ አይነቱን መጽሐፍ ለአንባብያን ለማቅረብ ከዛሬ ነገ የሚሳካ ጉዳይ አይደለም፤ የጃንሆይን የሕይወት ታሪክ ለመፃፍ ካሰብኩ በጣም ብዙ ግዜዬ ነዉ።ነገር ግን አሁን ዞር ብዬ ሳየዉ እንኳን አብዮቱ ከፈነዳ ከሶስት ከአራት ዓመት በኃላ አልፃፍኩት፤ እንኳን አሁን ፃፍኩት ብዬ እደሰታለሁ። ምክንያቱም ንጉሰ ነገሥቱ ከስልጣን ከወረዱ ዛሬ አርባ ዓመት ሆኖታል። በዚህ አርባ ዓመት ብዙ የቀሰምኳቸዉ ነገሮች ስላሉ፤ ይህን ታሪክ ከዚህ ቀደም ጽፊዉ ቢሆን ኖሮ በሌላ አመለካከት ሊቀርብ ይችል ነበር ብዬ አስባለሁ። በደረሰብኝም ከፍተኛ ሐዘን ምክንያት የኢትዮጵያን ሁኔታ በሌላ ዓይን ምናልባት ብዙ ነገሮችን ያላገናዘበ አርጌ ላቀርበዉ እችል ይሆን ነበር ብዬ አምናለሁ። ስለዚህ ግዜ ወስጄ በጀርመን፤ በፈረንሳይ፤ በእንግሊዝ፤ በዩኤስ አሜሪካ እና ኢጣልያ ዉስጥ ከሚገኙ የመረጃ መዛግብት ዉስጥ ያገኝኃቸዉን መረጃዎች በማካተት ይህን መጽሐፍ ለማቅረብ በመቻሌ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ»
ቦን ከተማ ደማቅ የስነ-ጽሑፍ ፊስቲቫልን በማዘጋጀት ዶክተር ልጅ አስፋወሰን አስራተን በከፍተኛ መድረክ ላይ የጋበዝዋቸዉ ፍሪድሬከ ሽትሪተር፤ ከፊስቲቫሉ በኃላ በሰጡት አስተያየት ፤
« ልጅ አስፋወሰን አስራተ ስለመጽሐፋቸዉ ያደረጉልን ትረካ እጅግ እጅግ አስደናቂ ነበር። በታሪኩም በጣም ተገርሜያለሁ። ስለኢትዮጵያና ስለ -ንጉሰ ነገሥቱ ታሪክ ከመፃሃፋቸዉ ቆንጥረዉ ያነበቡልን ክፍል አስገራሚ እና ሕይወት ያለዉ ነበር። ታሪኩን በምናባችን ማስቀመጥና አብረን እንድንጓዝ በቅርበት እንድናየዉ አድርገዉናል» ግን ደግሞ አሉ ፍሪድሪከ በመቀጠል በጣም ያስገረመኝ እና ልቤ የተነካዉ አሉ፤ «በጣም ያስገረመኝ እና ልቤ የተነካዉ፤ በዝያን ግዜ ጀርመን ሀገር ትምህርታቸዉን በመከታተል ላይ የነበሩት ዶክተር ልጅ አስፋወሰን፤ ንጉሱ ከስልጣን ከወረዱ በኃላ እና ቤተሰቦቻቸዉን ካጡ በኃላ፤ እጅግ አዝነዉ እንደነበር፤ በሌላ በኩል በኃይማኖታቸዉ እና በእምነታቸዉ ፀንተዉ፤ አስከፊዉን ግዜ ማሳለፋቸዉን በተናገሩ ግዜ እጅግ ልቤ ተነክቶአል። ምክንያቱም እኔም ኃይማኖተኛ በመሆኔ ነዉ»

Bildergalerie Iran Historischer König Schah Mohammed Reza

የአፄ ኃይለስላሴ የዉጭ ፖሊሲ እንከን የሌለዉ ነበር

ልጅ አስፋወሰን አስራተ «የአፍሪቃ የመጨረሻዉ ንጉሰ ነገሥት» የሚለዉን መጽሐፋቸዉን ባስተዋወቁበት መድረክ ላይ የተገኙት፤ በቦን ከተማ በሚገኘዉ የቴሌኮምንኬሽን አገልግሎት ሰራተኛ ሽቴፈን ድርጋን በበኩላቸዉ
« ልጅ አስፋወሰን በጀርመን የሚታወቁ በመሆናቸዉ አዲስ አልሆኑብኝም፤ በተልይ ስለ ስነ-ምግባር ለጀርመናዉያን ባቀረቡት መሐሃፋቸዉ ዝናን አግኝተዋል። እንድያም ሆኖ ዛሬ ልጅ አስፋወሰን ይዘዉት ከቀረቡበት መጽሐፋቸዉ ጋር እጅግ አስገርመዉኛል። ስለ ኢትዮጵያ እስካሁን የማላዉቀዉን አስደናቂ ታሪክ ነዉ የተረኩልን። ከሁሉም በላይ የትረካ አንደበታቸዉ እጅግ ማራኪና ፤ አሁንም አሁንም አዳምጥ የሚል ስሜትን ነበር ያስያዘኝ፤ በጣም ማራኪ ነበር።» ከዶልክተር ልጅ አስፋወሰን አስራተ ጋር ዉይይቴን በመቀጠል ፤ አፄ ሃይለስላሴን ምን ያህል ያቋቸዋል ብዬ ጠይቄያቸዉ ነበር፤
« ከልጅነቴ ጀምሪ አዉቃቸዋለሁ። ያዉ በዝምድናችን ፤ አጎቴም በመሆናቸዉ፤ በቤተሰብነት ቅርበት ነበረኝ፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ዉስጥ የፖለቲካ ሥራ አልነበረኝም። እንደሚታወቀዉ በሃያ ዓመቴ ነዉ ከኢትዮጵያ የወጣሁት። እኔ እስከማዉቃቸዉ ድረስ ግን ጃንሆይ፤ ከፍተኛ ግርማ ሞገስ የነበራቸዉ፤ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ፍቅር የነበራቸዉ፤ ንጉሰ ነገሥት እንደነበሩ በብዙ ነገር አይቻለሁኝ»

Asfa-Wossen Asserate auf der Frankfurter Buchmesse

ዶ/ር ልጅ አስፋዉ ወሰን አስራተ


የሁለተኛ ደረጃ ማጠቃለያ ፈተናን በአዲስ አበባ በሚገኘዉ የጀርመን ትምህርት ቤት ያጠናቀቁትና በጎርጎረሳዉያኑ 1968 ዓ,ም ለከፍተኛ ትምህርት፤ ወደ ጀርመን የመጡት ዶክተር ልጅ አስፋወሰን አስራተ፤ በቱቢንገን ከተማ ከሚገኝ ዩንቨርስቲ በህግ እና በኤኮኖሚ ትምርት ተመርቀዋል። በመቀጠል ለሁለት ዓመት በኬምብርጅ ዩንቨርስቲ ትምህርታቸዉን ቀጥለዉ፤ በጎርጎረሳዉያኑ 1978 ዓ,ም በፍራንክፈርት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ጥናት የዶክተርነት ማዕረግን ተቀብለዋል። ዶ/ር ልጅ አስፋዉ ወሰን አስራተ፤ ከኛ ጋር ስላደረጉት ረዘም ያለ ቆይታ እያመሰገንኩ «የአፍሪቃ የመጨረሻዉ ንጉሰ ነገሥት» በሚል ስለ አፂ ኃይለስላሴ በጀርመንኛ ቋንቋ ያቀረቡትን መፅሐፍ ፤ ለኢትዮጽያዉያን በአማርኛ ቋንቋ አንባብያን እንድያደርሱ በመጠየቅ የለቱን ዝግጅቴን አጠናቅቃለሁ ። ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫዉን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሃመድ

Audios and videos on the topic