የአፍሪቃ ስደተኞች በኢጣልያዋ አፑልያ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 13.08.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የአፍሪቃ ስደተኞች በኢጣልያዋ አፑልያ

ከማልታና ከግሪክ ቀጥሎ በርካታ አፍሪቃውያን ስደተኞች የሚጎርፉባት አውሮፓዊት ሃገር ኢጣልያ ናት።በአንዳንድ የኢጣልያ ግዛቶች መንግሥት ህገ ወጥ የሚላቸው አፍሪቃውያን ስደተኞች ደግሞ በኢጣልያ ጎስቋላ ህይወት ነው የሚገፉት።

በሺህዎች የሚቆጠሩ መንግሥት ህገ ወጥ የሚላቸው አፍሪቃውያን ስደተኞች በየዓመቱ ኢጣልያ ይገባሉ ። እነዚህ ስደተኞች ሥራ የማግኘት ፣ የተሻለ ህይወት የመምራት ወደ ቤተሰቦቻቸውም ገንዘብ የመላክ ተስፋ ሰንቀው በአስቸጋሪው የባህር ላይ ጉዞ ከሞት አምልጠው በተለያዩ የሃገሪቱ የባህር ጠረፎች በኩል ኢጣልያ ቢደርሱም የሚያልሙትን ሁሉ የማግኘት ዕድላቸው የመነመነ ነው ። ጥገኝነት ያላገኙት ደግሞ በአሰዛን ሁኔታ የወንጀለኛ ቡድኖች ሰለባ ሆነው ይሰቃያሉ ። የዶቼቬለዎቹ አሱምፕታ ላቱስ ና ዩልያ ሃን ጥሩ ተስፋ ሰንቆ ወደ ኢጣልያ የሄደ አንድ በደቡብ ምሥራቅ ኢጣልያው የአፑልያ ግዛት የሚገኝ አፍሪቃዊ ስደተኛ ያለበትን ሁኔታ ተመልክተዋል ። ከካርቶንና ከፕላስቲክ ከተቀለሰው ሊወድቅ ከተቃረበው ደሳሳ ጎጆ ውጭ ዝንቦች ያንዣብባሉ ፤ ሽታው ከሩቅ የሚተነፍገው ሳምንታት ያስቆጠረው ቆሻሻ ተከሞሯል ። በስፍራው ይህን መሰል ብዙ ጎጆዎች ይገኛሉ ። ንጹህ የመጠጥ ውሐ ኤሌክትሪክም ሆነ የመፀዳጃ ቤት የለም ። ነዋሪዎቹ አፑልያ ኢጣልያ ውስጥ የሚገኘውን ይህን አካባቢ የጎስቋሎች መንደር ወይም ጌቶ ነው የሚሉት ።

በአንደኛው ጎጆ ውስጥ አንድ ፍራሽ ላይ 5 ሰዎች ተኝተዋል ። በጥቂት ሴንቲሜትሮች ርቀት የሚገኙ ሌሎች 10 ባዶ ፍራሾችም በዚሁ ጎጆ ውስጥ አሉ ። ከላይ የሚንጠለጠሉ ገመዶች እንደ ልብስ መስቀያ ያገለግላሉ ። ወለሉ ላይ ጫማዎች ተደርድረዋል ። በፕላስቲክ ሳህኖች ምግብ ተቀምጧል ። አትሞ

ጎጆዋ የኢብራ ምባኬ ፋልና በአመዛኙ ከምዕራብ አፍሪቃ የመጡ የሌሎች 20 ስደተኞች መኖሪያ ናት ። ጎጆዋ ጠባብና ብዙ ሰዎች የሚኖርባት በመሆኗ አየር የታፈገና መጥፎ ጠረንም ያለው ነው ። ኢብራ ድህነትን ሸሽቶ ህይወቱን ለሞት አጋልጦ በአደገኛው የባህር ላይ ጉዞ ከሴኔጋል ትልቅ ተስፋ ይዞ ወደ ደቡብ ኢጣልያዋ የባህር ዳርቻ የመጣው የዛሬ 12 ዓመት ነው ።

«እዚህ የመጣሁት የራሴን ህይወት ለማሻሻል የሚረዳኝ ጥሩ ሥራ ማግኘት እችላለሁ ፤ ሴኔጋል የሚገኙትንም ቤተሰቦቼን ለመርዳት የሚያስችለኝ ጥሩ ገንዘብ አገኛለሁ ብዬ ነበር ። »

እስካሁን ግን ኢብራ በኢጣልያ የሚመኘውን ህይወት አላገኘም ። ኑሮ በኢጣልያዋ የባህር ዳርቻ አፑልያ ከድጡ ወደ ማጡ ሆኖበታል ። የ32 ዓመቱ ኢብራ በአገሩ የኮራ አናፂ ነበር ። ኢጣልያ እንደሄደ በሙያው መሥራት ባይችልም መጀመሪያ ላይ ጣልያኖች መሥራት የማይፈልጉትን ሥራ ማግኘት ችሎ ነበር ። ጥሩ ክፍያ ባያገኝበትም ከእርሻ ቦታ አትክልትና ፍራፍሬ ይለቅም ነበር ። ያኔ ጣሊያኖች ንቀው የማይሰሩት ይህ ሥራ ዛሬ የሰማይ ያህል ርቋል ። አሁን እንደ ቀድሞው በቀላሉ የሚገኝ ሥራ አልሆነም ። በዚህ የተነሳም አሁን የሚሰራው አጥቶ ሥራ ፍለጋ ሲዋትት ነው የሚውለው ። ኢብራን ለዕለት ቀለቡ ብቻ ሳይሆን አገሩ ሴኔጋል ለሚገኙት ዘመዶቹም ነው የሚያስበው ። ሥራ በነበረው ጊዜ ከሚያገኘው ገንዘብ ቆጥቦ ይልክላቸው ነበር ። አሁን ግን ያን ማድረግ አልቻለም ።

Destination Europe – Kapitel-Nr. 4

«ወደ አገር ቤት ገንዘብ መላክ ካቆምኩ 3 ወር ሆነኝ ። ሥራም ሆነ ገንዘብ እንደሌለኝ ልገልፅላቸው ብሞክርም የሚያምነኝ አላገኘሁም ። እነርሱን ዘንግቼ አውሮፓ የምንፈላሰስ ነው የሚመስላቸው »

ኢብራ ሥራ ከማጣቱ በፊት በሰዓት 3 ዩሮ ለሚከፍሉት ካፖላሪ ለሚባሉት ለኢጣልያና ለአፍሪቃ ማፍያዎች ይሰራ ነበር ። የስራ ውል ወይም ኮንትራት እንዲሰጠው ጠይቆ ስላልተሳካለት አቋርጦታል ። ኢብራ የኮንትራት ሥራ ይዞ ከሥራ ቢባረር እንኳን ከመግሥት ጥቂትም ቢሆን ገንዘብ ሊያገኝ እንደሚችል ያውቃል ። ይሁናና ለኢብራ ስራ የሚያመቻቹት እነዚህ ማፍያዎች ለመብቶቹ ደንታም የላቸውም ። ማፍያዎቹ ኢብራና መሰሎቹ ሊያገኙት ከሚገባው ገንዘብ 50 በመቶውን ወደራሳቸው ኪስ ያስገባሉ ። እነ ኢብራን በአነስተኛ ገንዘብ ቀጥረው የሚያሠሩት የአካባቢው ገበሬዎች ብዙ ያተርፉባቸዋል ። ኑሮ በኢጣልያ ያልተሳካለት ኢብራ አሁን ወደ ሃገሩ ወደ ሴኔጋል መመለስን እንደ ሽንፈት ነው የሚቆጥረው ። ወደ ሃገሩ ለመመለስ ቢወስን እንኳን ቲኬት መግዣ ገንዘብ የለውም ። ለክፉ ቀን ብሎ ያጠራቀመው ገንዘብም ቢሆን ተሟጧል ። አሁን ምናልባት ሥራ የሚሰጥ ባገኝ ብሎ በአትክልት እርሻዎች አካባቢ ይዘዋወራል ። ኑሮው ከቀድሞው አሁን ከብዶታል ። በአካባቢው እርዳታ የሚለግስ ደግሞ አንድ ድርጅት ብቻ ነው ።

Einwanderer in Spanien

« እዚህ ሲመጣ የምናየው ብቸኛው ድርጅት የካቶሊካውያን የበጎ አድራጎት ድርጅት ካሪታስ ነው ። ባለፉት ሁለት ወራት ሶስት ጊዜ ያህል ብቻ ነው የመጣው ። ሩዝ ፓስታ እና ቲማቲም ያከፋፍለናል ።»

በኢጣልያዋ የአፑልያ ግዛት በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ አፍሪቃውያን ስደተኞች ይኖራሉ ። አብዛናዎቹም መንግሥት ህገ ወጥ የሚላቸው ስደተኞች ናቸው ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀው በጎርጎሮሳውያኑ 2013 የመጀመሪያዎቹ 6 ወራት ከጥር እስከ እስካለፈው ሰኔ ወር ድረስ ፣ 8 ሺህ አፍሪቃውያን ስደተኞች ደቡብ ኢጣልያዋ ደሴት ላምፔዱዛ ገብተዋል ። የሚመጡትም በአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ውስጥ ሥራ ፍለጋ ነው ። እናም ከቀናቸው አብዛኛዎቹ ኢጣልያ ላይቆዩም ይችላሉ ። ያልሆነላቸው ደግሞ ኮፖራሊ በተባለው የወንጀለኞች ቡድን ስር እዚያው ኢጣልያ ውስጥ በሚገኙት የአትክልት እርሻዎች መስራት ይሆናል ዕጣቸው ። የአካባቢው ነዋሪዎች አፍሪቃውያኑ ስለሚገፉት ጎስቋላ ህይወት ያውቃሉ ። አንዳንዶቹ በአካባቢው አሁን ለነርሱ የሚሆን ስራ አንደሌለ ሲናገሩ ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ስደተኞቹ አመፅ እንዳያስነሱ ስጋት አላቸው ።

« በርካታ አፍሪቃውያን እዚህ እየመጡ ሥራ እንዳለ ይጠይቃሉ ። ሆኖም እዚህ ሥራ የለም ። በአንድ ወቅት ከመካከላቸው አንዱን ቀጥሬው ነበር ። ይሁንና አሁን ለርሱ የሚሆን ሥራ የለኝም ። »

«ወደ ተጎሳቆለው መንደር አልሄድኩም ። ሆኖም በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚኖሩ ሰምቻለሁ ። ሁኔታውንም ካሉበት ችግር ለማምለጥ እንደ አመፅ ማስነሻ አድርገው ሊጠቀሙበትም ይችላሉ ። ይህም መንግሥት ምንም እንደማያደርግ ያሳያል ። »

አስተያየት ሰጭዎቹ ይህን ቢሉም በካፖላሪዎች ወይም በማፍያዎች ጉዳይ ውስጥ ገብተው መናገር ግን ይፈራሉ ። ኢብራ እንደሚለው መንግሥትም ቢሆን ስደተኞቹን ዞር ብሎ አያይም ።

Afrikanische Migranten Almeria Behausung

« ባለሥልጣናቱ በምንም ዓይነት መንገድ አይረዱንም ። »

የአፑልዪ ከንቲባ ጅያንፍራንኮ ሳቪኖ በአፑሊያ የሚኖሩትን አፍሪቃውያን ስደተኞች ለመርዳት ምንም አለማድረጋቸውን ያምናሉ ። ምክንያት የሚያደርጉትም ሃገሪቱ አህን ያለባትን ችግር ነው ።

«የኤኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ነው ያለነው ። ያም ማለት እኛም ጎስቋላው መንደር እንደሚኖሩት ሰዎች ሁሉ ሥራ የሚያሻቸው ብዙ ሰዎች አሉን ። ኢጣልያ ውስጥ ከመንግሥት ተቋማት አንስቶ እስከ አካባቢ ባለሥልጣናት ድረስ እጅግ ከፍተኛ የኤኮኖሚ ችግር አለ ። በዚያ ላይ ደግሞ የስደተኞች ጉዳይም ሌላው ተጨማሪ ችግር ነው ። »

በአሁኑ ጊዜ ከግሪክ ቀጥሎ አውሮፓውያንን የሚያስጨንቀው የኢጣልያ ችግር ሆኗል ። ሃገሪቱ ከገጠማት የኢኮኖሚ ቀውስ ሌላ በየጊዜው በስደተኞች መጥለቅለቋ አሳሳቢ ነው ። አርካንጄሎ ስደተኞችን በተቻላቸው መጠን የሚረዱ የካቶሊክ ቄስ ናቸው ።

አፍሪቃውያኑን በየጊዜው ይጎበኟቸዋል ። ጣሊያንኛ እንዲማሩ የቋንቋ ኮርሶችን በማዘጋጀት እንዲሁም በተቻለ ሁሉ ስደተኞቹን ለማፅናናት ይሞክራሉ ። በእርሳቸው አስተያየት መንግሥት ስደተኞችን ላለመርዳት ችግሩን ሰበብ አድርጎ ማቅረቡ ተቀባይነት የለውም

«የኢጣልያ ተቋማት የሆኑት የፖሊስ ና የኢሚግሬሽን ቢሮዎች ማከናወን የሚገባቸውን እየሰሩ አይደለም ። ከዚህ ችግር በስተጀርባ ያሉት እነርሱ ናቸው ። ሁኔታው እንዲቀጥል ይፈልጋሉ ብዮም አስባለሁ ። ያ ካልሆነ ግን ባለቸው ሥልጣንና በስራቸው ያለውን አማራጭ ሁሉ ተጠቅመው ችግሩን ለምን አያስወግዱም ? »

ይሁንና ቄስ አርካንጄሎ ከኢጣልያ ቢሮክራሲ ጋር የተያያዘውን ይህን ችግር የመፍታት አቅም እንደሌላቸው ነው የሚያስረዱት ። አሁን ለኢብራ በአውሮፓ የተሻለ ህይወት የመምራት ተስፋው ወደ ቅዠት ተለውጧል ። አሁን ያለው አማራጭ አዲሱ መኖሪያው በሆነው በጎስቋላው መንደር እየኖረ ሥራ ፍለጋውን መቀጠል ብቻ ነው ።

ሂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic