የአፍሪቃ አበይት ጉዳዮች በ2016 | አፍሪቃ | DW | 24.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የአፍሪቃ አበይት ጉዳዮች በ2016

ለየአገሮቻቸው መንበረ-ሥልጣን ከእኔ በላይ ላሳር ባዮቹ የአፍሪቃ መሪዎች ዛሬም ከተቃዋሚዎቻቸው እና ተቺዎቻቸው ጋር እሰጥ አገባ ላይ ናቸው። በውዝግቡ እስር እና ሞት እዚህም እዚያም ይሰማል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:49
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:49 ደቂቃ

የ2016 የአፍሪቃ አበይት ጉዳዮች

የአብዮተኛው የቶማስ ሳንካራ አገር ቡርኪና ፋሶ የጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም. በጠባ በአስራ አምስተኛው ቀን በእገታ እና ግድያ ነበር የተቀበለችው። ድንበር አልባዋ ቡርኪና ፋሶ በዋና ከተማዋ ዋጋዱጉ ወደ ሆቴል እና ቡና ቤቶች ሰርገው የገቡ ታጣቂዎች 29 ሰዎች ገደሉ። አብዛኞቹ የውጭ አገራት ዜጎች ነበሩ። ከፍተኛ የወርቅ ክምችት በከርሰ ምድሯ የያዘችው ዓለም ግን በድሕነት ለይቶ በሚያውቃት ቡርኪና ፋሶ ለተፈጸመው ጥቃት ኃላፊነቱን የወሰደው በመግሪብ አካባቢ የሚገኘው የአልቃዒዳ ክንፍ ነበር። ከጥቃቱ የተረፉት አስደንጋጩ ዕለት በትውስታ ማኅደራቸው ተቀርፆ ይቀራል። «በመጀመሪያ ከባድ እና የነፍስ ወከፍ ጦር መሳሪያዎችን ተኮሱ። ከዚያ የክፍላችንን መዝጊያ ገንጥለው ገቡ። ሁለት ነበሩ። አንደኛው በእኔ ላይ በተኮሰው ጥይት ትከሻዬ ላይ ተመትቻለሁ።»

Symbolbild Terrorist Terrorismus Terror (AP Graphics)

ከሁለት ወራት በኋላ ከአይቮሪ ኮስቷ አቢጃን ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው ግራንድ ባሳም ሆቴል ላይ ተመሳሳይ ጥቃት በተመሳሳይ ጽንፈኛ ታጣቂዎች ተደገመ። አስራ ስምንት ሰዎች ተገደሉ ። የጸጥታ ተንታኞች ጊዜ እየቆጠረ ጥቃት የሚፈፅመው የመግሪብ ክንፍ ራሱን «እስላማዊ መንግስት» ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጋር ፍክክር ውስጥ ገብቷል ሲሉ ይናገራሉ። 
እዚያው ምዕራብ አፍሪቃ የናይጄሪያ እናቶች ልጆቻችንን መልሱ ሲሉ የጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም. ሊጠናቀቅ ነው። ናይጄሪያውያኑ ከትምህርት ቤታቸው ታፍነው የተወሰዱት ልጃገረዶች እንዲለቀቁ የሚጠይቁ ተከታታይ ዘመቻዎች ቢያደርጉም ምኞታቸው አልሰመረም። ተስፋ መቁረጥ ከተጫናቸው እናቶች መካከል የታገተችው ሳራያ ስቶቨር እናት ትገኝበታለች። የልጇን ፎቶ ግራፍ ከደረቷ ለጥፋ ስለ ልጇ የምታሰላስለው ሞኒካ ስቶቨር የናይጄሪያ መንግስት አቅመ ቢስነት እጅጉን ካስቆጣቸው መካከል ናት። 
« ገና ስለ እገታው ስሰማ ነበር ተስፋ የቆረጥኩት። ልጄን እንደገና በሕይወት አያታለሁ ብዬ ለማሰብ አልችልም። »
ባለፈው ግንቦት ወር በቦኮ ሐራም ከሁለት አመት በፊት ከታገቱ የቾቦክ ልጃገረዶች መካከል አንዷ መለቀቋ  ለእነዚህ እናቶች ደግም ክፉም ዜና ነበር። 
«ከታገቱት የቺቦክ ልጃገረዶች መካከል አንዷ መለቀቋ ፍፁም ደስታ ይፈጥራል። 218ቱ አሁንም እንደታገቱ መሆናቸው በአንፃሩ ጽኑ ህመም አለው። ምንም ተደርጎ ቢሆን ልጆቻችንን ልንመልሳቸው ይገባል።»እኚህ እናት እንደተመኙት ሁሉም ልጃገረዶች ወደ ቤታቸው ባይመለሱም ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ እና የስዊዝ መንግሥት ጣልቃ ገብተው በተደረገ ድርድር 21ዱ በጥቅምት ወር ተለቀዋል። በጎርጎሮሳዊው 2016 የመጀመሪያ ወር ቦኮ ሐራም ዶሪ የተባለችውን የናይጄሪያ መንደር በመውረር ቢያንስ 65 ሰዎችን ገድሎ ነበር። የመንደሪቷ ነዋሪዎች ግን የሟቾች ቁጥር ከ100 ይልቃል ሲሉ ተደምጠዋል። 

ድንበር ተሻግሮ ምዕራብ አፍሪቃን ከሚያምሰው የቦኮ ሐራም ታጣቂ ጋር ግብግብ የገጠመችው ቻድ ፕሬዝዳንት ዓመቱ የተገባደደው ከተቃውሞ እና የስራ ማቆም አድማ ጋር ሲተናነቁ ነው። ለአምስተኛ የሥልጣን ዘመን በዚሁ ዓመት ቃለ-መኃላ የፈጸሙት ፕሬዝዳንት ኤድሪስ ዴቢ ተቀዋሚዎቻቸውን እየለቀሙ ዘብጥያ ቢወረውሩም ተቀባይነታቸውን ከማሽቆልቆል ሊታደጉት ተስኗቸዋል። ከ25 ዓመታት በላይ በሥልጣን የቆዩትን ዴቢን ተቃውመው በፕሬዝዳንትነት የተወዳደሩት ሳሌህ ኬብዛቦ በበዓለ ሲመቱ ዋዜማ አሁንም እንቃወማቸዋለን ብለው ነበር። 
« የዴቢ ድል ሕጋዊ እና ትክክለኛ አልነበረም። እውነቱ እስኪያሸንፍ ድረስ ስልጣናቸውን መቃወማችንን እንቀጥላለን። የሕዝብን ደህንነት በሚያስቀድም መንግሥት እንታገላቸዋለን። እርግጥ፣ ዴቢ የጦር ኃይሉን፣ ፊናንሱን እና መንግሥቱን ይቆጣጠራሉ። ያም ቢሆን ግን እንቃወማቸዋለን። ጊዜው ሲያመችም ይህን መንግሥት እናቋቁማለን። »


በአምባገነንነት የሚወቀሱት የ64 ዓመቱ ኤድሪስ ዴቢ የቻድን ሥልጣን የተረከቡት ከሒሴኔ ሐብሬ ነበር። ሒብሬ በአፍሪቃ ፍርድ ቤት ተዳኝተው በሰብዓዊነት ላይ በፈጸሙት ወንጀል ጥፋተኛ የተባሉ ብቸኛው አፍሪቃዊ መሪ ናቸው። የቀድሞው አምባገነን መሪ በሥልጣን ላይ በነበሩባቸው ዓመታት በተፈጸሙ ወንጀሎት የተከሰሱ ሲሆን ሴኔጋላዊው ዳኛ ግቤርታኦ ካም እድሜ ይፍታሕ ፈርደውባቸዋል።«ሒሴኔ ሐብሬ ችሎቱ የዘፈቀደ ግድያ፤ ግርፋት እና ሰዎችን በማጥፋት ወንጀሎች ጥፋተኛ ሆነው አግኝቶዎታል።» 
ለፍርድ ቤቱ እውቅና የነፈጉት ሒብሬ ሁለት ጊዜ በፖሊስ እየተጎተቱ ከችሎት ለመቅረብ ተገደዋል። የቀረበባቸውን ክሥ የሚቃወሙት ጠበቆቻቸውም ቢሆኑ ሒብሬ የቀረበባቸውን የግድያ እና አስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ሊቀበሉ አይሹም። ሒብሬ ከዚህ ችሎት የቀረቡት በህይወት የተረፉ ሰለበዎቻቸው ለዓመታት ካደረጉት ጥረት በኋላ ነው። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሒብሬ ጥቃት የደረሰባቸው 93 ግለሰቦች በፍርድ ቤቱ ቃለ-መሐላ ፈጽመው መስክረውባቸዋል። ሒብሬ የቀረበባቸውን ክስ ለመከላከል ባይሞክሩም የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ግን የዓመታት በደላቸውን በልባቸው ሸክፈው ለኖሩ ሰለባዎች እፎይታ ነበር።  

