የአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤና ማላዊ | አፍሪቃ | DW | 13.06.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤና ማላዊ

የአፍሪቃ ኅብረት የመጪዉ ሐምሌ ወር ጉባኤዉን አዲስ አበባ ላይ እንደሚካሄድ ይፋ አድርጓል። ጉባኤዉ እንዲካሄድ የታቀደዉ ማላዊ ነበር። ዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀል ችሎት ICC የእስር ማዘዣ የቆረጠባቸዉ የሱዳኑ ፕሬዝደንት ዑመር አልበሽር፤

default

በስብሰባዉ ላይ እንዲገኙ መጋበዛቸዉን ያልደገፈችዉ ማላዊ እንደማታስተናግድ ያሳወቀችዉ ባለፈዉ ሳምንት ነዉ። የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዝደንት ማላዊ እንዲህ ዓይነቱን የድርጅቱን ጉባኤ ለማስተናገድ ዝግጁ አይደለችም ይበሉ እንጂ ዋናዉ በICC ፈራሚ ሀገርነቷ ከለጋሽ ሀገሮች የሚመጣባትን ተፅዕኖ ለመሸሽ እንደሆነ ነዉ የተገለፀዉ።

አዣንስ ፍራንስ ፕረስ የጠቀሳቸዉ የማላዊ ምክትል ፕሬዝደንት ኩምቦ ካቻሊ መንግስታቸዉ 54 አባላት ላሉት የአፍሪቃ ኅብረት ላስቀረበዉ አስገዳጅ አማራጭ አልተንበረከከም። የአፍሪቃ ኅብረት በመጪዉ ሐምሌ ጉባኤዉ ላይ የመላዉ አባል መንግስታት መሪዎች እንዲገኙ በማሳሰብ ማላዊ የሱዳኑን ፕሬዝደንት ዑመር አልበሽርን ጭምር እንድትጋብዝ ጠይቋል። ካልሆነ ግን ጉባኤዉን የማስተናገዱ እድል ለሌላ ሀገር እንደሚሰጥ አመልክቷል። ማላዊ የዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀል ፍርድ ቤት ICC የተቋቋመበትን ዉል ከፈረሙ 33 የአፍሪቃ ሀገሮች አንዷ ናት። ባለፈዉ ሳምንት መጀመሪያ የICC ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሉዊስ ሞሬኖ ኦካምፖ ለጋሽ ሀገሮች ፕሬዝደንት አልበሽርን ለማሰር የማይተባበሩ መንግስታትን መርዳት እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።

Luis Moreno-Ocampo

ሉዊስ ሞሬኖ ኦካምፖ

ከቆዳ ስፋቷ አንፃር በህዝብ ብዛት የተጨናነቀችዉ ደሃ አፍሪቃዊት ሀገር ማላዊ ከዓመታዊ በጀቷ 40 ከመቶ የሚሸፈነዉ በዉጪ ርዳታ ነዉ። የወቅቱ የአፍሪቃ ኅብረት ሊቀመንበር በመሆኗ ኅብረቱን ጉባኤ ማስተናገድ የነበረባት የባህር በር አልባዋ ማላዊ ምጣኔ ሃብቷን ለመደጎም የምታገኘዉን ርዳታ መመዘን ተገደደች። እናም ሀገሪቱ ከለጋሽ መንግስታት ጋ ልትገባበት የምትችለዉን ዉዝግብና ዉጥረት ያገናዝበዉ በአዲሷና የመጀመሪያዋ የሀገሪቱ ሴት ፕሬዝደንት ጆይስ ባንዳ የሚመራዉ የማላዊ መንግስት የአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤ በሌላ ሀገር እንዲስተናገድ ወሰነ። ዉሳኔዉን በደቡብ አፍሪቃ የዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ተቋም ተመራማሪ ቶም ዊለር መርህን መሠረት ያደረገ ሲሉ አድንቀዉታል። የአልበሽርን መገኘት ያልፈለገችዉ ማላዊን ዉሳኔ ተከትሎ የጉባኤዉን ቦታ የቀየረዉ የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽነር ዋና ጸሐፊ ጄን ማፋሶኒ ስብሰባዉ የአፍሪቃ መንግስታት እንደመሆኑ ሁሉም መገኘት እንደሚችሉ ነዉ የገለፁት፤

«ሁሉም አባል ሀገሮች ወይም መሪዎች እንዲገኙ ተጋብዘዋል። ምክንያቱም ይህ ስብሰባቸዉ ነዉ። ስለዚህ ሁሉም መሪዎች ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። እናም በራሳቸዉ ዉሳኔ መሠረት ይመጣሉ፤ አንዳንዶቹ ራሳቸዉ አንዳንዶች ደግሞ ተወካዮች ይልካሉ፤ ሆኖም ሁሉም መሪዎች በነፃነት በመምጣት በጉባኤያቸዉ መገኘት ይችላሉ።»

በአዉሮጳዉያኑ 2009ዓ,ም ዓለም ዓቀፉ የወንጀል ችሎት በሰብዓዊነት ላይ ወንጀል በመፈፀፍ የሚያቀርበዉን ክስ በሚመለከት ላለመተባበር የአፍሪቃ ኅብረት ዉሳኔ አሳልፏል። በወቅቱም ከቦትስዋና በቀር የችሎቱ መቋቋሚያ ዉል ፈራሚ የሆኑ ሌሎች የአፍሪቃ ሀገሮች ማላዊን ጨምሮ ማለት ነዉ ዉሳኔዉን በይፋ አልተቃወሙትም ነበር።

Gipfel Afrikanische Union Addis Abeba

የአፍሪቃ ኅብረት አባል መንግስታት መሪዎች

ናይሮቢ ኬንያ የሚገኘዉ ዓለም ዓቀፍ የፖለቲካ መርህና የዉዝግብ ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር ናዱንጉ ወይናይና የአፍሪቃ ኅብረት አባል መንግስታት ICCን አስመልክቶ ያላቸዉ አቋም የተለያየ እንደሆነ ይገልፃሉ፤

«አፍሪቃ ኅብረትና መሪዎቹ የዓለም ዓቀፉን የወንጀል ችሎት ክሶች፤ ወይም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሚያስጠይቅ ወንጀል ፈፀሙ በሚባሉ ሰዎች በሚመለከት የጋራ የሚባል አቋም ኖሯቸዉ አያዉቅም። ይህን በሚመለከት እያንዳንዱ ሀገር የየግሉን ርምጃ የመወስድ ነገር ነዉ ያለዉ። ሆኖም በጉዳዩ ላይ የምናገኘዉ የአፍሪቃ ኅብረትን ፖለቲካዊ አቋም ነዉ። ተግባራዊ ማድረጉ ላይ እጅግ ትልቅ ችግር አለ። ምክንያቱን እነዚህ ሀገሮች የተለያዩ ፍላጎት ነዉ ያላቸዉ፤ ያንን የተለያየ ፍላጎት ደግሞ ለማጣጣም እጅግ አዳጋች ይሆናል።»

Ankunft Al Baschir in Ägypten Kairo

ዑመር አልበሽር የሱዳን ፕሬዝደንት

በሱዳኗ ምዕራባዊ ግዛት ዳርፉር የጦር ወንጀል ፈፅመዋል በሚል በዓለም ዓቀፉ ፍርድ ቤት የሚፈለጉት ፕሬዝደንት ዑመር አልበሽር፤ የእስር ማዘዣ ከተቆረጠባቸዉ ወዲህ ወደተለያዩ ሀገሮች ሄደዋል። ማላዊ በዋነኛነት ጉባኤዉን ላለማስተናገድ የአልበሽርን መገኘት ምክንያት ብታደርግም ከዝግጅት አኳያ የአቅም ጉዳይ እንዳለም ተጠቅሷል።

ዘገባዎች እንደሚሉት አልበሽር የኅብረቱ 19ኛ ጉባኤ ሀገራቸዉ ከደቡብ ሱዳን ጋ የገባችበትን ዉዝግብ እንዲመለከት ይፈልጋሉ። ለዚህም ነበር ማላዊ ሊሎንግዌ ላይ በሐምሌ ወር መባቻ ሊካሄድ ታቅዶ በነበረዉ ስብሰባ ለመሳተፍ የተሰናዱት። አሁን ያለስጋት አዲስ አበባ መሄድ ይችላሉ፤ ኢትዮጵያም የICC ፈራሚ ባለመሆኗ እሳቸዉን ለማሰር አትገደድም።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic