የአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤ ትኩረት | አፍሪቃ | DW | 29.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤ ትኩረት

የዘንድሮዉ የአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤ ትኩረቱን «ሴቶችን ለተለያየ ሥልጣን ማብቃት» ላይ በማድረግ የአፍሪቃ የ2063አጀንዳ የተሰኘዉን እንደሚያጠናክር ይጠበቃል።

ሆኖም የዚህ ዓመቱ ጉባኤ በሰሜን ናይጀሪያ የሚንቀሳቀሰዉ የቦኮሃራም ጥቃት መጠናከር፣ የኤቦላ ወረርሽኝ ያስከተለዉ ተፅዕኖ እንዲሁም በደቡን ሱዳንና በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክና ሶማሊያ ያለፉ ግጭት ያጠላበት ይመስላል።

«ቦኮሃራም በሕዝብ ላይ በሚፈፅመዉ አሳዛኝ ድርጊት፤ ወጣት ልጃገረዶችን ከትምህርት ቤት ማገት፣ መንደሮችን ማቃጠል፣ ማኅበረሰቡን ሁሉ ማሸበር እና መግደል በጣም ተጨንቀናል። በአንድ አካባቢ የነበረዉ ቡድን አሁን ወደምዕራብ አፍሪቃና ማዕከላዊ አፍሪቃ ሲስፋፋ እያየን ነዉ። ርምጃ መወሰድ ያለበት አሁን ነዉ። እየተስፋፋ የሄደዉን ስጋት በጋራ ርምጃ መመከት ይኖርብናል።»

በያዝነዉ ሳምንት መጀመሪያ ነዉ የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ንኮሳንዛና ድላሚኒ ዙማ የጉባኤዉን ዋነኛ መነጋገሪያ አጀንዳ በዚህ መልኩ ግልፅ ያደረጉት። የአፍሪቃ ኅብረት ሰሜን ናይጀሪያ ዉስጥ በሚንቀሳቀሰዉ ፅንፈኛ እስላማዊ ቡድን ቦኮሃራም ላይ ወታደራዊ ርምጃ ለመዉሰድ አልሟል። ይህም ባለፈዉ መስከረም ወር ናይሮቢ ላይ የመንግስት ባለስልጣናት ፅንፈኛ እስላማዊ የሽብር ድርጅቶችን ለመዋጋት ልዩ ስለበጀት የተነጋገሩበት ዝግጅት አካል ነዉ። በአዲስ አበባዉ ጉባኤ ደግሞ የሃገራቱ መሪዎች አሁን 3000 ገደማ ጠንካራ የመንግሥት ወታደሮችን ችግሩ ወደጠናባቸዉ ናይጀሪያ፣ ኒዠር፣ ቤኒን፣ ቻድ እና ካሜሮን ስለመላክ ይነጋገራሉ።

Nkosazana Dlamini-Zuma

የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ንኮሳንዛና ድላሚኒ ዙማ

የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ቀደም ብለዉ ባለፉት ሳምንታት ከጋና ፕሬዝደንት ድራማኒ ማሃማ ተገናኝተዉ ሲነጋገሩ የሎጀስቲክስና ወታደራዊ ድጋፍ ከአዉሮጳ ኅብረት እንደሚያገኙ አረጋግጠዋል። እንዲህ ያለዉ ዘመቻ ሲታሰብ የናይጀሪያን ፍላጎት ማካተት እንዳለበት የፀጥታ ጥናት ተቋም የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር ሰሎምን ደርሶ ያሳስባሉ።

«ናይጀሪያ እንዲህ ያለ ወታደራዊ ዘመቻ በግዛቷ እንደማትፈልግና ቦኮሃራምን ራሷ እንደምትቋቋም ገልጻለች። እንዲህ ያለዉ የፖለቲካዊ መዕክት ነዉ በተደጋጋሚ ከናይጀሪያ ሲነገር የተደመጠዉ። ስለዚህ ናይጀሪያ የዓለም አቀፍ ወታደራዊ ኃይልም ሆነ የፈረንሳይን ጦር ግዛቷ ዉስጥ እንዲዘምት ትፈቅዳለች ብዬ አልገምትም።»

እንዲያም ሆኖ በትናንትናዉ ዕለት የተመድ የሳህል አካባቢ ልዩ መልዕክተኛ የቦኮሃራም የሽብር እንቅስቃሴ ናይጀሪያ ላይ ብቻ የተወሰነ ባለመሆኑ፤ አቡጃ ብቻዋን ለዚህ ችግር መፍትሄ ልታገኝ እንደማትችል አመላክተዋል። በሰሜን ናይጀሪያና የሶማሊያዉ ፅንፈኛ እስላማዊ ታጣቂ ቡድን አሸባብ ሰሜናዊ ኬንያ ዉስጥ አሰቃቂ የሽብር ጥቃት ካደረሱ ወዲህ ለአፍሪቃ ችግር አፍሪቃዉ መፍትሄ የሚለዉ መፈክር ምን ያህል ሊያስኬድ እንደሚችል ጥያቄ አስነስቷል። ለዓመታት የተነገረለት እንዲህ ባለዉ ወቅት ፈጥኖ የሚሠማራ የአፍሪቃ ተጠባባቂ ኃይል በምህፃሩ ASFን የመገንባቱ ነገር እስካሁን እዉን አልሆነም። በሌላ በኩል አህጉሪቱ የአፍሪቃ ለቀዉስ አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ ኃይል በሚል በሁለተኛ ደረጃ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ለማደራጀት መሞከሯን በበርሊኑ የሳይንስና ፖለቲካ ተቋም የአፍሪቃ የሰላምና የፀጥታ ምህንድስና ተመራማሪ ዬዲዝ ሽቶክ ይተቻሉ።

Nigeria Selbstmordattentat

የተስፋፋዉ የቦኮሃራም ጥቃት

«የተናጠል ግብረ-ሐይል መመሥረት፤ አጠቃላዩ ትልቅ ሐይል ጋር ሊቀናጅ አይችልም።ይልቁንም የሚያስፈልገዉ ፈጥኖ እርምጃ መዉስድ የሚችልበትን ሥልት መፈለግ ነዉ። ግን ይህ ምን ያህል ተግባራዊ ይሆናል? የአፍሪቃ ኅብረት በሰላምና ፀጥታዉ ምክር ቤቱ ሥር ይህን ሐይል ማቋቋምና ማዝመቱ ይሳካል ወይ የሚለዉን መገመት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ለጊዜዉ የሚታየዉ ፈጣን መፍትሄ መፈለጉ ይመስላል።»

ተንታኟ እንዲህ ያለዉን አህጉራዊ ኃይል ለማቋቋም አስፈላጊ ከሆነዉ አቅም በተጓዳኝ የአፍሪቃ ኅብረትን የፀጥታ አስከባሪ ኃይል በመፍጠሩ ረገድ በሃገራቱ መካከል መቀናናት መኖሩንም አስተዉለዋል። ለምሳሌም በአካባቢዉ ኃያል ሀገር ናይጀሪያና ከፈረንሳይ ጋ ትስስር ባላቸዉ ቻድና ኒዠር መካከል ፀረ ቦኮሃራም ኃይል ቢኖር የማንቀሳቀሱን ሀላፊነት ማን ይረከብ በሚለዉ ላይ ያለዉ ልዩነት ምሥጢር አይደለም። ሌላዉ ኅብረቱ በዚህ ጉባኤዉ የሚመለከተዉ በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች መካከል የቀጠለዉን ግጭትና ዉዝግብ ነዉ። እርግጥ ነዉ የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪርና የአማፅያኑ መሪ ሪየክ ማቻር ባለፈዉ ሳምንት አሩሻ ታንዛኒያ ላይ የተከፈለዉን ገዢ ፓርቲ SPLMን መልሰዉ አንድ ለማድረግ ተስማምተዉ ቢፈራረሙም ዘላቂ ሰላም ሊያሰፍን የሚችል ስምምነት አዲስ አበባ ላይ ከጉባኤዉ ጎን በሚኖራቸዉ ንግግር የማምጣታቸዉ ነገር የሚታይ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ የዩጋንዳዉ ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት የተቋቋመበትን የሮማዉን ዉል የፈረሙት የፈረሙ የአፍሪቃ ኅብረት አባል ሃገራት እንዲወጡ እንደሚቀሰቅሱም ይጠበቃል። በሌላ በኩል ያለዉ መልካን ዜና የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ኮሚሽን በኤቦላ ወረርሽኝ በአህጉሪቱ ኤኮኖሚ ላይ ያደረሰዉ ተፅዕኖ መጠነኛ መሆኑ መገለፁ ነዉ።

ሉድገር ሻዶምስኪ/ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic