የአፍሪቃ ቀንድ የሰላም ይዞታ | የጋዜጦች አምድ | DW | 25.07.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የአፍሪቃ ቀንድ የሰላም ይዞታ

መንግስት አልባዋና ለረጅም ዓመታት በእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ የከረመችዉ ሶማሊያ ሰሞኑን የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ስባለች።

የተቃዉሞ ሰልፍ በሶማሊያ

የተቃዉሞ ሰልፍ በሶማሊያ

በርካታ የዜና አዉታሮች የኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች ከአቅመ ደካማነቱ የተነሳ የገዛ አገሩን ግዛቶች መቆጣጠር የተሳነዉን የሶማሊያን የሽግግር መንግስት ለመደገፍ ባይደዋ ገብተዋል ይላሉ።

የኢትዮጵያ መንግስት ቃል አቀባይ ባለፈዉ ሳምንት ለነዚሁ የዜና አዉታሮች እንደገለፁት ደካማዉን የሶማሊያ የሽግግር መንግስት የእስላማዊዉ ሸንጎ ሚሊሺያዎች የሚተናኮሉ ከሆነ የተባለዉ እንደሚሆን ተናግረዋል።
እስላማዊዉ ሸንጎ ዓርብ ዕለትም ሆነ ትናንት ደጋፊዎቹን አስተባብሮ በመቋዲሾ ባካሄደዉ ሰልፍ የኢትዮጵያ ወታደሮችን ባይደዋም ሆነ ተጎራባች ከተሞች መግባት አዉግዟል፤ እዋጋቸዋለሁም ብሏል።
ይህ ሁኔታ በአፍሪካ ቀንድ ምን ያስከትላል? በናይሮቢ የዓለም ዓቀፍ የግጭት ታዛቢ ቡድን የአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ተንታኝ የሆኑት ማድ ብሪዳን ማብራሪያ ሰጥተዋል ።

ለአፍሪቃ ቀንድ ጉዳይ ተንታኝ ማድ ብሪዳን በመጀመሪያ የቀረበላቸዉ ጥያቄ በአሁኑ ጊዜ የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት የሳበዉ የሶማሊያ ሁኔታ ምን ያህል አስጊ ነዉ የሚል ነበር፤ እሳቸዉም ሲመልሱ

«ሁኔታዉ በጣም አደገኛ ነዉ። ባለፉት በርካታ ሳምንታት ደግሞ በጣም እየተባባሰ ነዉ የሄደዉ። የኢትዮጵያ ወታደሮቿን ወደሶማሊያ ምድር ማንቀሳቀስ ደግሞ ከፍተኛ ፍጥጫ እንደሚያስከትል ይገመታል።» ብለዋል።

በሁለቱ ተጎራባች ሀገራት መካከል የቆየ ቁርሾ ቢጤ ዉጥረት መኖሩ ይነገራል። የኢትዮጵያ ወታደሮች ሶማሊያ ገብተዋል መባሉ ደግሞ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ዓይነት ነዉ የሆነዉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በፍጥጫዉ የትኞቹ ግንባሮች ናቸዉ በዋናነት ሊጠቀሱ የሚችሉት?
«ግንባሮቹ ያዉ የሶማሊያ የሽግግር መንግስትና ደጋፊዎቹ በአንድ ወገን መቋዲሾን የያዘዉ የእስላማዊ ሸንጎ ደግሞ በሌላ ወገን ናቸዉ። ሆኖም የኢትዮጵያና የሌሎች ቡድኖች ጣልቃ ገብነት ለሸንጎዉ ጣልቃ ገብነቱን በሚቃወሙ ወገኖች ዘንድ ድጋፍ ያስገኝለታል።»

ግን እኮ የሽግግር መንግስቱም ሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ወታደሮቹ አልገቡም ብለዉ አስተባብለዋል።

«በርካታ የታማኝና የአይን ምስክሮች መረጃና ዘገባ አለ። ይህ ደግሞ በዲፕሎማቶችና በደህንነት ምንጮች ተረጋግጧል። አሁን ጥያቄዉ የኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች ሶማሊያ አሉ ወይ አይደለም። ጥያቄዉ ስንት ናቸዉ ምንስ ሊያደርጉ ነዉ የፈለጉት የሚለዉ ነዉ። ማስተባበሉ በሁለት ምክንያቶች ይሆናል፣ አንደኛዉ በቴክኒክ ደረጃ የተባበሩት መንግስታት የጣለዉን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ መጣስ ነዉ በተጨማሪም የሽግግር መንግስቱ ህጋዊነት አነጋጋሪ ይሆናልና ነዉ።»

ለመሆኑ በዚህ ዉጥንቅጥ መካከል የሶማሌ ህዝብ ማንን ነዉ ያመነዉ? የሽግግር መንግስቱን ወይስ የእስላማዊዉን ሸንጎ?

«የሚያሳዝነዉ ነገር አብዛኛዎቹ ሶማሌዎች የሚደግፉት የለም ብዬ አስባለሁ። ሁለቱም ወገኖች ቢሆኑ የሶማሌዎችን ማዕከላዊ ጉዳይ የሚወክሉ አይደሉም። እስላማዊዉ ሸንጎ ሳይመረጥ በኃይል ነዉ መቋዲሾ የከተመዉ። ምንም እንኳን በርካታ ሰዎች በጎሳ በጣጥቀዉ ምንም ሳያደርጉላቸዉ የከረሙትን የጦር አበጋዞች በማሳደዳቸዉ ተቀብለዋቸዋል ቢባልም ገና የመምራትም ሆነ መቋዲሾ የሚገኙትን ሰዎችና ጎሳዎች ወክለዉ የመናገር መብት አላገኙም። በሌላ በኩል የፌደራል የሽግግር መንግስቱ ወዲያዉ ነዉ ተቀባይነቱን ያጣዉ ከመነሻዉም ስር የሰደደ አልነበረም። በአብዛኛዉቹ ሶማሌዎች የራሱን አጀንዳና የቅርብ አጋሮቹን ከመወከል ያለፈ እንዳልሆነ ነዉ የሚታየዉ። እናም አብዛኛዉ ሶማሌዎች ከማንም ሳይሆኑ መሃል ላይ ነዉ የሚገኙት።»

ይህ እንዲህ ከሆነ በሚቀጥለዉ ሳምንት ይካሄዳል የተባለ የሰላም ድርድር አለ። ግጭት መኖሩ በተጠቀሰዉ የሰላም ድርድሩን ወደኋላ ይመልሰዋል ብለዉ ይገምታሉ? በምል ለቀረባላቸዉ የአፍሪቃ ቀንድ ጉዳይ ተንታኙ ይህን ምላሽ ነዉ የሰጡት።

«የሰላም ሂደቱ በጣም ከባድ ችግር ላይ ነዉ። ምክንያቱም እስላማዊዉ ሸንጎ ወደካርቱም የላከዉን ተደራዳሪ ልዑክ መልሷል ወይም ሊመልስ እያስፈራራ ነዉ። የኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች ከሶማሊያ ካልወጡም ከሽግግር መንግስቱ ጋር አልነጋገርም ብሏል። መንግስትም ቢሆን ከሸንጎዉ ጋር ለመነጋገር ቸልተኝነት አሳይቷል። ከመነሻዉ ፕሬዝደንቱ ልዑካን መላክ አልፈለጉም ነበር ፓርላማዉ ስለተቃወማቸዉ ነዉ። የሰላም ድርድሩ ቢካሄድም እንኳን በእነዚህ ሁለት ወገኖች መካከል እርቅ የመምጣት እድሉ በጣም ጠባብ ነዉ። እኛ በእርግጥ እንዲሆን የምንፈልገዉ የሰላም ዉይይቱ ተካሄደም አልተካሄደ የሽግግር መንግስቱ በህገመንግስት የተደገፈ አገር አቀር የህብረት መንግስት እንዲሆንና፤ እስላማዊዉ ሸንጎም ከመቋዲሾ የሚወክላቸዉን ሰዎች ከግምት በማስገባት በመንግስት ዉስጥ መብት እንዲኖረዉ ነዉ። አለበለዚያ ግን እነዚህ እጅግ ተፃራሪ ፍላጎት ያላቸዉ ሁለት በጣም ፅንፈኛ ቡድኖች ዉይይት ማድረጋቸዉ የሚያመጣዉ ነገር አለ የሚል ተስፋ አይታየኝም።»

ዜናዉ በተደጋሚ መነገር ከጀመረ በመሰንበቱ ዓለም ዓቀፉ ማህበሰብ አልሰማም ሊባል አይችልም። አቋሙ ግን ግልፅ አልወጣም። እናም አዉሮፓና አሜሪካስ ግጭቱ ያሳሰባቸዉ አይመስሉም እንዴት ነዉ ነገሩ?

«እንደሚመስለኝ በመጀመሪያ አዉሮፓዉያን በርካታ ገንዘብ በማፍሰስ የሽግግር መንግስቱን የሚደግፉ ናቸዉ። ይህ መንግስት ባጠቃላይ ወጪዉን በዉጪ እርዳታ መሸፈኑ ይታወቃል። ሶማሌዎች ደግሞ ይህ መንግስት በጣም ደካማና ሁሉንም የማይወክል መሆኑን ስለተረዱ ይወድቃል ብለዉ ያምናሉ። አሜሪካዉያኑም በተለየ ምክንያት ከእስላማዊዉ ሸንጎ ጋር መተባበር አይፈልጉም። ምክንያቱም በእስላማዊዉ ሸንጎ ስርዓት ዉስጥ ጂሃድ መኖሩ፤ አንዳንድ አባላቱም ከአልቃይዳ ጋር ባላቸዉ ግንኙነት የአልቃይዳን አባላት ሶማሊያ ዉስጥ ሰዉረዋል የሚል እምነት አሜሪካ አላት።»

የሆነዉ ሆነና አሁን ጦርነት ይነሳል ብለዉ ይገምታሉ?
«ከፍተኛ የጦርነት አደጋ ይኖራል ብዬ አስባለሁ። እስላማዊዉ ቡድን በሶማሊያ ምድር በሚገኙ የኢትዮጵያ ኃይሎች ላይ ጅሃድ አዉጇል። ወታደራዊዉ እንቅስቃሴ ካለ ሁኔታዉ ይስፋፋል የሚል ስጋት አለ።»