የአፍሪቃ አምባሳደሮች የትራምፕን ይቅርታ ይሻሉ | ዓለም | DW | 13.01.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የአፍሪቃ አምባሳደሮች የትራምፕን ይቅርታ ይሻሉ

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአፍሪካ ሀገራትን ለመግለጽ የተጠቀሙበት ጸያፍ ቋንቋ አሁንም ማነጋገሩን ቀጥሏል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ አምባሳደሮች ቡድን ንግግሩን የሚያወግዝ መግለጫ ዛሬ አውጥቷል፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ አምባሳደሮች ትላንት ምሽቱን ካካሄዱት አስቸኳይ ስብሰባ በኋላ ባወጡት መግለጫ ንግግሩን “አስደንጋጭ፣ ዘረኛ እና መጤ ጠል አስተያየት ያለበት” ሲሉ አውግዘውታል፡፡ ከዚህም ሌላ ፕሬዝዳንቱ ለንግግራቸው ማረሚያ እንዲያወጡ አሊያም ይቅርታ እንዲጠይቁ አሳስበዋል፡፡ የጋናው ፕሬዝዳንት ንግግሩን “ተቀባይነት የሌለው” ሲሉት ከእርሳቸው በፊት ሀገሪቱን ይመሩ የነበሩት ደግሞ “ዘረኛ” ብለውታል፡፡

ትራምፕ ጸያፉን ንግግር ተናገሩ የተባለው ከአሜሪካ የምክር ቤት አባላት ጋር ስለ ኢምግሬሽን እቅድ በመምከር ላይ እያሉ ነበር፡፡ ፕሬዝዳንቱ ለኑሮ ምቹ ያልሆነ እና ቆሻሻ ቦታን ለመግለጽ የሚውለውን ጸያፍ ቃል የተጠቀሙት ሀገራቸው መጀመሪያውኑ ለምን ከሃይቲ እና ከአፍሪካ ሀገራት የሚመጡ ስደተኞችን እንደምትቀበል ጥያቄ ባነሱበት ወቅት ነው፡፡ በትራምፕ ንግግር የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ቁጣቸውን ትናንት ዓርብ ገልጸዋል።  

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ጽህፈት ቤትም የትራምፕን አገላለጽ “ዘረኛ” እና “መጤ ጠል ጥላቻን የሚቀሰቅስ ነው” ሲል ትናንት ክፉኛ መተቸቱ ይታወሳል፡፡ የጽህፈት ቤቱ ቃል አቀባይ ሩፐርት ኮልቫይል ከዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት የተሰሙት አስተያየቶች “አሳፋሪ እና አስደናጋጭ ናቸው” ብለዋል፡፡ የፕሬዝዳንቱን አስተያየት ለመግለጽ “አንድ ሰው ሌላ ቃል ሊጠቀም አይችልም ዘረኛ እንጂ” ሲሉ ትናንት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ ትራምፕ ጸያፉን ንግግር አልተናገርኩም ሲሉ ቢያስተባብሉም ከየአቅጣጫው የሚሰነዝርባቸው ትችት ቀጥሏል፡፡ 

ተስፋለም ወልደየስ

ልደት አበበ

ተዛማጅ ዘገባዎች