የአፍሪቃ ኅብረት እና የተሀድሶ እቅዱ | አፍሪቃ | DW | 27.01.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የአፍሪቃ ኅብረት እና የተሀድሶ እቅዱ

የአፍሪቃ ሀገራት ርዕሳነ ብሔር እና መራሕያነ መንግሥት በነገው ዕለት 30ኛውን  የአፍሪቃ ህብረት በአዲስ አበባ ይጀምራሉ። ሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባዔ ለሚሳተፉትአፍሪቃውያኑ መሪዎች በወቅቱ ቅድሚያ የያዘው ዋነኛ ጉዳይ አንድ ጠንካራ እና ሰላማዊ አፍሪቃ መፍጠር የሚለው  ሀሳብ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:37

የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ

መሪዎቹ የሕዝቦቻቸውን ኑሮ ማሻሻል ስለሚችሉበት ጉዳይ ከተወያዩ እና እዚህ ለመድረስም  ህብረቱ ጠቃሚ ድርሻ ማበርከት እንዲችል ምን ዓይነት ተሀድሶ ማድረግ እንደሚገባ በሰፊው ከመከሩ በኋላ በአህጉሩ ሁለንተናዊ ለውጥ የሚያመጡ ውሳኔዎች ያስተላልፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አንዳንድ ታዛቢዎች ይገምታሉ። 
አፍሪቃውያን መሪዎች የአፍሪቃ ህብረትን ተሀድሶ ለማድረግ ባለፈው ዓመት መስማማታቸው ይታወሳል። 55 ሀገራት የተጠቃለሉበት ይኸው አካል ለሰላም ማስከበሪያ ተግባራት የሚያስፈልገው ገንዘብ እጥረት ገጥሞታል።  ስራውን ለማካሄጃ ዛሬም በብዛት በውጭ ድጋፍ ላይ ጥገኛ ነው። እጎአ ከ2015 ዓም በጀት መካከል 72% ዩኤስ አሜሪካን እና የአውሮጳ  ህብረትን ከመሳሰሉ ለጋሾች የተገኘበትን ድርጊት ታዛቢዎች እንደ ድክመት ጠቅሰዋል። ህብረቱ ካጋጠመው የገንዘብ እጥረት ጎን በተጨማሪ፣ ለፀጥታ ስጋቶች ፈጣን ርምጃ ያልወሰደበት አሰራሩ ትችት እያሰነዘረበትም ነው። 
የአፍሪቃ ህብረት ተሀድሶ ለማድረግ የጀመረውን ጥረት የህብረቱ ሊቀ መንበር የጊኒ ፕሬዚደንት አልፋ ኮንዴን በመተካት እንዲተኩ ባለፈው ዓመት ሀምሌ ወር በተካሄደው የመሪዎች ጉባዔ የተመረጡት እና ከጥር 2018 ዓም ወዲህ ስልጣናቸውን የጀመሩት  የርዋንዳ ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ በቀዳሚነት እየመሩት ነው። 
ካጋሜ እንደሚሉት፣ የአፍሪቃ ህብረት ተሀድሶ ትኩረት በፊናንሱ አኳያ ራሷን የቻለች እና የተዋሀደች አፍሪቃ መፍጠር ነው። ምክንያቱም፣ ካጋሜ «ከውጭ የሚገኘው ድጋፍ  በማንኛውም ጊዜ ሊደርቅ የሚችል በመሆኑ ህብረቱ በዚሁ ድጋፍ ላይ ጥገኛ የሚሆንበት ድርጊት ለአፍሪቃ በጣም ጎጂ ነው።»  በማለት ኒው ታይምስ በተባለው የሀገራቸው ጋዜጣ ላይ ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት መጻፋቸው ይታወሳል። የተሀድሶውን   መሪ ሀሳብ እና ዓላማ መጠበቅ አስፈላጊ ሲሆን፤ ባንዳንድ ጉዳዮች ላይ አባል ሀገራት   ሌላ ሀሳብ ለመቀበል ዝግጁ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።ይሁንና፣ ይኸው የካጋሜ ዓላማ ፣ ብዙዎቹ የህብረቱ አባል ሀገራት መሪዎች የየራሳቸውን መንገድ በመከተል ላይ በመሆናቸው ፣ እውን ሊሆን የማይችል ፣ ሕልም ብቻ ሆኖ እንደሚቀር ነው ታዛቢዎች የሚናገሩት።


በአዲስ አበባ የሚገኙት የፕሪቶርያው ዓለም አቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም፣ በምህፃሩ አይ ኤስ ኤስ  ተመራማሪ ያን ቤድዚጊም የአፍሪቃ ህብረት የተሀድሶው ሂደት መቀጠል እንዳለበት ያምናሉ። እንደ ቤድዚጊ አስተያየት፣ ዘላቂ ውጤት ለማግኘት እና ራስን ለመቻል ከተፈለገ የተነቃቃው ተሀድሶን ወደፊት ማራመድ አስፈላጊ ይሆናል።
«ከአፍሪቃ ህብረት በጀት መካከል ሁለት ሶስተኛው ባለፉት ዓመታት የተገኘው ከውጭ ለጋሾች ነው። እና የህብረቱ ስራን ፍቱንነት ፣  በተመለከተ አፍሪቃውያን ለድርጅቱ የሚከፍሉትን መዋጭዋቸውን ማሳደግ ይኖርባቸዋል። ይህን በሚያደርጉበት ጊዜ ህብረቱ ሰላምና ፀጥታ፣ መልካም አስተዳደርና ልማትን  በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ሕጋዊ መሆኑን ሊያረጋግጡ ይችላሉ። » 
በዚሁ ረገድ አንዳንድ መሻሻል ታይቷል፣ ቀጣይ ይሆናል አይሆንም ብሎ አሁን ለመናገር ግን አዳጋች መሆኑን አይ ኤስ ኤስ  ተመራማሪ ያን ቤድዚጊም አስታውቀዋል።
«ተሀድሶው በህብረቱና በመዋቅሩ ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ ጠብቆ ማየት ግድ ይላል። በህብረቱ ስራ ላይ በተለይ ችግር የሚደቅኑ ሁኔታዎችን ለይቶ ማወቅ እና አቅሙን  ለማሳደግ አስፈላጊው  ገንዘብ ማቅረብ ወሳኝ ነው። ይህ ተግባራዊ በሚደረግበት ጊዜ ያኔ ውጤታማ መሆን ትችላለህ። »
አባል ሀገራት  ለአፍሪቃ ህብረት ከኢምፖርት ቀረጥ 0,2 ከመቶ ለመክፈል የቀረበውን ሀሳብ ተስማምተውበታል። ስምምነቱን 20 ሀገራት ሲፈርሙት፣ 14ቱ ቅርቡ  ሊተረጉሙት ነው ተብሏል። ሁሉም እኩል ለማይጀምሩበት ድርጊት ሀገራቱ የሚገኙበት ሁኔታ ምክንያት መሆኑን ቻታም ሀውስ የተባለው በለንደን የሚገኘው የብሪታንያውያኑ የፖለቲካ ጥናት ተቋም የአፍሪቃ ክፍል ኃላፊ አሌክስ ቫይንስ ገልጸዋል።

 «እዚህ ላይ ወጥ የሆነ አሰራር የመከተል  ጉዳይ ይነሳል። ምክንያቱም አንዳንድ ያካባቢ አፍሪቃውያን ድርጅቶች ፣ ለምሳሌ የምዕራብ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ማህበረሰብ፣ ,ምህፃሩ ኤኮዋስ አባላል ሀገራት ወደ ሀገራቸው በንግድ በሚገባ ዕቃ ላይ በሚያስከፍሉት ቀረጥ ወጪያቸውን ይሸፍናሉ። ፉክክር አለ እና ምዕራብ አፍሪቃውያኑ መንግሥታት ሌላ ቀረጥ የማስተዋወቁ  ሀሳብ ያን ያህል አያስደስታቸውም። የአፍሪቃ ህብረት  መፍትሔ ሊያገኝላቸው የሚገቡ ሌሎች ተመሳሳይ አዳጋች ጉዳዮች አሉ። »
አሌክስ ቫይንስ በአፍሪቃ  ህብረት ተሀድሶ ለማነቃቃት የሚያስችሉ ጥሩ ሀሳቦች እንደቀረቡ ይሰማቸዋል፣ ጥያቄው ግን ገቢራዊነቱ ላይ ነው ይላሉ። ህብረቱ በውጭ ድጋፍ ላይ ብቻ ሳይሆን ደቡብ አፍሪቃ፣ አልጀሪያ፣ ግብፅ እና ናይጀሪያን በመሳሰሉ ጥቂት አፍሪቃውያት ሀገራት መዋጮም ላይ ጥገኛ መሆኑን ነው አሌክስ ቫይንስ ያጎሉት። በዐረባውያቱ ሀገራት  የሕዝብ ዓመፅ በተቀሰቀሰበት እና የምርት ዋጋ በቀነሰበት ጊዜ ለህብረቱ የሚከፈለው መዋጮም ቀጣይነት ማጣቱን ነው ቫይንስ ያስረዱት።
« 55 ም ሀገራት በሙሉ አይደሉም በአንድ ዓይነት ሁኔታ የሚገኙት። አንዳንድ ከፍተኛ እድገት ያስገኛሉ የሚባሉ ሲኖሩ ሌሎች ጥሩ እደገት የማያሳዩ ሀገራት አሉ።   
ቫይንስ እንደሚሉት፣ የአፍሪቃ ህብረት በአህጉሩ ገንዘቡን ለማሰራት የሚፈልጉ ሁሉን  የሚያያበረታታ ሲሆን፣ በመሪዎቹ ጉባዔ ላይ ቻይና ዋነኛ መወያያ ርዕስ ትሆናለች ብለው ይገምታሉ። ይሁንና፣ በአውሮጳ አንፃር ቻይና ለአፍሪቃ ህብረት በጀት ድጋፍ ሰጪ ከሚባሉት ሀገራት መካከል አትቆጠርም፣ እና በበጀቱ ጥያቄ ላይ  በሚካሄደው ክርክር ላይ አነስተኛ ሚና ነው የምትጫወተው። ያም ቢሆን ግን፣  የአፍሪቃ ህብረት እና ቻይና በቅርብ ተባብረው ይሰራሉ። ቻይናም እጎአ በ2015 ዓም ወደ አፍሪቃ ህብረት ቋሚ ተልዕኮ ልካለች፣ አዲሱን የአፍሪቃ ህብረት ጽሕፈት ቤትንም የገነባችው ቻይና ስትሆን፣ በብዙ አፍሪቃውያት ሀገራት ውስጥ መሰረተ ልማቱን በመገንባቱ ተግባር ላይ ሰፊ ድርሻ እያበረከተች ነው። ይሁንና፣ ሰፊ ክፍፍል የሚታይበት የአፍሪቃ ህብረት አሁንም ፈታኝ ተግዳሮቶች ይጠብቁታል። ህብረቱ የወጠነው የተሀድሶ እቅድ የበቂ አፍሪቃውያን መሪዎችን ስምምነት ማግኘቱን ብዙ የፖለቲካ ተንታኞች ይጠራጠሩታል።


አርያም ተክሌ/ማርቲና ሺቭኮቭስኪ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic