የአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤ ተጠናቀቀ | አፍሪቃ | DW | 31.01.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤ ተጠናቀቀ

26ኛው የአፍሪቃ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ ተጠናቀቀ። በጉባኤው በርካታ ጉዳዮች ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፤ የቡሩንዲ ቀውስ እና የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት የሽብር ስጋት ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ እንደነበር ተገልጧል።

ጉባኤው ላይ ትናንትና ተገኝተው የተናገሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሓፊ ባን ኪሙን ኅብረቱ የጎሣ እና የፖለቲካ ቀውስን በቡሩንዲ ለመታገል «የመከላከል እና ጥበቃ ተልዕኮ»ን ለማቋቋም ማቀዱ የሚወደስ ነው ብለዋል። የኅብረቱ ድርጊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተግባርን የሚያግዝ ነው ሲሉም አክለዋል። ከዚህም ሌላ ባን ኪ ሙን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን ለመታደግ አንገብጋቢ የነፍስ አድን ርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አሳስበዋል። ኢትዮጵያ ከ30 ዓመት በፊት ከገጠማት አሰቃቂ ድርቅ ወዲህ አኹንም ትግል ላይ ናት ብለዋል ዋና ጸሓፊው። በአሁኑ ወቅት አስቸኳይ ርዳታ የሚያስፈልገው 10.2 ሚሊዮን ዜጋ በወራት ውስጥ በእጥፍ ሊያድግ እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስጠንቅቋል።

በኤል ኒኖ የተነሳ የተከሰቱ ጎርፎች እና ያልተጠበቁ ዝናማማ ወቅቶች በአብዛኛው የአፍሪቃ ክፍል የሚራበው ሰው ቁጥር አስደንጋጭ በሆነ መልኩ እንዲጨምር አድርጓል ብሏል ድርጅቱ። በተለይ የኢትዮጵያ ግን ልዩ ትኩረት ያሻዋል ሲል አክሏል። የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚንሥትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለሰብአዊ ርዳታ ከሚያስፈልጋት $1.4 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ያላት ግማሽ ያኽሉን ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል። የሰብአዊ ርዳታ ፈላጊው ቁጥርም ካለፈው ዓመት በከፋ ሁኔታ መባባሱን ጠቅሰዋል።

ከትናንት ጀምሮ እስከዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ ሲኪያሄድ በቆየው የአፍሪቃ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይም ወደ ቡሩንዲ ሰላም አስከባሪ ጦር የመላኩ ሐሳብ ተመክሮበታል። በመጨረሻም ኅብረቱ ያለ ቡሩንዲ ይኹንታ የሰላም አስከባሪ ወታደሮችን ወደ ሀገሪቱ ላለመላክ መወሰኑን አስታውቋል።የአፍሪቃ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በሊቢያ የሰፈነውን ግጭት ለማብረድም በአምስት ዓመራሮች ሥር የሚገኝ ግብረ ኃይል ማደራጀቱን አስታውቋል። ሊቢያ ውስጥ ራሱን «እስላማዊ መንግስት» እያለ የሚጠራውን ቡድን የተለያዩ ይዞታዎችን መቆጣጠሩ ይታወቃል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ልደት አበበ