የአፍሪቃ ቀንድ ረሃብና የልማት ይዞታ | ኤኮኖሚ | DW | 27.07.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአፍሪቃ ቀንድ ረሃብና የልማት ይዞታ

በአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ በተስፋፋው ከባድ ድርቅና ይሄው ባስከተለው ረሃብ ባለፉት ወራት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል።

default

በድርቁ ሳቢያ ለረሃብ አደጋ የተጋለጠው የአካባቢው ሕዝብ 12 ሚሊዮን ገደማ እንደሚጠጋ ነው የሚነገረው። የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ፋኦ ትናንት ኢጣሊያ ርዕሰ-ከተማ ሮማ ላይ ባስተናገደው ዓለምአቀፍ ስብሰባ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰፊና የተፋጠነ ዕርዳታ እንዲቀርብ ጥሪ ሲያደርግ በእርሻ ልማት ዘርፍ ላይ ያተኮረ የረጅም ጊዜ መፍትሄ ማፈላለጉም ዓቢይ መነጋገሪያ ጉዳይ ነበር።
የዓለም ባንክ በበኩሉ በአብዛኛው ለዚሁ ተግባር በሥራ ላይ የሚውል 500 ሚሊዮን ዶላር ሲያቀርብ ሰሞኑን ናይሮቢ ላይ የለጋሾች ጉባዔም እንደሚካሄድ ይጠበቃል። የአፍሪቃን ቀንድ በወቅቱ ያዳረሰው ድርቅና የረሃብ ፈተና ከ 60 ዓመታት ወዲህ ከባዱ እንደሆነ ነው የሚነገረው። ችግሩ ታዲያ የአፍሪቃ ቀንድ የኤኮኖሚ አዋቂ ክሪስቶፈር ኢድስ እንደሚሉት እንደቀድሞው የተፈጥሮ ቁጣ ወይም እንበል የዝናብ እጦት ብቻ ያስከተው አይደለም።

“በተለይ የሶማሊያን ሁኔታ ብንመለከት ችግሩ የሁለት ነገሮች ድብልቅ፤ ማለትም የአየርና የፖለቲካ ተጽዕኖ ውጤት መሆኑን እንረዳለን። በአካባቢው ይሄ በርከት ላሉ ዓመታት የኖረ የነበረ ነገር ነው። እናም አሁን ተጽዕኖው እንደገና ጎልቶ ከሚታይበት ደረጃ ደርሷል። በጥቅሉ ባለፉት 60 ዓመታት እነዚህ ሁለት ነገሮች እየተባባሱ ነው የመጡት”

ቀደም ሲል እንደጠቀስነው ትናንት ሮማ ላይ ከተጠየቀው አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ባሻገር በተለይም በእርሻ ልማት መልክ የረጅም ጊዜ መፍትሄ የመፈለጉ ሃሣብ አንዱ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነበር። ችግሩን ከመሠረቱ መታገል መሆኑ ነው። እና እንዴት ሊሳካ ይችላል? እንደ ክሪስቶፈር ኢድስ ከሆነ ሃሣቡን ለማሳካት ዓለምአቀፍ ለጋሾችም ሆኑ የአካባቢው መንግሥታት በቅድሚያ ስህተቶችን ማረማቸው ግድ ነው የሚሆነው።

“ይሄ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው። በአካባቢው ስለዚህ ሲወራ ለነገሩ ሰላሣ ዓመታት አልፈዋል። በተለይም በ 80 ኛዎቹ ዓመታት በኢትዮጵያ ደርሶ ከነበረው ከባድ ረሃብ በኋላ በጉዳዩ ብዙ ነው የተባለው። እርግጥ ነው በአካባቢው መንግሥታትና በለጋሾች ዘንድ በእርሻ ልማት ላይ በማተኩሩና መስኖዎችን በማስፋፋት ረገድ ስህተቶች ተሰርተዋል። ይህ እንዲሳካ እንግዲህ በለጋሾም ሆነ በተረጂዎቹ መንግሥታት ዘንድ ቅንነትና ቁርጠኝነት መኖሩ ግድ ነው። በመሠረቱ ችግሩ አዲስ አይደለም። አሁን ደግሞ የሚከተለው እያደር የሚታይ ይሆናል”

ለአፍሪቃ ድርቅና ረሃብ የረጅም ጊዜ መፍትሄ የማግኘቱ ሃሣብ ለነገሩ አዲስ አይደለም። በአካባቢው ከባድ ረሃብ በተከሰተ ቁጥር በየጊዜው ይሄው ጥሪ ግሎቶ ሲሰማ ነው የኖረው። ይሁንና የተባለው ሁሉ ይባል እንጂ ሁኔታው ስር-ነቀል በሆነ መልክ ሲለወጥ አልታየም። የዓለም ሕብረተሰብ እንግዲህ ዛሬም የሚሌኒየሙን ግቦች ካስቀመጠ ከአንድ አሠርተ-ዓመት በኋላም ረሃብን ያለፈ ታሪክ ማድረጉ ቀርቶ በሚገባ ሊያለዝበው እንኳ አልቻለም። ምዕራባውያኑ መንግሥታት በድህነት ላይ ክተት ካወጁበት ከስኮትላንዱ የቡድን-ስምንት የግሌንኢግልስ ጉባዔ በኋላ ዓለም ዛሬ የምትገኝበት ሃቅ ይህን የመሰለ ነው። አፍሪቃ ኢትዮጵያን ጨምሮ በረሃብ መለያነት መታየቷ ባለበት ቀጥሏል። ሁኔታው እንዲሻሻል በተለይም በምዕራባውያኑ የልማት ዕርዳታ ፖሊሲ ላይ ለውጥ መደረጉ የአፍሪቃ መንግሥታትም የእርሻ ልማት ጥቅማቸውን ለይተው ማስቀመጣቸው አጣዳፊነት ይኖረዋል።

“አንዱ ሊደረግ የሚችለው ነገር በእርሻ ልማት ላይ በማተኮር መቀጠሉ ነው። ባለፉት ጊዜያት በመሠረቱ በሁሉም የልማት መስኮች እንቅስቃሴ ተደርጓል። እንበል በዴሞክራሲ፣ በውሁዳን መብቶች ወዘተ ... እንግዲህ ወደነዚህ የፖለቲካ ጉዳዮች ሽግሽግ ተደርጓል ማለት ነው። እና ለጋሽ መንግሥታት ሊያደርጉት የሚችሉት አንድ ነገር ወደ ልማቱ ዘርፍ የመመለስ መንፈስ እንዲጠናከር ማድረግ ይሆናል። ለረጅም ጊዜ ሲወራ የኖረው በብዙ አገሮች የእርሻ ልማትን ለማዳበር ተገቢው ሁኔታ እንዳልተመቻቸ ነው። ተዓምር አይኖርም። እናም እዚህ ላይ ለጋሾችም ተለጋሾችም የልማቱን ዘርፍ በረጅም ጊዜ ለማዳበር ጽናት ማሳየት አለባቸው”

የአፍሪቃ መንግሥታትም ራሳቸው ችግሩን ለማስወገድ ወይም ቢቀር ለመቋቋም የቤት ስራቸውን በሚገባ አከናውነዋል ለማለት አይቻልም። በሙስና፣ በበጎ አስተዳደር ጉድለትና አቅድ ባጣ የኤኮኖሚ ዘይቤ የተነሣ ከወደፊት ዕርምጃ ይልቅ የኋልዮሽ ሂደት አመዝኖ መቀጠሉ ያለ ነው። ለዕድገት የተገኘውን ዕድል ሁሉ በሚገባ መጠቀም አልተቻለም። የአፍሪቃን ቀንድ አካባቢ ሁለት አገሮች ኢትዮጵያንና ኡጋንዳን ብንመለከት፤ እነዚህ ሁለት አገሮች ባለፉት ዓመታት በአፍሪቃ ያልተቋረጠ ከፍተኛ የኤኮኖሚ ዕድገት ማድረጋቸው ከሚነገርላቸው አገሮች መካከል የሚመደቡት ናቸው። ዓለምአቀፍ ዕርዳታን በመቀበል ረገድም ቢሆን በአካባቢው ቀደምት መሆናቸው የተሰወረ ነገር አይደለም። ይህም ሆኖ ግን አሁንም የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ሕዝቦቻቸውን ከረሃብ ሞት ለመሰወር አልበቁም። ለምን?

“በአካባቢው ዛሬ ትልቁ ጉድለት አስፈላጊው የእርሻ ልማት መዋቅር አለመኖር ነው። እርግጥ ኢትዮጵያ መስኖን በማስፋፋት የተወሰነ ዕርምጃ አድርጋለች። ግን የሚገባውን ያህል የተፋጠነ አይደለም። ወደፊት በውጭ መንግሥታትና ባለሃብቶች በሚካሄዱት አዳዲስ የእርሻ ልማት ፕሮዤዎች ሁኔታውን ለማሻሻል ነው ተሥፋ የተጣለው። ግን እኔ በበኩሌ ወሣኝ የማደርገው ከተመረተው ምርት ምን ያህሉ በአገር ይቆያል የሚለውን ጥያቄ ነው። ልማቱ ምንም ይል ይስፋፋ ምርቱ እንዳለ ከወጣ ችግር ይኖረዋል”
በእርግጥም ለወቅቱ የአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ረሃብ መባባስ አንዱ ምክንያት የምግብ ዋጋ ከመጠን በላይ መናር ነው። ሁኔታውን ለመሆኑ እንዴት ማሻሻል ይቻላል? የአፍሪቃው ቀንድ ጉዳይ አስተንታኝ ክሪስቶፈር ኢድስ የውጭ ጥገኝነትን መቀነሱ ይበጃል ባይ ናቸው።

“በጣም ትልቅ ጥያቄ ነው። የምግብ ዋጋ በተለያዩ ምክንያቶች ንሯል። አንዳንዶቹን የንረቱን ምክንያቶች ደግሞ የግድ ከአንድ የተወሰነ የአፍሪቃ አገር ጋር የሚያገናኛቸው ነገር የለም። ለምሳሌ በገበዮች ላይ ትርፍ ለማጋበስ የሚደረገው ጥረት! ሆኖም ግን ሁኔታውን ማባባሳቸው አልቀረም። አጠቃላዩ ይዞታ ይህ ሲሆን በአፍሪቃ አገሮች ከውጭ በሚገቡ የምግብ ምርቶች ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ መጣሩ ግድ ነው። የዋጋውን ሂደት ግን ሊቆጣጠሩት አይችሉም”

ዛሬ የምድራችን የአካባቢ አየር ከሚገኝበት ከባድ ሁኔታና ከሕዝብ ቁጥር መናር አንጻር ወደፊት የምግብ እጥረትና የምግብ ዋጋ መናር እየባሰ መቀጠሉ ብዙ ትንቢት የማያስፈልገው አይሆንም። ረሃብን በመቋቋም ወደፊት ያለፈ ታሪክ እንዲሆን ማድረጉ በተለይም የአፍሪቃውያን መንግሥታት ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባዋል። የሚያሳዝን ሆኖ አብዛኞቹ የአፍሪቃ መንግሥታት ዛሬም ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርታቸው አሥር በመቶዋን ድርሻ ለእርሻ ልማት ለማዋል የገቡትን ቃል ዕውን አላደረጉም። ይህ ደግሞ አብዛኛው ሕዝብ በገጠር በሚኖርባትና በእርሻ ላይ ጥገኛ በሆነባት ክፍለ-ዓለም ሊረዱት የሚያዳግት ነው። በየጊዜው ሕዝብ በረሃብ በተጠቃ ቁጥር ወደ ምዕራቡ ዓለም የልመና ዕጅ ለመዘርጋት መነሣቱ ያሳፍራል። አፍሪቃ የድህነትና የረሃብ መድረክ ሆና መቀጠል የለባትም። አቅድ ባለው ልማት ከወደቀችበት አዙሪት መውጣት ይኖርባታል። የሕጻን ልጆቿ ስቃይ የ 21ኛው ክፍለ-ዘመን መለያ ገጽታዋ ሊሆን አይገባም።

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሠ

Audios and videos on the topic