1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

"የአፍሪቃ ቀን" የ 59 ዓመታት ጉዞ ስኬቶችና ተግዳሮቶች

ሰኞ፣ ግንቦት 22 2014

ባለፈው ሳምንት የአፍሪካ ቀን ሲከበር የአኅጉሪቱ መሪዎች እና ፖለቲከኞች መልካም የተመኙባቸውን መልዕክቶች አስተላልፈዋል። ይኸ ቀን የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አአድ) በተመሠረተበት ግንቦት 25 በየዓመቱ ታስቦ ይውላል። የአኅጉሪቱ መሪዎች በመልካም ምኞት መግለጫቸው የሚያነሱትን አኅጉራዊ አንድነት በመፍጠር ረገድ ግን አልተሳካላቸውም።

https://p.dw.com/p/4C3EP
Äquatorialguinea AU Treffen in Malabo
ምስል AFP/Getty Images

ማህደረ ዜና፦ "የአፍሪቃ ቀን" የ 59 ዓመታት ጉዞ ስኬቶችና ተግዳሮቶች

የአሁኑ የአፍሪቃ ህብረት የቀድሞው የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት የተመሰረተበት 59ኛ ዓመት ባለፈው ግንቦት 25,2014 ዓ.ም አዲስ አበባ በሚገኘው የህብረቱ ዋና ጽ/ቤትና በአንዳንድ የአባል አገራቱ በተለያዩ መርሃግብሮች ተከብሯል:: በቅኝ አገዛዝ ስር የነበሩ የአፍሪቃ ሀገራትን ነጻ የማውጣት ዋና ዓላማን አንግቦ በ 32 ነጻ የአፍሪቃ ሃገራት የተመሰረተው ድርጅቱ ዛሬ 55 አገራትን በአባልነት አቅፏል:: ድርጅቱ ከምስረታው ጀምሮ እንደ ደቡብ አፍሪቃና ዚምባብዌ ያሉ በቅኝ ቅዛት ይማቅቁ የነበሩ ለነበሩ የአፍሪቃ ሃገራት ወታደራዊና የስልጠና ድጋፍ ሲሰጥ መቆየቱም የሚታወስ ነው:: እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ 1960 ዓ.ም በአህጉሪቱ 17 ተጨማሪ ሃገራት ከቅኝ አገዛዝ ነጻ መውጣታቸውን ተከትሎም ድሉ በየዓመቱ ግንቦት 25 "የአፍሪቃ የነጻነት ቀን" ተብሎ እንዲከበር ምክንያት ሆኗል:: አፍሪቃን በፖለቲካ በንግድና በምጣኔ ሃብት በማዋሃድ አንድ የተባበረ ሃገረ መንግስት የመመስረት ውጥንን ያለመው ህብረቱ ዛሬም ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ በጥቂት ስኬቶችና አያሌ ተግዳሮቶች ተከቦ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል:: 

አብዛኛዎቹ የአፍሪቃ ሃገራት ከምዕራባውያን ቅኝ አገዛዝ ነጻነታቸውን ከተቀዳጁ በኋላ በተለይም "ለአፍሪቃ ነጻነትና ክብር እንቆማለን" ባሉ ሁለት የተለያየ ሃሳብን በሚያቀነቅኑ ቡድኖች የእርስ በርስ ሽኩቻና ግጭት ሳቢያ አህጉሪቱ በተሻለ መልኩ ጥንካሬና አንድነቷን ጠብቃ ልትቆም አልቻለም:: እንደውም "አፍሪቃውያን በፖለቲካና ምጣኔ ሃብት ራሳቸውን ከመቻል ጀምሮ እስከ ኮንፌዴሬሽን አንድ ወደ መሆን ውህደት ሊያመሩ ይገባል" የሚል ዓላማን በሚያራምደው የጋናውን ኩዋሚ ኑኩሩማንና የጊኒውን ሴኩቱሬ የመሳሰሉ የነጻነት ታጋዮችን ያሳተፈው ስድስት ያህል አገራት በመሰረቱት የካዛብላንካ ቡድንና " አፍሪቃውያን ራሳቸውን ችለው ለመቆም ምጣኔ ሃብታቸውን ለማሳደግና ጠንካራ እንዲሆኑ ለማስቻል በሌሎች ያደጉ ሃገራት መደገፍ አለባቸው" የሚለውን ሃሳብ በሚያቀነቅነው አብዛኛዎቹ የፈረንሳኝ ቅኝ ተገዢ የነበሩ 22 የአፍሪቃ ሃገራትን ባካተተው የሞኖሮቪያው ቡድን መሃል የተፈጠረውን ቅራኔ አስወግዶ መላው አፍሪቃውያን ልዩነታቸን አስወግደው በጋራ የሚሰባሰቡበትንና ወደ ጠንካራ ውህደት የሚያመሩበትን አንድ ወጥ የሆነ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት በመመስረቱ ሂደት በአድዋው የጦርነት ድል ምክንያት በአፍሪቃውያንና መላው ጥቁር ሕዝቦች ዘንድ ከፍተኛ ክብር የተቀዳጀችው ኢትዮጵያ ያበረከተችው ሚና የላቀ መሆኑ በታሪክ ይጠቀሳል::

Flaggen African Union AU Südafrika CLOSE
ምስል picture alliance/landov

በ 1930 ዎቹ ዓ.ም ኢትዮጵያ የሊግ ኦፍ ኔሽንስ የወቅቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ብቸኛዋ አፍሪቃዊት አባል አገር እንድትሆን ትልቅ ሚና የተጫወቱት የኢትዮጵያው ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት የዛሬው የአፍሪቃ ህብረት እንዲመሰረት ከሃሳብ ጀምሮ እስከ ተግባራዊ ምስረታው ዕውን መሆን እንደ ጋናው ክዋሜ ንክሩማ የኬንያው የነፃነት ታጋይና አርበኛ ጆሞ ኬንያታ የጊኒው ሴኮ ቱሬ የሴኔጋሉ ሊኦፖልድ ሴዳር ሴንጎርና ሌሎችም የአፍሪቃ ቀደምት መሪዎች የነጻነት ታጋዮችና የፓን አፍሪቃኒዝም ፍልስፍና አቀንቃኞች ጋር በጋራ በመሆን ያበረከቱት አስተዋጽኦ ዛሬም ድረስ ሲወሳ የሚኖር ነው:: ግንቦት 15 ቀን 1955 ዓ.ም ዋናው የድርጅቱ ምስረታና የአፍሪቃ መሪዎች የመክፈቻ ጉባኤ አዲስ አበባ ውስጥ ሲካሄድ ንጉሰ ነገስቱ ባሰሙት ንግግር "የዚህ ታላቅ ጉባኤ መደረግና የመላው አፍሪቃ መሪዎች ተካፋይ መሆን ለዚህች ክፍለ ዓለማችን በውስጧም ለሚገኙ ሕዝቦቻችን ላለን ጥልቅ አሳቢነት ዓይነተኛ ምስክር ነው ተስፋና ራዕያችንንም በተግባር እናሳያለን" ሲሉ ድርጅቱ ለአፍሪቃ የሰነቀውን ተስፋና ዕድል ገልጸው ነበር::

Haile Selassie, ätiopischer Politiker und König
የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ኃይለስላሴ ግንቦት 15 ቀን 1955 ዓ.ም ዋናው የድርጅቱ ምስረታና የአፍሪቃ መሪዎች የመክፈቻ ጉባኤ አዲስ አበባ ውስጥ ሲካሄድ ባሰሙት ንግግር "የዚህ ታላቅ ጉባኤ መደረግና የመላው አፍሪቃ መሪዎች ተካፋይ መሆን ለዚህች ክፍለ ዓለማችን በውስጧም ለሚገኙ ሕዝቦቻችን ላለን ጥልቅ አሳቢነት ዓይነተኛ ምስክር ነው ተስፋና ራዕያችንንም በተግባር እናሳያለን" ሲሉ ድርጅቱ ለአፍሪቃ የሰነቀውን ተስፋና ዕድል ገልጸው ነበር። ምስል picture-alliance

"በዚህ በዛሬው ቀን ወደዚህ ዋና ከተማችን አዲስ አበባና ኢትዮጵያ የመጣችሁ የመላው የነፃ አፍሪቃ አገራት መሪዎች ወንድሞቻችንን በራሳችንና በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ስንቀበል በጣም ደስ ይለናል:: ይህ ዛሬ እኛ የአፍሪቃ ነፃ መንግሥታት መሪዎች የምናደርገው ጉባኤ በዓለም ላይ እስካሁን ድረስ ተወዳዳሪ የለውም:: የዚህን ታላቅ ጉባኤ መደረግና የመላው አፍሪቃ አገሮች መሪዎች ተካፋይ መሆን ለዚህች ክፍለ ዓለማችን በውስጧም ለሚገኙት ሕዝቦቻችን ላለን ጥልቅ አሳቢነታ ዓይነተኛ ምስክር ነው:: ባጭሩ ይህ ቀን ለአፍሪቃና ለአፍሪቃውያን በመላ ታሪካዊና ታላቅ ቀን ነው" ሲሉ ነበር ንጉሰ ነገስቱ ንግግራቸውን ያሰሙት::

የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ተቋም የአንድ ጎልማሳ እድሜ ካስቆጠረም በኋላ ለአፍሪቃውያን የሚፈልጉትን ስኬት ሰላምና ብልጽግና ካለማምጣቱም ሌላ በድርጅቱ መተዳደሪያ ቻርተር ላይ "በአገራት ሉዓላዊነት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም" የሚለው አንቀጽ አባል ሃገራቱ ተገቢ ያልሆነ ህገ ወጥ ተግባርን እንዲፈጽሙና በመካከላቸው የሚከሰቱ ግጭቶችንም ለማስቆም የሚያስችል አቅም እንዲያጣ  አድርጎት ቆይቷል:: አባል ሃገራቱ የሚጠበቅባቸውን ዓመታዊ መዋጮ መክፈል አለመቻላቸውም እንቅስቃሴዉን ይበልጥ እያዳከመው በመምጣቱ ደቡብ አፍሪቃ ደርባን በተካሄደ ጉባኤ ተቋሙ ይህን መሰረታዊ ችግር ገምግሞ በአህጉሩ የተሻለ የፖለቲካዊ የማህበራዊና የምጣኔ ሃብት እድገት ለማስመዝገብ አዲስ የጋራ ተቋም መገንባት መተኪያ የሌለው አማራጭ መሆኑን በማመን እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር ሀምሌ 2 ቀን 1995 ዓ.ም የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪቃ ህብረትነት ሊቀየር ችሏል:: ጉባኤው የደቡብ አፍሪቃውን የቀድሞ ፕሬዝዳንት ታቦ ምቤኪን የመጀመሪያው የህብረቱ ሊቀመንበር አድርጎ መሰየሙም የሚታወስ ነው:: ከ 59 ዓመታት በፊት የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ምስረታ ዕውን ከሆነ በኋላ በየዓመቱ ሲያከብረው የቆየውን "የአፍሪቃ የነጻነት ቀን" ከህብረቱ ዳግም ምስረታ ጊዜ ጀምሮ "የአፍሪቃ ቀን" በሚል ተክቶት ላለፉት 20 ዓመታት ህብረቱ በልዩ ልዩ መርሃ-ግብሮች እያከበረው ይገኛል:: ዘንድሮም ዓመታዊ የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከግንቦት 25 እስከ 28, 2014 ዓ.ም በኢኳቶሪያል ጊኒ ማላቦ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ በሁለት ዋና ዋና መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር አካሂዶ ውሳኔ አስተላልፏል:: አንዱ የመከረበት ጉዳይ በአህጉሩ ስላለው የሰብዓዊ ጉዳይ ተግዳሮቶች ስለ ሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት ተደራሽነትና ስለ ግጭት አፈታት ሰላምና ልማት ሲሆን ሌላው ጽንፈንነትንና ሽብርተንነትን በመዋጋት እንዲሁም በአፍሪቃ አህጉር እየተባባሰ በመጣው ህገመንግስትን የሚጻረር የመንግሥት ለውጥ ወይም መፈንቅለ መንግሥት አሳሳቢነት ጉዳይ በቀረቡ ሪፖርቶችና መፍትሄዎች ዙሪያ ተወያይቷል:: በደቡብ አፍሪቃ የዩኒቨርሲቲ መምህር ተመራማሪና የፓን አፍሪቃኒዝም ፍልስፍና አቀንቃኝ የሆኑት ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ ዛሬ 55 ያህል አባል ሃገራትን ያቀፈው የአፍሪቃ ህብረት ከምስረታው ጀምሮ ውህደቱ እንዳይጠናከር የሚያደርጉ አያሌ ተግዳሮቶች ተጋርጠውበት እንደቆዩ በመግለጽ ዓመታዊው "የአፍሪቃ ቀን" እንኳ እንደ ጋና ናሚቢያ ዚምባብዌ ላይቤሪያ ማሊና ዛምቢያን ከመሳሰሉ ከ 12 ከማይበልጡ ሃገራት ውጪ በሌሎች አለመከበሩ የድርጅቱን ጥንካሬ ማነስ አመላካች ነው ሲሉ ያለፉትን 59 ዓመታት የተቋሙን የጉዞ ሂደት በመገምገም ለዶይቼ ቨለ "DW" ገልጸዋል::

"አውሮጳውያን ቅኝ ገዢዎች አፍሪቃን ለቀው በሚወጡበት ወቅት በተለይም ፈረንሳይ በቅኝ ግዛት ይዛ የቆየቻቸው አገሮች ከ እነሱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲቀጥሉ የሚያስችላቸውን ዘዴ ዘርግተው በመሆኑ ዛሬም ከእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝና ብዝበዛ አልተላቀቁም:: እነዚህ አገራት ገንዘባቸውን ጭምር በፈረንሳዩ ማዕከላዊ ባንክ እንዲያስቀምጡ አስገዳጅ ስምምነት በመፈረማቸው ዛሬም ከነጻነት በኋላ የገዛ ገንዘባቸውን ከባንኩ ማውጣት ሲፈልጉም ፈረንሳይ በቅኝ ግዛት ዘመን በአገራቱ ላከናወነቻቸው የልማት እንስቃሴዎች በሚል የቅኝ ግዛት ግብር እየከፈሉ ይገኛሉ:: ከዚህ ሌላ መላው የአፍሪቃ አገራትን በአንድነት የሚያስተባብረው የአፍሪቃ ህብረት እያለ ከዚህ ተቋም ውጪ የተመሰረቱት እንደ ኢኮዋስ ሳድክ ማግሬብ ኢጋድና የመሳሰሉት ቀጠናዊ ትብብሮች የህብረቱን አቅም እያዳከሙትና ክፍፍልን እያሰፉ መሆናቸውን እያየን ነው:: ምዕራባውያን በበርካታ የአፍሪቃ አገራት እየገነቧቸው የሚገኙት የጦር ካምፖችም በሃገራት መካከል ያለውን ትብብር እንዲዳከም የሚያደርጉ በመሆናቸው አገራቱ እስከ 2063 ዓ.ም የዘረጉትን የውህደት አጀንዳቸውን ቆም ብለው በማጤን የውጭ ኃይላት ውድድር በመፍጠር አንጡራ ኃብታችንን ለመቀራመት በኃይማኖትና ብሔር ልዩነት እየከፋፈሉ ብዝበዛ ለማካሄድ የዘረጉትን ሥውር የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ መረብ በመበጣጠስ ከሌላው ዓለም በተሻለ በአህጉሩ የሚገኘውን ብዛት ያለው የሰው ኃይልና ዕምቅ የተፈጥሮ ሃብት በማቀናጀት ልማትና እድገትን በማፋጠን ከምዕራባውያን ተጽዕኖ እርዳታና ጥገኝነት የሚላቀቁበትን መላ ዛሬውኑ ሊዘይዱ ይገባል" ሲሉ አብራርተዋል::

የአፍሪቃ ህብረት ከምስረታው ጀምሮ በምዕራባውያን አገዛዝ ስር የሚገኙ ቀሪ የአፍሪቃ ሃገራትን ከቅኝ ተገዢነት  ነጻ ማውጣት ብቻ ሳይሆን ከድርጅቱ ዓበይት ዓላማዎች መካከል በአህጉሩ ሰላምና ደህንነትን እንዲሁም ዴሞክራሲ የፖለቲካ መረጋጋትንና መልካም አስተዳደርን ማስፈን ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር ማድረግ ከብድርና ከውጭ ጥገኝነት መላቀቅ ፈጣን የምጣኔ ኃብት እድገትን ማምጣት በተጨማሪም ዓለማቀፍ ተሰሚነትን ማረጋገጥ ዋና ተግባሩ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቢቆይም ገለልተኛ መርህ ከመከተል ይልቅ አህጉሩ ዛሬም ከብድርና እርዳታ ሊላቀቅ ባለመቻሉ ላለፉት ስድስት አስርተ ዓመታት ለምዕራባውያን ርዕዮተ ዓለምና ተጽዕኖ ከፍተኛ ተጋላጭ ሆኖ መቆየቱ ለተለያዩ ተግዳሮቶች እንዳጋለጠው ይታመናል::

Äthiopien Afrikanische Union Addis Ababa
ምስል Eduardo Soteras/Getty Images/AFP

የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ምስረታ ዕውን ሲሆን በ 1950ዎቹ ዓ.ም 228 ሚልዮን ያህል የነበረው የአፍሪቃ ሕዝብ ብዛት ዛሬ ከአምስት እጥፍ በላይ ጨምሮ ከ 1 ቢልዮን 400 ሚልዮን ልቋል:: የእርስ በእርስ ግጭቶችና ጦርነቶች አሸባሪዎችና ጽንፈኞች የሚፈጥሯቸው ቀውሶች ድህነት ኋላቀርነት ስደት የሕዝቦች መፈናቀል ሙስና ብልሹ የመንግስት አስተዳደርና መፈንቅለ መንግሥት በምግብ እራስን አለመቻልና የውጭ እርዳታ ጥገኝነት የአየር ጸባይ ለውጥ ተደጋጋሚ ድርቅና የረሃብ ክስተት የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች እነዚህ ሁሉ ተግዳሮቶች አህጉሪቱ አሁንም ወደ ውህደትን የምታደርገውን ጉዞ አስቸጋሪ ያደረገው ሲሆን ውስጣዊና ውጫዊ በሆኑ ውስብስብ ፖለቲካዊና የምጣኔ ኃብት ቀውሶች ተተብትባ እንድትቆይ አድርጓታል፡፡ አምና 69 ቢልዮን ያልተከፈለ ዕዳ ይዛ ወደ አዲሱ የአውሮጳውያን ዓመት የተሸጋገረችው አፍሪቃ እስከ 2024 ዓ.ም መከፈል ያለበት ሌላ ተጨማሪ 185 ቢልዮን ዶላር ዕዳ ተሸክማ አበዳሪዎቿን የምዕራባውያን ሃገራትና ተቋማት እየተማጸነች ትገኛለች:: እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ 2019 ዓ.ም በአፍሪቃ ከ 25 በላይ በሚሆኑ ሃገራት የእርስ በእርስ ግጭቶች መቀስቀሳቸውንና ከእነዚህም ውስጥ 13ቱ የድንበር ውዝግቦች መሆናቸውን ጥናቶች ሲጠቁሙ ግሎባል ሲትዝን ይፋ ባደረገው መረጃ ዛሬ ላይ በመላው አፍሪቃ ከ 32 ሚልዮን የሚልቁ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው በግጭት ሳቢያ በግዳጅ የተፈናቀሉ ሲሆን በስደትና በሌሎች የጎረቤት ሃገራት በጥገኝነት ይገኛሉ:: ከ 50 በመቶ የሚልቀው መፈናቀል የተከሰተው እንደ ኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሶማሊያ ሱዳን ደቡብ ሱዳን ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ማሊ ኒጀር ቡርኪናፋሶ ናይጄሪያ ሞዛምቢክ ሊቢያና ካሜሩንን በመሳሰሉ ሃገራት እንደሆነም ታውቋል::አኮርድ አፍሪቃም በአንድ ጥናቱ በተዳከመ ምጣኔ ኃብት በድህነት በሚዳክረው የአፍሪቃ አህጉር እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር ከ 1952 ዓ.ም ጀምሮ ከ 200 በላይ መፈንቅለ መንግስት መካሄዳቸው ጠቅሶ ከእነዚህም መካከል ከ 100 የሚልቁት የተሳኩ እንደነበር አመልክቷል:: ባለፉት 22 ወራት ጊዜ ውስጥ እንኳ በማሊ ቡርኪናፋሶ ቻድ ጊኒ ቢሳውና ሱዳንን በመሳሰሉ ሀገራት ከስድስት ያላነሱ መፈንቅለ መንግስት ተካሂደዋል::በምስራቅ አፍሪቃ በሳህል ቀጣናና በሌሎችም የምዕራብና የሰሜን የአህጉሪቱ ክፍሎች በውጭ ኃይላት ድጋፍ እየተዘወሩ ያሉት የሽብርተኞችና የጽንፈኛ ኃይላት ጥቃቶችም በሃገራት ላይ እጅግ ከፍተኛ የሰብዓዊና የምጣኔ ሃብት ቀውስን እያስከተሉ ይገኛሉ:: 

ግንቦት 25 ዓመታዊውን የአፍሪቃ ቀን የተወሰኑ የህብረቱ አባል ሃገራት ትኩረት ቢሰጡትም እንደ ደቡብ አፍሪቃ ባሉ የህብረቱ መስራች አገራት ግን " አፍሪቃ ዛሬም ከምዕራባውያን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ አልተላቀቀችም" የሚሉ የትግል ድምጾች የተንጸባረቁባቸው ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰልፎችን አስተናግደዋል:: በጁሊየስ ማሌማ የሚመራው የደቡብ አፍሪቃው የምጣኔ ኃብት ነጻነት ታጋዮች የግራ አክራሪ ፓርቲ /ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ ፓርቲ/ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች በተለይም ፕሪቶሪያ ከተማ በሚገኘው የፈረንሳይ ኤምባሲ ፊትለፊት ተሰባስበው "ፈረንሳይ አፍሪቃን ለቃ በአስቸኳይ ትውጣ" የሚሉ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዟን አሁንም አጠናክራ ቀጥላለች ባሉዋት ፈረንሳይ ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል::

"ዛሬ የአፍሪቃ ቀን እየተከበረ ነው:: መላው አፍሪቃ በቅኝ ቅዛት ስር ወድቃ መቆየቷና ኢትዮጵያ ብቻ ነጻነቷን አስከብራ የኖረች አገር መሆኗን እናውቃለን:: ሆኖም ፈረንሳይ በወንጀል የጎደፉ እጆቿን ዛሬም ከቀደሙት የምዕራብ አፍሪቃ የቅኝ ግዛት ሀገሮቿ ልታነሳ አልቻለችም:: እናም በዛሬው የአፍሪቃ ቀን በዓል ፈረንሳይ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዟ እንዲያበቃና አፍሪቃን ለቃ እንድትወጣ ለመጠየቅ ነው የተቃውሞ ሰልፉን ያካሄድነው"

Mali | Militär | FAMA | Armed forces
ምስል Souleymane Ag Anara/AFP

አፍሪቃ ከሌሎች ዓለማት በተለይ ተዝቆ የማያልቅ እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት ብትሆንም ከውጭ እርዳታና ጥገኝነት ለመላቀቅ ባለመቿላ ዛሬም የአፍሪቃ ህብረት በምዕራባውያን ተጽዕኖ ስር እንደወደቀ መሆኑ ይነገራል:: ጽንፈኝነትና ሽብርተኝነት የእርስ በእርስ ግጭትና ጦርነት በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ወደ ስልጣን የመጡ መንግሥታትን በወታደራዊ ኃይል የመለወጥ እንቅስቃሴ መጠናከር አምባገነናዊ የሆነ ሙሰኛና ብልሹ አስተዳደር መንሰራፋት የውጭ ኃይላት ግጭቶችን በተለያየ መንገድ በመቀስቀስ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ስም ወታደሮቻቸው አስፍረው የሃገራትን የተፈጠሮ ሃብት የሚቀራመቱበት ስልታዊ ዘዴና ስፍር ቁጥር የሌለው ወታደራዊ የጦር ጣቢያዎችን በአፍሪቃ እየገነቡ ያለው ሂደት  አምባገነን  የአፍሪቃ  መንግሥታትም በውጭ ድጋፍ እየታገዙ የውክልና ጦርነት በጎረቤቶቻቸው ላይ የሚከፍቱበት መንገድ ከአህጉራዊ ውህደት ይልቅ ቅራኔን የሚያሰፋ መሆኑ ሲጠቀስ ድህነትና የእዳ ጫናም የአፍሪቃ ህብረት ግቦቹን እውን እንዳያደርግ ከጋረጡበት እንቅፋቶች ጥቂቶቹ ናቸው የሚሉት ፕሮፌሰር ማሞ ዛሬም ችግሮቹ ተባብሰው መቀጠላቸውን ተናግረዋል::

የአፍሪቃ ህብረት የአውሮጳ ህብረትን ልምድ በመቅሰም በአፍሪቃ ፖለቲካዊ ውህደትን ለመፍጠር የተወጠነው ዕቅድ በአባል ሃገራቱ መካከል የተመጣጠነና የተረጋጋ ምጣኔ ኃብት በሌለበት ሁኔታ አዳጋች መሆኑን ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡ ያም ቢሆን በጀመረው ተቋማዊ ለውጥ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የዘለቀ የተዋሃደ አንድ የአፍሪቃ ማህበረሰብን የመፍጠር ራዕዩን ዕውን ለማድረግ እንደ የአፍሪቃ ነጻ የንግድ ትብብር መርሃግብርን የመሳሰሉ የማህበረሰቡን ቁርኝትና የምጣኔ ሃብት እድገትን ሊፈጥሩ የሚችሉ ዕቅዶቹን ገቢራዊ አድርጓል:: የአፍሪቃ ጉዳዮች ተንታኝና የፓን አፍሪቃኒዝም አቀንቃኙ ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ 55 የአፍሪቃ ሃገራትን የሚያስተባብረው ህብረቱ እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር እስከ 2063 ዓ.ም ዕውን አደርገዋለሁ ብሎ የነደፈውን አጀንዳ ተግባራዊ ለማድረግና የበለጸገች አፍሪቃን ለመገንባት መሪዎች ለለውጥ ከሚኖራቸው ቁርጠኝነት ባሻገር አገራት ዘርፈ ብዙ የትብብር ግንኙነቶችን መፍጠር ይኖርባቸዋል የሚል ምክረሃሳብ አላቸው::

እንዳልካቸው ፈቃደ

እሸቴ በቀለ