1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ ሥደተኞች፥ የአዉሮጳ ሕብረትና የማሊ ማዕከል

ማክሰኞ፣ መስከረም 27 2001

...ለአፍሪቃ ከፍተዉ የአፍሪቃ ምጣኔ ሐብት እንዲያድግ ቢያደርጉ ብዙዎች እንደሚሉት ዘላቂ መፍትሔ በሆነ ነበር።

https://p.dw.com/p/FVfn
እነዚሕ ቢያንስ ከሞት ተርፈዉ-ጣሊያን ጠረፍ ደርሰዋልምስል AP

የአዉሮጳ ሕብረት ወደ አዉሮጳ የሚሰደዱ አፍሪቃዉያን የሚሠፍሩና የሚሠለጥኑበት ማዕከል ማሊ ርዕሠ-ከተማ ባማኮ ዉስጥ ከፍቷል።ሕብረቱ ከአዉሮጳ ዉጪ የስደተኞች ማዕከል ሲከፍት ያሁኑ የመጀመሪያዉ ነዉ።ባለፈዉ ዕሁድ የተከፈተዉ ማዕከል ወደ አዉሮጳ የሚገቡ ሕገ-ወጥ ስደተኞችን ለመቆጣጠርና በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ አዉሮጳ ለመግባት ሲሞክሩ ሕይወታቸዉን የሚያጡ አፍሪቃዉያንን ከአደጋ ለመከላል ይረዳል።ማዕከሉ ወደ አዉሮጳ ለሚሰደዱ አፍሪቃዉያን የቋንቋና የሙያ ሥልጠና ይሰጥበታልም።ይሁንና የማዕከሉን መቋቋም የሚቃወሙም አሉ።ነጋሽ መሐመድ ዝር ዝሩን አጠናቅሮታል።


ብዙ ተጉዟል-ካሰበዉ ግን አልደረሰም።ሙሉ ስሙን መናገር አይፈልግም።ምናልባት ካሰበዉ እስኪደርስ-ክላዉደ-መባሉን ብቻ ነዉ የመረጠዉ።ኮንጓዊ ነዉ።ሲሔድ፥ ሲሔድ፥ ሲሔድ አልጄሪያ ድንበር ላይ ከምትገኘዉ ትንሽ የሞሮኮ ከተማ አጠገብ ደርሷል።

«በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ በኩል ወደ ካሜሩን ተሰደድኩ።ከካሜሩን ናይጄሪያና ቤኒንን አቋርጬ ኒጀር ገባዉ።ከኒጀር በአልጄሪያ አድርጌ እዚሕ ደረስኩ።ድፍን ስድስት ወር ስጓዝ ነበር።ገንዘብ ካገኘዉ ጉዞዬን አሁንም አቅጠላለሁ።»

ከተሳካለት-ዛሬም፥ እንደ ድምፃዊቷ ልብ፥ መንገደኛ ነዉ።-አዉሮጳ እስኪገባ።ወይም በየጊዜዉ የሚጠብቀዉን የአዉሮጶች ቁጥጥርን ሾልኮ የሚያልፍበትን የሐሩር-የባሕር መስመር ለማቋረጥ እየሔደ እንደ ብዙ ብጤዎቹ እንድም በረሐ፥ አለያም ባሕር ዉስጥ ይቀራል።የአዉሮጳ ሕብረት ከማሊ መንግሥት ጋር በመተባበር ባማኮ ላይ ሥለከፈተዉ ማዕከል የሚስረዳዉ ሰነድ መልዕክት ፥ ሱድ ዶቸ ሳይቱንግ የተሰኘዉ የጀርመን ዕለታዊ ጋዜጣ እንደፃፈዉ ጥሩ ነዉ።

ጥሩነቱ ደግሞ ለሁሉም ነዉ።ክላዉደን-የመሳሰሉ ብዙ ሺሕ አፍሪቃዉያን ወጣቶች ባዝነዉ እንዳይቀሩ፥ ከከፋም የበረሐ፥ የዉሐ የጥይት-ጩቤ ሲያሳይ እንዳይሆኑ፥ በየደረሱበት ከወንጀለኞች እጅ እንዳይወድቁ ወይም ራሳቸዉ ወንጀለኛ እንዳይሆን ለመከላከል ይረዳል።-አንድ።

መከራዉን አልፈዉ-አዉሮጳ ቢገቡ እንኳን በሕገ-ወጥነት ከመሸማቀቅ፥ በሥዉር ሥራ ከመበዝበዝ፥ ለሴተኛ አዳሪነት፥ ለወንጀለኝነት ከመጋለጥ ይተርፋሉ።ሁለት።

የአዉሮጳ መንግሥታት የማይፈልጉትን ሥደተኛ በየጠረፉ ከማደን፥ አልፎ ከመጣም ከማስተናገድ ይገላገላሉ።-ሰወስት። የአፍሪቃ መንግሥታት በተለይ እንደ ማሊ፥ ሊቢያ፥ አልጄሪያ፥ ሞሮኮ የመሳሰሉት ለስደት የፈለሱ አፍሪቃዉያን መጨናነቂያ፥ የሕገ-ወጥ አሻጋሪዎች መናኸሪያ ከመሆን ይድናሉ-አራት።የማሊዉ ፕሬዝዳት አማዱ ቶማኒ ቶሬ በማዕከሉ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ይሕንኑ መስከረዋረዋል።

«እዚሕ ላይ ልናሰምርበት የሚገባዉ ጉዳይ መንግሥታት ሕገ-ወጥ ስደተኞችን የሚያሻግሩ ወንጀለኞችን መረብ ለመቆጣጠር እስካሁን አለመቻላቸዉን ነዉ።»

የአዉሮጳ ሕብረት እስከ ሁለት ሺሕ አራት-ድረስ አስር ሚሊዮን ዩሮ የሚያፈስበት ማዕከል ወደ አዉሮጳ መሻገር ለሚፈልጉ አፍሪቃዉያን የሙያና የቋንቋ ሥልጠናና ትምሕርትም ይሰጥበታል።ይሕ ማለት ግን የሕብረቱ የልማት ኮሚሽን ቃል አቀባይ ጆን ክላንሲ እንዳሉት ከማዕከሉ የሚገባዉ አፍሪቃዊ ሥልጠናዉን እንዳጠናቀቀ ከባማኮ ፍራንክፈርት ተሻግሮ ማክ-ዶናልድ ሳንዲዊች ቤት ይቀጠራል ማለት አይደለም።የሕብረቱ መንግሥታት በፈለጉበት ወቅት የሚፈለጉትን የሰዉ ሐይል ብቻ ነዉ-የሚወስዱበት።ወሳጅ ያጡት ደግሞ ወደየሐገራቸዉ መመለሳቸዉ ግድ ነዉ።

አንዳድ የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ግን ማዕከሉ አፍሪቃዉዊን ስደተኛ ባለበት ከማስቀረት ባለፍ የሚተክረዉ ነገር የለም።የሕብረቱ የልማት ተራድኦ ኮሚሽን ሉዊ ሚሼል ግን የመብት ተሟጋቾቹን ትችት አይቀበሉትም።
ድምፅ
«ስደተኝነት ሊቀር የማይችል የሰዉ ተፈጥሯዊ ክስተት ነዉ።እንደሚጠቅመን አጋጣሚ አድርገን ልንቀበለዉ ይገባል እንጂ የምናስወግደዉ ክስተት አድርገን የማየት የለብንም።የሰዉ ልጅ ታሪክ ሁሉ የስደተኝነት ታሪክ ነዉ።ስደተኝነት የሌለበት ታሪክ አልነበረም፥ አይኖርምም»

ከተለያዩ ሐገራት በተለይም ከአዉሮጳ የተመለሱ የቀድሞ የማሊ ስደተኞች የመሠረቱት ማሕበር እንደሚለዉ ግን ማዕከሉ የአፍሪቃ ስደተኞች አዉሮጳ እንዳይገቡ ለመከላል የአዉሮጳ ሕብረት የድንበር አጥርን እስከ ባማኮ ያደረሰ ነዉ-በማለት አጣጥሎ ነቆፎታል።አፍሪቃዉያን ወጣቶች ከበለፀገዉ አለም ለመግባት እየሔዱ መሞትን እስከ መምረጥ የደረሱት በየሐገራቸዉ ሥራ-ና የመኖር ዋስትና በማጣታቸዉ ነዉ።

አዉሮጳና ብጤዎችዋ አፍሪቃዉያን ወጣቶችን በየኬላ-ማቆያ ሠፈሩ ከመቆጣጠር-ከማቆየት ይልቅ በየሐገሩ መልካም አስተዳደር እንዲመሰረት፥ ገበያቸዉን ለአፍሪቃ ከፍተዉ የአፍሪቃ ምጣኔ ሐብት እንዲያድግ ቢያደርጉ ብዙዎች እንደሚሉት ዘላቂ መፍትሔ በሆነ ነበር።