በቡሩንዲ የተቀሰቀሰውን ኹከት ለማብረድ የአፍሪቃ ኅብረት ሰላማዊ ዜጎችን ለመጠበቅ 5,000 ሰላም አስከባሪዎችን ለመላክ ያቀረበውን እቅድ ፕሬዝዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ ያጣጣሉት ገና በዓመቱ የመጀመሪያ ወር ነበር። ንኩሩንዚዛ የተቀሰቀሰባቸውን ተቃውሞ በኅይል እየደፈጠጡ፤ገረቤቶቻቸውን እየወነጀሉ ይኸው ሥልጣን ላይ ናቸው። የቡሩንዲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አላን ኤሜ ኒያሚትዌ  «ሉዓላዊነታችንን እና ክብራችንን ተጋፍታለች» ያሏትን ጎረቤት አገራቸውን ርዋንዳን በፍርድ ለመሞገት ዝግጁ ነን ብለው ነበር። 
 «ርዋንዳ እንደ ሃገር የህዝባችንን ሉዓላዊነት እና ክብር መጋፋቷን የሚጠቁም ማስረጃ አለን። በማንኛውም ሰዓት በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ክስ ልንመሰርት እንችላለን።ምክንያቱም ሁለቱም አገሮች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል በመሆናቸው በሰላም አብሮ ለመኖር በሚያስገድዱ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ለመገዛት ተስማምተዋል። አባል አገራት ከቅኝ-ገዢዎቻቸው የተላለፉ ድንበሮችን እንዲያከብሩ የሚያስገድዱ ሰነዶች እና ድንጋጌዎች በጸጥታው ምክር ቤት እና በጠቅላላ ጉባዔው ዘንድ ይገኛሉ። የሌሎች አገራት ድንበሮችን የሚጥሱ አገሮች ፍርድ ቤት ቀርበው ሊዳኙ ይገባል።»


ፕሬዝዳንት ፓል ካጋሜ ሐሰት ይበሉ እንጂ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለፈው ግንቦት ወር ባወጣው ዘገባ ርዋንዳ የቡሩንዲን ተቃዋሚዎች ትደግፋለች ብሎ ነበር። ፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛ ለሶስተኛ የሥልጣን ዘመን ዳግም ለመወዳደር መወሰናቸውን ካስታወቁበት ጊዜ ጀምሮ በተቀሰቀሰ ኹከት 400 ሰዎች መገደላቸውን እና ከ260,000 በላይ መሰደዳቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጧል። የቡሩንዲ ቀውስ አሁንም መፍትሔ ባያገኝም ንኩሩንዚዛ ከቀጣናው አገራት እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ አይደሉም። የትንሺቷን አገር ፖለቲካ የሚከታተሉ ተንታኞች ግን ቡሩንዲ ወደ ማያባራው አዘቅት እየተንደረደች ነው ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። 
በአንድ ወቅት በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን ፖለቲካ ቁልፍ ሚና የነበራቸው ሪየክ ማቻር አጋሮቻቸው እና ወዳጆቻቸው ሁሉ ፊታቸውን ያዞሩባቸው በዚሁ ሊገባደድ ቀናት በቀሩት የጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም. ነው። አንዴ ወዳጅ ሌላ ጊዜ ተቀናቃቸው ከሚሆኑት የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ጋር የአንድነት መንግሥት ለመመሥረት ሥምምነት ፈርመው በሚያዝያ ወር የአገሪቱን ሁለተኛ ከፍተኛ ሥልጣን ዳግም የተረከቡት ማቻር ወቅት እየጠበቁ ውግንናቸውን የሚቀያይሩ ተንኮለኛ ፖለቲከኛ ናቸው ይሏቸዋል-ወቃሾቻቸው። ለሁለት አመታት በርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የዘለቀችው ደቡብ ሱዳን እንደገና ወደ ርስ በርስ ጦርነት እየተንደረደረች ነው የሚል ማስጠንቀቂያ ከዓለም አቀፍ ተቋማት በተደጋጋሚ ቢደመጥም ማቻር እና ኪር ተቃርኗቸውን መፍታት ተስኗቸው ቆይቷል። በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግፊት በደቡብ ሱዳናውያን ልመና የሰላም ሥምምነት ተፈርሞ ማቻር ወደ ደቡብ ሱዳን ሊመሰሉ ሲዘጋጁ ባላንጣቸው በመናገሻ ከተማቸው ስለ ዕርቅ ሰብከው ነበር።

የሰላም ሥምምነቱ አልሰመረም። የአንድነት መንግሥቱ ፈርሷል። ዕርቅም አልወረደም። ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ምክንያት ደርድረው ምክትላቸውን ወንጅለው ማቻርን ሻሯቸው። በአዲስ አበባ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጄምስ ፒትያ ሞርጋን እንደሚሉት ለማቻር ጀርባውን የሰጠው የገዛ ፓርቲያቸው ነው።
 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በደቡብ ሱዳን ላይ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ለመጣል ሳይሳካለት ቀርቷል። አገሪቱ በገፍ የምትሸምተው የጦር መሳሪያ ያሳሰባቸው የኃይማኖት አባቶች ትችት ተቀባይነት አላገኘም። የአካባቢው አገራት በሳልቫ ኪር ላይ ፊታቸውን አዙረዋል። ደቡብ ሱዳናውያን ግን በገፍ ወደ ጎረቤት አገራት ይሰደዳሉ። የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ባወጣው መረጃ ባለፈው ወር 2,480 ደቡብ ሱዳናውያን በየቀኑ ወደ ዩጋንዳ ተሻግረዋል። በሚቀጥለው ዓመት ስለመመለሳቸው የሚታወቅ ነገር የለም።  

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic