የአፍሪቃ ቀንድ፣ ነዳጅ ሃብትና የተጠናከረ ፍለጋው | ኤኮኖሚ | DW | 07.03.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአፍሪቃ ቀንድ፣ ነዳጅ ሃብትና የተጠናከረ ፍለጋው

በዓለም ላይ እየጠናከረ የመጣው የኤነርጂ ፍጆት ብርቱ የዋጋ መናርን ከማስከተሉም ባሻገር ነዳጅ ዘይትና ጋዝን የመሳሰለ የተፈጥሮ ጸጋ በሚገኝባቸው አካባቢዎች ሃብቱን ከከርሰ-ምድር አውጥቶ ለመጠቀም በዓለምአቀፍ ኩባንያዎች መካከል የተያዘው ፉክክር ከመቼውም በላይ እያየለ እንዲሄድ አድርጓል።

ሰላም የራቃት ሶማሊያ

ሰላም የራቃት ሶማሊያ

ዛሬ በተለይም በአፍሪቃ ነዳጅ ዘይትና ሌሎች የተፈጥሮ ጸጋዎችን ለማግኘት በቻይናና በምዕራቡ ዓለም ኩባንያዎች መካከል የሚደረገው እሽቅድድም እጅግ የጠነከረ ነው። ገና ያልተነካ የነዳጅ ዘይት ሃብት አላቸው ከሚባሉት አገሮች መካከል ከ 15 ዓመታት በላይ ዕርጋታ ተለይቷት የኖረችው ሶማሊያም ትገኝበታለች። ከፕሬዚደንት ሢያድ ባሬ ውድቀት ወዲህ ከ 15 ዓመታት በላይ ሥርዓተ-ዓልባ ሆና የቀጠለችው ሶማሊያ መንግሥታዊ ሉዓላዊነቷን መልሳ የማግኘቷ ተሥፋ አሁንም ጨልሞ እንደቀጠለ ነው። በዋና ከተማይቱ ሞቃዲሾ የሻሪያው ፍርድቤቶች ሕብረት ተባሮ የሽግግሩ መንግሥት በቦታው ቢተካም ሰላም ሊወርድ ቀርቶ የብሄራዊ ዕርቅ ጉባዔ እንኳ ሊካሄድ አልቻለም። የሶማሊያ ሃቅ ዛሬም እንደ ትናንቱ ይህን የመሰለ ነው። በሞቃዲሾ የዓማጺያን የሮኬትና የሞርታር ጥቃት ዕለታዊ ነገር ሆኗል፤ የአገሪቱ የሕንድ ውቂያኖስ ጠረፍ የመርከብ መንገዶችም የባሕር ዘራፊዎች የነገሱባቸው ናቸው።

ታዲያ በዚህ ሁኔታ ገና ያልተነካውን የአገሪቱን የነዳጅ ዘይትና የጋዝ ሃብት ለማግኘት ደፍሮ ገንዘቡን የሚያፈስ የውጭ ኩባንያ ይገኛል ወይ? ከጥቂት ዓመታት በፊት ቢሆን ኖር መልሱ የለም፤ አይገኝም ነበር የሚሆነው። ነገር ግን ጊዜው ተለውጧል። ባለፉት ዓመታት የነዳጅ ዘይት ዋጋ መናር ሳቢያ ከዚህ ቀደም ባልነበረ መጠን ትርፍ ያጋበሱት ምዕራባውያን ኩባንያዎች ቻይናን ከመሳሰሉት የኤነርጂ ጥማቸው ከፍተኛ ከሆነ አገሮች በኩል በተፈጠረባችው ፉክክር፤ እንዲሁም በላቲን አሜሪካና በሩሢያ የኤነርጂ ብሄረተኝነት ባስከተለው ስጋት የተነሣ ዓይናቸውን በምሥራቅ አፍሪቃ ላይ አሳርፈዋል። ፍላጎታቸው እንዳሁን የጠነከረበት ጊዜ ጨርሶ አይታወስም።

ሶማሊያን ከወሰድን ከታላላቅ ምዕራባውያን ኩባንያዎች እስከ ትናንሽ ነዳጅ ዘይት አውጪዎች ብዙዎች በአገሪቱ ላይ ዓይናቸውን ማሳረፍ የጀመሩት ገና አሁን አይደለም። ቼቭሮንን፣ ቶታልንና ኮኖኮ-ፊሊፕስን የመሳሰሉት ታላላቅ ኩባንያዎች እንዲያውም የነዳጅ ዘይት ፍለጋ ውል ያደረጉት አገሪቱ እ.ጎ.አ. በዘጠናኛዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ለዛሬው ቀውስ ከዳረጋት የእርስበርስ ጦርነት ላይ ከመውደቋ በፊት ነበር። የዓለም ባንክ በጊዜው በሥምንት የሰሜን-ምሥራቅ አፍሪቃ አገሮች ላይ ባካሄደው ጥናት በነዳጅ ዘይት ሃብት ሶማሊያን በዋና የንግድ አምራችነት አቅም ከሱዳን ቀጥሎ በሁለተኛ ስፍራ ነበር ያስቀመጠው።

የከርሰ-ምድር ምርምር ጠበብት እንደሚያመለክቱት ሰሜናዊው ሶማሊያ የአደንን ባሕረ-ሰላጤ አቋርጦ እስከ ደቡብ በሚዘልቀው የነዳጅ ዘይት ሃብት ክልል ውስጥ ነው የሚገኘው። ነዳጅ ሃብት ፈላጊዎችም በዚሁ የጠበብት መረጃ በመደፋፈር አራት ቢሊዮን በርሚል ጥሬ ዘይት ክምችት እንዳለበት በሚነገርለት አካባቢ ከየመን በታች በማሪብ ሃጃርና ሣዩን-አል-ማሢላ ተቀጥላ ተቀማጭ ለማግኘት ተሥፋ መጣላቸውም አልቀረም። ሆኖም ዓመታት ያስቆጠረው በጦር አበጋዞች መቀናቀን የተከተለ ደም መፋሰስ ዕቅዱን አንቆ ይዞት ቆይቷል።

ግን አሁን እንደገና የሶማሊያ ሽግግር መንግሥት ነዳጅ ፍለጋው እንዲጠናከር ለማድረግ እየጣረ ነው። የሽግግሩ አስተዳደር አፈ-ቀላጤ አብዲራህማን ዲናሪ ሰሞኑን አገሪቱ ብዙ ነዳጅ ዘይት እንዳላት በማመልከት መንግሥት የነዳጅ ማውጣት ፈቃድ የሚሰጥበትን ሁኔታ የሚደነግግ ቁልፍ ሕግ ማጽደቁን አስታውቀዋል። ዲናሪ አሁን በወቅቱ በመጀመሪያ ጸጥታን መልሶ ለማስፈንና ለመልሶ-ግንባታው ዓለምአቀፍ ድጋፍ ማስፈለጉንም ሳይጠቅሱ አላለፉም። በዲናሪ አባባል ፈቃድ በመስጠቱ ረገድ ማን ረዳ፤ ማን ሳይረዳ ቀረ ወደፊት ወሣኝነት ሊኖረው ነው።

ለማንኛውም ታላላቁ ምዕራባውያን የአሜሪካ ኩባንያዎች ለጊዜው ዳር ቆመው ሁኔታውን በመመልከት ወይም በማቅማማት ላይ ናቸው። ግን በዚህ ለረጅም ጊዜ የሚገፉበት አይመስልም። ኩባንያዎቹ እያንዳንዳቸው ባለፉት ጊዜያት የነዳጅ ዋጋ መናር ሳቢያ በብዙ መቶ ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ትርፍ ሲያገኙ ለኢስ ፍለጋ የሚያፈሱት በቂ ገንዘብ አላቸው። በሌላ በኩል በአመራረት ውላቸው ላይ ጥብቅ አቋም እየያዙ በመጡት በቬኔዙዌላ፣ ኤኩዋዶር፣ ቦሊቪያና ሩሢያ መሰናክል እየገጠማችውም ነው። ይህ የኋለኛው ምክንያት ደግሞ ይበልጥ በአፍሪቃ ላይ እንዲየኩሩ አድርጓቸዋል። ምንም እንኳ በናይጄሪያ የነዳጅ ዘይት አካባቢ ዓመጽ ቢያይልና በአልጄሪያ የምርት ቀረጥ ቢጨመርባቸውም!

እርግጥ በአፍሪቃ ነዳጅ ዘይት ሃብት ላይ ያለው ጉጉት በቻይና፣ በሕንድና በማሌይዚያ ኩባንያዎች ዘንድ ያመዝናል። እነዚሁ ኩባንያዎች በጸጥታው ሁኔታ አሳሳቢነት የምዕራባውያኑን ያህል ሳይጨነቁ ብዙ ገንዘብ ለማውጣትና የቴክኖሎጂ ጥበብን በሥራ ለማዋል ዝግጁ ናቸው። በዓለም ላይ በነዳጅ ዘይት ፍጆቷ ከአሜሪካ ቀጥላ ሁለተኛዋ የሆነችው ቻይና ከአሁኑ ከአንጎላ እስከ ሱዳን በነዳጅ ዘይት ማውጣት ፕሮዤዎች ተሰማርታ ትገናለች። ከዚህም ባሻገር በሰሜናዊው ሶማሊያና በኢትዮጵያ የኢጋዴን አካካቢ ላይ ዓይኗን ማሳረፏ አልቀረም።

ዛሬ ታላላቆቹ የቻይና ኩባንያዎች የተሟላ ቴክኖሎጂና አስፈላጊው ዕውቀት ስላላቸው የምዕራባውያኑን ትብብር የሚፈልጉበት ጊዜ አልፏል። ሆኖም አነስተኛና በተፋጥነ ሁኔታ እየተራመዱ የሚሄዱ ኩባንያዎች አስቸጋሪ በሆነው በምሥራቅ አፍሪቃ ግንባር ድርሻ ለማግኘት፤ ለዚያውም የኢንሹራንስ ጥበቃ ሳይኖራቸው ለመሥራት ዝግጁ ናቸው። የአውስትራሊያው Woodside Petroleum በኬንያ ጠረፍ አኳያ ይቆፍራል፤ የደቡብ አፍሪቃ Ophir Energy በታንዛኒያና፤ የስዊድን Lundin Petroleum ደግሞ በኢትዮጵያ በኤነርጂ ፍለጋ ተግባር ተሰማርተዋል።

ሌሎች ኩባንያዎችም ሶማሊያ ውስጥ ሣይቀር በነዳጅ ፍለጋ ተግባር መሰማራት እንደሚቻል እያረጋገጡ ነው። አንድ የአውስትራሊያ ኩባንያ በ 2005 በከፊል ራስ-ገዝ በሆነችው ፑንትላንድ በመላው የግዛቲቱ ንጥረ-ነገርና ነዳጅ ዘይት ሃብት ላይ ሰፊ ድርሻ የሚሰጠው ውል ለማስፈን በቅቶ ነበር። Canmex Minerals የተሰኘው የካናዳ ኩባንያ ደግሞ ባለፈው ወር በሶማሊላንድ ወሰን አኳያ በነዳጅ ፍለጋ ተግባር 50 ሚሊዮን ዶላር ለማውጣት ተስማምቷል። ነዳጁ ከወጣ 80 በመቶውን ድርሻ የሚይዘው ኩባንያው ነው።

በሌላ በኩል ሶማሊላንድ ውስጥ የሚካሄደው ፍለጋ በሞቃዲሾ መንግሥት ዘንድ አከራካሪ መሆኑ አልቀረም። የሢያድ ባሬን መውደቅ ተከትሎ ከሶማሊያ ተገንጥላ የብቻ መንግሥት ያቋቋመችው ሶማሊላንድ አንጻራዊ ዕርጋታ ሲታይባት የከርሰ-ምድር ተመራማሪዎች እንደሚሉት በአብዛኛው የነዳጅ ሃብት ምንጭ የሚገኘውም በዚህችው ግዛት ነው። የደቡብ አፍሪቃው ኦፊር በዚያ የጠረፍ ቦታ ሲይዝ የቻይናና የሕንድ ኩባንያዎችም ዓለምአቀፍ ዕውቅና ካልተሰጠው መንግሥት ድርሻ ለማግኘት እየጣሩ መሆናቸው ነው የሚነገረው። በተበጣጠሰችው ሶማሊያ ምንም እንኳ ዲናሪ ሁላችንም ሶማሌዎች ነን፤ ችግሩን በጋራ እንፈታዋለን ቢሉም ሃብቱን ለጋራ ጥቅም ማዋሉ ቀላል የሚሆን አይመስልም።

ምዕራባውያን ኩባንያዎችና የእሢያ ተፎካካሪዎቻቸው ለምሥራቃዊው አፍሪቃ የነዳጅ ሃብት የሚሰጡት ትኩረት እያየለ ቢሄድም ዕርጋታ ሳይሰፍን የኤነርጂ ጸጋውን አውጥቶ መጠቀም መቻሉ ብዙ የሚያጠያይቅ ነው። በሌላ በኩል እጅግ በተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ የምትገኘው ቻይና የኤነርጂ ጥሟን ለመወጣት በያዘችው ግፊት በተለይ በአፍሪቃ ፖሊሲዋን በማጠናከሯ ለምዕራቡ ዓለም ፉክክር ከመግጠም የተለየ ሌላ ምርጫ አይጠብቀውም። ይህም ነው ብዙዎች ኩባንያዎችን ዕርጋታ በሌለባቸው አካባቢዎች ገንዘብ ለማፍሰስ እስከመገፋፋት ያደረሰው።

ቻይና ዛሬ አርባ በመቶውን የኤነርጂ ፍጆቷን የምትወጣው ነዳጅ ከውጭ በማስገባት ነው። ይሄው መጠን በ 2020 ገደማ 60 በመቶ እንደሚደርስም ይጠበቃል። ቻይና በመካከለኛው ምሥራቅ የነዳጅ አቅርቦት መሰናከል መቻል ባደረባት ስጋት፤ ከማዕከላዊው እሢያና ከሩሢያ የቧምባ ዝርጊያው ረጅም ጊዜ ሊፈጅ እንደሚችል በማሰብም ነው ወደ አፍሪቃ በሰፊው ያዘነበለችው። ምዕራባውያን መንግሥታት ቻይና በአፍሪቃ ሰብዓዊ መብትን ከሚረግጡ ገዢዎች ትተራበራለች ሲሉ ፖሊሲዋን ቢነቅፉም ግንኙነቷን ቁርጠኛ ሆና ማስፋፋቱን ቀጥላለች።

ለቻይና ግንኙነቱ የውጭ ፖሊሲዋ ዓቢይ አካል ነው። በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ታዳብራለች፤ ከብዙዎች አገሮች ጋር የንግድ ስምምነቶችን ተፈራርማለች። ቤይጂንግ ከአፍሪቃ መንግሥታት ጋር የጋራ የትብብር መድረክ በመፍጠር ከ 5,5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዕርዳታ ስትለግስ ለ 31 አገሮች የዕዳ ስረዛ ማድረጓ የሚታወቅ ነው። በአፍሪቃ መዋቅራዊ ግንባታ ዘርፍ ዛሬ የቻይና ሠራተኞች የማይታዩበት ቦታ የለም። በናይጄሪያ የባቡር ሃዲድ ዝርጊያ፣ በሩዋንዳና በሌሎች የአፍሪቃ አገሮችም ከድልድዮች እስከ ስታዲዮሞች ግንባታ በሁሉም ዘንድ አሻራዋ ደምቆ የሚታይ ነው።

ይህ ብቻ አይደለም፤ የቻይናና የአፍሪቃ የንግድ ልውውጥ በ 2005 ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ 40 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ሊል በቅቶ ነበር። ይህም ቀደም ካለው ዓመት ሲነጻጸር በአምሥት ቢሊዮን የላቀ መሆኑ ነው። ጃፓን በተመሳሳይ ጊዜ ከአፍሪቃ ጋር ከነበራት የንግድ ልውውጥ ቢነጻጸር ደግሞ በ 22 ቢሊዮን ዶላር ክፍ ያለ ይሆናል። የቻይና በአፍሪቃ መሰማራት ለአካባቢው አገሮች የገቢ ምንጭ መሻሻል አስተዋጽኦ ማድረጉም አልቀረም። እርግጥ ጥያቄው የተራው ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል አድርጓል ወይ ነው። ለጊዜው አወንታዊ ምላሽ መስጠቱ ብዙ ያዳግታል።

በሌላ በኩል ምዕራባውያን መንግሥታት ዛሬ የቻይናን የአፍሪቃ ፖሊሲ ለሰብዓዊ መብት ከበሬታ እንቅፋት ሆኗል ሲሉ አጥብቀው ይንቀፉ እንጂ ራሳችው ይከተሉት የነበረው መርህ ከአፍሪቃ ሕዝብ ጥቅም አንጻር ብዙም የተለየ ነበር ለማለት የሚያዳግት ነው። የዛኢሩን አምባገነን ሞቡቱን ሤሤ ሤኮን ከመሳሰሉት የአፍሪቃ ገዢዎች ጋር የነበራቸው የቀረበ ግንኙነት የማያሳማ አልነበረም ለማለት አይቻልም። ሁለቱም ግንኙነት ምናልባት የአቀራረብ ስልቱ ይለያይ እንደሆን እንጂ የአፍሪቃን የተፈጥሮ ጸጋ በመጠቀሙ ላይ ያተኮረ መሆኑ ግልጽ ነው።

በዚህ በምዕራቡ ዓለምና በቻይና መካከል ከተያዘው ክርክር አፍሪቃውያን ሊቀስሙት የሚገባው ግንዛቤ ከሁኔታው እንዴት በተሻለ መንገድ ተጠቃሚ ልንሆን እንችላለን የሚለው ሊሆን ይገባል። እርግጥ ለዚህም ዕርጋታ ወዋኝ ነው። ወደ ምሥራቅ አፍሪቃው ሁኔታ መለስ ካልንም በሶማሊያም ሆነ በሱዳን፤ በኦጋዴን ሆነ በጋምቤላ የተፈጥሮው ጸጋ ለአውጪውም ሆነ ለአገሬው ጠቃሚ የሚሆነው በቅድሚያ ለልማት ጥርጊያ የሚከፍት አስተማማኝ ሰላም ሲረጋገጥ ብቻ ነው።

ተዛማጅ ዘገባዎች