የአፍሪቃ አሜሪካ ጉባኤ | ዓለም | DW | 04.08.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የአፍሪቃ አሜሪካ ጉባኤ

ዛሬ የተጀመረው የዩናይትድ ስቴትስና የአፍሪቃ ጉባኤ ዋነኛ ዓላማ የዩናይትድ ስቴትስና የአፍሪቃን የኤኮኖሚ ግንኑነት ይበልጥ ማጠናከር መሆኑ ተገለፀ። ሶስት ቀናት የሚዘልቀው የዚህ ጉባኤ ትኩረት በሁለቱ ክፍለ ዓለማት መካከል የሚካሄደው ንግድ እንደሚሆን የአሜሪካን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

በጉባኤው ላይ ለተወሰኑ የአፍሪቃ ሃገራት ምርቶች በአሜሪካ የገበያ እድል የሚሰጠው (AGOA)አጎዋ የተባለው የአሜሪካን መርሃ ግብር መራዘም እና ከሰሃራ በስተደቡብ በሚገኙ የአፍሪቃ ሃገራት የኤሌክትሪክ አቅርቦትን በእጥፍ ለማሳደግ የተያዘው እቅድ ውይይት ይደረግበታል። በአሁኑ ጊዜ የዩናይትድ ስቴትስና የአፍሪቃ ንግድ፤ አፍሪቃ ከአውሮፓ ኅብረትና ከቻይና ጋር ከምታካሂደው ንግድ ቀጥሎ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። በተለይ ባለፉት 10 ዓመታት በአፍሪቃ የቻይና የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ማደግና ቻይና በአፍሪቃ ላይ ያሳደረችው ተፅእኖ ዩናይትድ ስቴትስ ይህን መሰሉን ጉባኤ ከአፍሪቃ መሪዎች ጋር ለማካሄድ እንዳነሳሳት ቢነገርም ዩናይትድ ስቴትስ ግን ዓላማው ከዚህ ጋር የሚገናኝ እንዳይደለ አስታውቃለች። በዚህ ጉባኤም አሜሪካ ለንግድ ዉሎች፣ የሰላም ማስከበር፣ እንዲሁም የምግብ ምርቶችና የኃይል ማመንጫዎችን ለማስፋፋት ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገደማ ሥራ ላይ እንደምታዉል ይፋ ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል። በጉባኤ ላይ ከአራት የአፍሪቃ ሃገራት ማለትም ከማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ከሱዳን ከኤርትራ ና ከዚምባብዌ መሪዎች በሰተቀር የተቀሩት የአፍሪቃ ሃገራት መሪዎች ተጋብዘዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ስለ አፍሪቃ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ለጉባኤተኞቹ እንዲያነሱ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች አሳስበዋል።

ዛሬ በዋሽንግተን ዲሲ ዩናይትድ ስቴትስ የሚካሄደዉ የአፍሪቃ አሜሪካ ጉባኤ ዩናይትድ ስቴትስ ፈጣን እድገት እያስመዘገበች የምትገኘዉ የአፍሪቃ አህጉር ላይ ያላትን ፍላጎት እንደሚያሳይ ነዉ የተነገረዉ። የጉባኤዉ አዘጋጆች ዓላማዉ የተጠናከረዉ የቻይና አፍሪቃ የንግድ ግንኙነት ያስከተለዉ ነዉ የሚለዉን ጥርጣሬ ወደጎን ነዉ ያደረጉት። ይልቁንም የቻይና ትኩረት እንደነዳጅ ዘይትና ማዕድናት ያሉ የአፍሪቃ ጥሬ ሃብቶች ላይ መሆኑን በመጠቆም የዩናይትድ ስቴትስ ፍላጎት ደግሞ ከዚያ የላቀ መሆኑን ለማስረዳት ይጥራሉ። በዚህ ጉባኤ አፍሪቃዉያት ሃገራት የዩናይትድ ስቴትስ ባለሃብቶችን ለመሳብ ያላቸዉን የሚያሳዩበት፤ አሜሪካ በፋንታዋ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ፣ የኃይል አቅርቦት እንዲሁም የምግብ ምርቶች የሚስፋፉበትን ዘርፍ ለመደገፍ ገንዘብ የምታቀርብበት እንደሚሆን ነዉ የሚጠበቀዉ። ለንግድ ዉሎች፣ ለሰላም ማስከበርና ለምግብ ምርት ማስፋፊያ መርሃግብሮችም ዩናይትድ ስቴትስ ወደአንድ ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንደምትመድብ ይፋ ታደርጋለች ተብሏል። እስከ ረቡዕ በሚዘልቀዉ የሶስት ቀን ጉባኤም 50 የሚሆኑ የአፍሪቃ ሃገራት ይሳተፋሉ።

አበበ ፈለቀ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic