የአፍሪቃ ኅብረት አንገብጋቢ ጉዳዮች  | አፍሪቃ | DW | 30.01.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የአፍሪቃ ኅብረት አንገብጋቢ ጉዳዮች 

የቻድ ውጭ ጉዳይ ሚኒሥትር ሙሳ ፋቂ ማሐማት የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሆነው በ28ኛው ጉባኤ ተመርጠዋል። ሙሳ ፋቂ ማሐማት በመጨረሻው ዙር ድምፅ አሰጣጥ የኬንያዋን ውጭ ጉዳይ ሚኒሥትር አሚና ሞሐመድን መርታታቸውን ዲፕሎማቶች ተናግረዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:06

የአፍሪቃ ኅብረት የቻዱን ሙሳ ፋቂ ማሐማት የኮሚሽኑ ሊቀ-መንበር አድርጎ መርጧል

አዲሱ ሊቀ-መንበር የጥይት ተኩስ ድምፅ በባሕላዊ ዝማሬዎች የሚተኩባት አፍሪቃ ለማየት እንደሚጓጉም ተናግረዋል። ሙሳ ፋቂ ማሐማት ከኬንያዋ ውጭ ጉዳይ ሚኒሥትር በተጨማሪ ከቦትስዋና፤ኤኳቶሪያል ጊኒ እና ሴኔጋል እጩዎች ጋር ተፎካክረዋል። የአፍሪቃ መሪዎች እና ፖለቲከኞች አንገብጋቢ ያሏቸውን የውይይት ርዕሰ ጉዳዮች ይዘው አዲስ አበባ ጉባኤ ተቀምጠዋል። በጉባኤው የየአገሮቻቸውን ምርጫ አሸንፈው ሥልጣን የያዙት አዳማ ባሮው እና ናና አኩፎ አዶ ከነ ሮበርት ሙጋቤ ጋር በአንድ አዳራሽ ታድመዋል። የአህጉሪቱ መሪዎች እና ተደማጭ ፖለቲከኞች የአፍሪቃ ኮሚሽንን አወቃቀር እንደገና ሊፈትሹ አቅደዋል። የኅብረቱ አመታዊ በጀትም በዚሁ ስብሰባ ይመከርበታል። 

ደቡብ አፍሪቃዊቷ ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ በጎርጎሮሳዊው 2012 ዓ.ም. የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበሪት ሆነው ሲመረጡ የአህጉሪቱ ሰማይ የተስፋ ዳመና አርግዞ ነበር። በርካታ ተንታኞች ድላሚኒ ዙማ የተጣለበትን ኃላፊነት መከወን ተስኖታል እየተባለ የሚወቀሰውን የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ሥልጣን ለተተኪያቸው ሲያስረክቡ እንደታቀደው ለውጥ ለማምጣታቸው እርግጠኛ አይደሉም። የኅብረቱ ኮሚሽን ከውስጥም ሆነ ከውጪ የአወቃቀር እና የአሰራር ለውጥ ማድረግ አለበት የሚሉ ድምፆች እየተሰሙ ነው። ኮሚሽኑ ፖሊሲ ከማርቀቅ ያለፈ ሥልጣን የለውም፤ የድርጅቱን መመሪያዎች ለማስፈጸምም ሆነ ህግጋት በሚጥሱ አባል አገራት ላይ ማዕቀብ መጣል የሚያስችል ተቋማዊ አቅም አለመኖሩ በተንታኞች ከሚጠቀሱት መካከል ይገኙበታል። የኮሚሽኑ ሊቀ-መንበር የራሱን ምክትል ሊቀ-መንበርም ሆነ ስምንት ኮሚሽነሮቹን

የመምረጥ ሥልጣንም የለውም። በጠቅላላ ጉባኤው የሚሾሙ ኮሚሽነሮችን ቦታ መቀየር ማባረርም አይችልም። ኮሚሽኑን እንደገና የማዋቀር ኃሳብ የተጠነሰሰው ከአስር ዓመት በፊት ቢሆንም የርዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ በ27ኛው ጉባኤ ባለሙያዎች አዋቅረው ሞክረውታል። አዲስ አበባ ዛሬ የተጀመረው ጉባኤ የኮሚሽኑን ሥልጣንና አወቃቀር የመከለስ ፍላጎቱ እንደገፋበት ተሰናባቹ የኅብረቱ ሊቀ-መንበር ቻዱ ፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቤ ጥቆማ ሰጥተዋል። በአፍሪቃ የጸጥታ ጥናት ተቋም ተንታኝ ሆነው የሚያገለግሉት ሌስል ሎው በአዲስ አበባ ጉባኤውን በቅርበት በመከታተል ላይ ከሚገኙ መካከል አንዷ ናቸው። 

«የጉባኤው ሊቀ-መንበር ፕሬዝዳንት ኤድሪስ ዴቢ በመክፈቻው ስብሰባ ማሻሻያውን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። በትክክል ምን ለማድረግ እንደወሰኑ ግን በዚህ ወቅት የታወቀ ነገር የለም። ስንገምት ከዚህ ቀደም ከቀረበው የማሻሻያ ኃሳብ ጋር ተመሳሳይ ሳይሆን አይቀርም። የአፍሪቃ አገሮች የማሻሻያ ኃሳብ ያቀረቡት ከአስር ዓመት በፊት ነበር።»
ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ያዋቀሩት እና ዘጠኝ አፍሪቃውያን የተካተቱበት ኮሚቴ ኅብረቱ የ2063 ውጥኑን ለማሳካት ውጤታማ እና ራሱን የቻለ ተቋም አድርጎ የማዋቀር ኃላፊነት በቀደመው ጉባኤ ተቀብለዋል። ፖል ካጋሜ በበላይነት የሚመሩት የለውጥ ኮሚቴ የአፍሪቃ ኅብረትን ከገንዘብ ድጎማ ጥገኝነት የማላቀቅ እቅድም አለው። የአፍሪቃ ኅብረት በአኅጉሪቱ ለሚያከናውናቸው ተልዕኮዎች የአባል አገራት መዋጮ በገንዘብ ምንጭነት መጠቀም የተሻለው አማራጭ ተደርጎ ተይዟል። 

«የአፍሪቃ ኅብረት ሥራዎችን ወጪ ለመሸፈን ወደ አህጉሪቱ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ 0.2 በመቶ አስገዳጅ ቀረጥ የመጣል እቅድ ባለፈው ዓመት ጸድቋል። ተግባራዊነቱ ግን መጀመሪያ ካስታወቁበት ጊዜ አኳያ ዘገምተኛ ሆኖ ይታያል። በእርግጠኝነት የአፍሪቃ አገራት ኃሳቡን ተግባራዊ የማድረግ እቅድ አላቸው። ሌሎች አማራጭ 50 በመቶ የሚሆነውን የኅብረቱን ወጪ አምስቱ ባለ ግዙፍ ኤኮኖሚ አገሮች ማለትም ደቡብ አፍሪቃ፤ ናይጄሪያ፤ አንጎላ፤ግብፅ እንዲያዋጡ ማድረግ ነው። ነገር ግን በተለያዩ አገሮች ግጭቶች እና ቀውሶች በመቀስቀሳቸው የኅብረቱ ወጪ ከፍ ማለቱ አይቀርም። አባል አገራትም መዋጮ በአግባቡ አይከፍሉም።»


ሞሮኮ ከሶስት አስርት አመታት በፊት በተቃውሞ ረግጣ የወጣችውን አህጉራዊ ተቋም እንደገና ለመቀላቀል ያቀረበችው ጥያቄ በአባል አገራት ዘንድ መከፋፈል ቢፈጥርም ኅብረቱ የሚፈልገው ይመስላል። ሞሮኮ እና ንጉስ መሐመድ አምስተኛ ያላቸው የፈረጠመ ኤኮኖሚያዊ አቅም የቀድሞዋ ሊቢያ እና ሞዓመር ጋዳፊ የነበራቸውን ሚና ሊተካ ይችላል የሚል ተስፋ መኖሩን ሌስል ሎው ተናግረዋል። 

« የሞሮኮ ጥያቄ እጅጉን ከፋፋይ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ደቡብ አፍሪቃ እና አልጄሪያን የምዕራብ ሰሐራዊ ጉዳይ ሞሮኮ አባል ከመሆኗ በፊት ሊፈታ ይገባል የሚል አቋም አላቸው። በርካታ አገሮች ግን ሞሮኮ በአፍሪቃ አህጉር ውስጥ የምትገኝ እንደመሆኗ ኅብረቱን እንድትቀላቀል ፈቃዳቸው ነው። ሞሮኮ የምዕራብ ሰሐራ በቅድሚያ ከአፍሪቃ ኅብረት ትባረርልኝ የሚል ቅድመ-ሁኔታ ካላቀረበች ተቃውሞ እንደሌላት አልጄሪያ ጭምር አስታውቃለች።»
የቻዱ ውጭ ጉዳይ ሚኒሥትር ሙሳ ፋቂ ማሐማት አራት ተፎካካሪዎቻቸውን ረተው የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሆነዋል። የ54 አመቱ ጎልማሳ የሚረከቡት ሥልጣን ግን ተንታኞች «በአፍሪቃ ኅብረት ውስጥ ትርጉም ያለው የአወቃቀር ለውጥ ካልተደረገ በቀር የሚረባ አይደለም» ሲሉ የሚያጣጥሉት ነው። 


እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ 

Audios and videos on the topic