የአፍሪቃ ኅብረት ርምጃና የግብጽ ዉሎ | አፍሪቃ | DW | 05.07.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የአፍሪቃ ኅብረት ርምጃና የግብጽ ዉሎ

የአፍሪቃ ኅብረት ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት የተካሄደባትን ግብጽን ከአባልነት አገደ። ግብፅ ውስጥ፤ «የቁጣ ፣ የተቃውሞ ቀን ነው»ሲሉ የሙስሊም ወንድማማች ፓርቲ አባላት ባቀረቡት ጥሪ፣ ተከታዮቻቸው አደባባይ በመውጣት እንደተነገራቸው ፈጽመዋል።

በቅርቡ የተከሠተውን ለውጥ የሚደግፉት ወገኖች በፊናቸው ተሰባስበው ድምጻቸውን አሰምተዋል። የሙሐመድ ሙርሲ ደጋፊዎች ፣ አሁንም ፕሬዚዳንቱ ራሳቸው ናቸው በማለት ወደ ሥልጣን መንበራቸው ካልተመለሱ ወደየቤታችን አንገባም ማለታቸውም ተሰምቷል። በግብፅ የተከሠተው የፖለቲካ ቀውስ ወዴት እንደሚያመራ፣ ግብጻውያኑም ሆኑ የውጭ ው ዓለም ባለማወቅ ጋራ መጋባቱ አልቀረም።

የአፍሪቃ ኅብረት ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት የተካሄደባትን ግብጽን ከአባልነት አግዷል። የኅብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ንኮሳንዛና ድላሚኒዙማ አዲስ አበባ ላይ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ፕሬዝደንት ሞሃመድ ሞርሲ ከስልጣን የተወገዱበት አካሄድ በአፍሪቃ ኅብረት መመሪያ መሠረት ህገመንግስታዊ ያልሆነ የመንግስት ለዉጥ መሆኑን አስታዉቀዋል። በዚሁ መሠረትም ዛሬ በጉዳዩ ላይ የተወያዩት የኅብረቱ ባለስልጣናት ህገመንግስታዊዉ አሰራር እስኪመለስ ድረስ ግብጽ በኅብረቱ ዉስጥ ያላት ማንኛዉንም ተሳትፎ እንዲታገድ ወስነዋል። እንዲያም ሆኖ ለግብጽ ሕዝብ ድጋፉ እንደሚቀጥል ድላሚኒዙማ አመልክተዋል።

Afrikanische Union feiert 50. Jubiläum

ንኮሳንዛና ድላሚኒዙማ

«ለግብፅ ህዝብ ያለንን ድጋፍ እንዲሁም ለተሻለ የኑሮ ሁኔታም ላለዉ ጥያቄ ድጋፋችንን ማደስ እንፈልጋለን። ሆኖም ግን ምርጫን በሚመለከት ሕገመንግስታዊዉ አካሄድ መጠበቅ አለበት።»

ድላሚኒዙማ አያይዘዉም ብሔራዊ እርቅን ተከትሎ ጊዜያዊዉ የግብጽ መንግስት ባፋጣኝ ምርጫ ያካሂዳል ብለዉ እንደሚጠብቁ ገልጸዋል። ፕሬዝደንት ሞርሲን ከስልጣን ያነሳዉ የግብጽ ጦር ኃይል ጊዜያዊ የሲቪል አስተዳደር እንደሚያቋቁም አስታዉቋል። የአፍሪቃ ኅብረት በያዝነዉ ዓመት በተመሳሳይ መፈንቅለ መንግስት የተካሄደባት ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክንም ከአባልነት አግዷል። በጦር ኃይሉ ስልጣን እንዲለቁ የተገደዱት የሞሐመድ ሞርሲ ደጋፊዎች ካይሮ ላይ የተቃዉሞ ሰልፍ ዛሬ አካሂደዋል። ተከታታይ ተቃዉሞም እንደሚቀጥል ተገልጿል። ከመስጊድ ፊት ለፊት በወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ተከበዉ የሚገኙት የሞርሲ ደጋፊዎች እሳቸዉ ወደመንበራቸዉ እስኪመለሱ ቤታችን አንገባም እያሉ ነዉ፤

«ሙርሲ ወደስልጣናቸዉ እስኪመለሱ እዚህ ከተሰበሰብንበት አደባባይ አንነሳም። እንደፈጣሪ ፈቃድ እሳቸዉ ተመልሰዉ የመላዋ ግብፅ ፕሬዝደንትነታቸዉ እስኪረጋገጥ።»

በሌላ በኩል የሙርሲ ተቃዋሚዎችም ዳግም ለጎዳና ላይ ተቃዉሞ ጥሪ እያቀረቡ ነዉ። የግብፅ ወታደራዊ ኃይል ሰላማዊ ተቃዉሞን እንደሚደግፍ ቢያመለክትም በደጋፊና ተቃዋሚዎች መካከል የአመፅ እንቅስቃሴ እንዳይኖር ስጋት እንዳለዉ አመልክቷል። ሕዝቡም ከበቀል ይልቅ ለእርቀሰላም እንዲነሳ ተማፅኗል። በድጋፍና ተቃዉሞዉ እንቅስቃሴ መካከል የሰዎች ህይወት መጥፋቱን የጠቆመዉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ሂዉመን ራይትስዎች በሁለቱም ጎራ የተሰለፉ ወገኖች ምናልባትም የፀጥታ ኃይሎች ለግድያዊ ተጠያቂ መሆናቸዉን አመልክቷል። ከረቡዕ ምሽት ወዲህ ስልጣን የለቀቁት ሞርሲ ቀጣይ ሁኔታ ምን ሊሆን እንደሚችል ግን ግልጽ አይደለም። የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ ቃል አቀባይ ጌሃድ ኤልሃዳድ ግን የተፈጸመዉ ከህግ ዉጭ ነዉ እያሉ ነዉ።

«ተከታዮቹ ሃቆች ማለትም አንደኛ ሙሉ በሙሉ መቃወማችን እንዲሁም ከህገመንግስቱና ከአገሪቱ ህግ በተቃራኒ ፕሬዝደንቱ ላይ የተፈፀመዉን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስትን ዉድቅ ማድረጋችን እንዲተኮርባቸዉ እንሻለን።»

ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ሞርሲ ይገኙበታል በተባለዉ ወታደራዊ ጽህፈት ቤት ፊት ለፊት ለተቃዉሞ ከወጡ ሶስቱ በተኩስ ህይወታቸዉን አጥተዋል። የጦር ኃይሉ ቃል አቀባይ ወታደሮች ከአስለቃሽ ጭስ ሌላ አልተኮሱም እያሉ ነዉ።

ይልማ ኃ/ሚካኤል

ተክሌ የኋላ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic