የአፍሪቃ ሚዲያ መሪዎች ጉባኤ እና «ሲ ፒ ጄይ» | አፍሪቃ | DW | 11.11.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የአፍሪቃ ሚዲያ መሪዎች ጉባኤ እና «ሲ ፒ ጄይ»

የአፍሪቃ ሚዲያ መሪዎች ጉባኤ ካለፈው ረቡዕ እስከ ዓርብ ድረስ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በዚህ ጉባኤ ላይ ከተካፈሉ ድርጅቶች መካከል ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተዉ ዓለም ዓቀፉ ድርጅት «ሲ ፒ ጄይ» ይገኝበታል።

CPJ logo, COMMITTEE TO PROTECT JOURNALISTS, graphic element on white 2008/11/26

ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተዉ ዓለም ዓቀፉ ድርጅት «ሲ ፒ ጄይ» የምስራቅ አፍሪቃ ተጠሪ የሆኑት ቶም ሮድስ በኢትዮጵያ የፕረስ ነፃነት ይዞታ ባልተሟላበት እና ጋዜጠኞች ታስረው በሚገኙበት ሁኔታ በአዲስ አበባ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የአፍሪቃ ሚዲያ መሪዎች ጉባኤ ላይ ድርጅታቸው ይካፈል አይካፈል በሚለው ጥያቄ ላይ ብዙ ካሰላሰለ በኋላ ለመሳተፍ እንደወሰነ ነበር የገለጹት። « ሰባት ጋዜጠኞች በእስር ላይ እያሉ በመገናኛ ብዙኃን እድገት ላይ ተሰብስቦ መወያየቱ ስህተት መስሎ ታይቶን ነበር። ይሁንና ስጋታችንን ለ «ኤ ኤም አይ» (አፍሪካን ሚዲያ ኢኒሽየቲቭ) ኃላፊዎች ገልጸናል። የግድ ወቀሳ ለማቅረብ ብቻ ሳይሆን በጋራ መፍትሄ ለመፈለግ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋ መካፈሉ አስፈላጊ ነበር ። ዝም ከምንልና ከስብሰባው ከምንቀር በስብሰባው ላይ ብንካፈል እና ድርድር ብንጀምር ይሻላል የሚለው ውሳኔ ላይ ደረስኩ።»

የአዲስ አበባው ጉባኤ ያተኮረው የአፍሪቃውያን ዘገባ አቅራቢዎች እና ፀሀፊዎችን ድምፅ እንዴት በአለም አቀፉ የመገናኛ ብዙኋን ላይ እንዲሰማ ማበረታታት ይቻላል፣ እንዲሁም የፕረስ ነፃነት እና መሻሻል የሚገባቸው የፕረስ ህጎች በሚሉ ነጥቦች ላይ እንደነበር ሮድስ ገልጸውልናል። ጉባኤው ለሮድስ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር በአካል ተገናኝተው ለመነጋገርም እድል ፈጥሮላቸዋል።
«ስም መጥቀስ አልፈልግም ነገር ግን ከተወሰኑ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ይፋ ያልሆነ ንግግር ለማድረግ ችያለሁ። እና CPJ እንደዚህ አይነቱ አጋጣሚ ወደፊትም ይፈጠራል ብሎ ተስፋ ያደርጋል። የሚገርም ሆኖ ያገኘሁት ከአንዳንድ ባለስልጣናት ጋ በተናጠል ስነጋገር የታሰሩትን ጋዜጠኞች በተመለከተ ያላቸው አስተያየት የተለየ መሆኑ ነው። አንዳንዶቹ በተወሰኑት ጋዜጠኞች መፈታት ይስማማሉ። ይሄ የሚያበረታታ ነው። እና በአሁኑ ሰዓት የተወሰኑ ለውጦች እናያለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።»

ቶም ሮድስ በመንግስት እና በጋዜጠኞች በኩል ሊለወጡ የሚገባቸው ነገሮች አሉ ብለው ያምናሉ።
«የመጀመሪያው ርምጃ የ 2009ኙ የፀረ አሸባሪነት ህግ የሚሻሻልበት እና ጋዜጠኞች በነፃ መዘገብ የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠር አለበት ብዬ አምናለሁ። ከዚህ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃንም ሙያዊ ግዴታውን በሚገባ ለመወጣት እና በተቻላቸው መጠን የተመዛዘነ ዘገባ ለማቅረብ መሞከር አለባቸው ብዬ አምናለሁ። »

ቶም ሮድስ የአፍሪቃ ሚዲያ መሪዎች ጉባኤን ከመካፈል በተጨማሪ የታሰሩ ጋዜጠኞችንም ለመጎብኘት ሞክረው እንደነበር ገልፀውልናል። «እኔና የተወሰኑ የኢትዮጲያ ባልደረቦቼ ሆነን ቃሊቲ ወደሚገኘው ወህኒ ቤት ትናንት ሄደን ነበር። ርዮት አለሙ፣ እስክንድር ነጋን እና ውብሸት ታዬን ለመጎብኘት ነበር የፈለግነው። ይሁንና አልተፈቀደልንም፤ ያሳዝናል። እንደውም ከውብሸት ታዬ ጋ እንድንነጋገር የሚፈቀድልን መስሎኝ ነበር። ነገር ግን ሳይሆን ቀርቷል።»

ቶም ሮድስም ይሁኑ ሌሎች ባልደረቦቻቸው የታሰሩትን ጋዜጠኞች እንዳይጎበኙ የተከለከሉበት ምክንያት ምን እንደሆነ ሲገልፁ፤ « ጠባቂዎቹ ተረኛው ኃላፊ በአቅራቢያው እንደሌለ እና በአካባቢው ፍቃዱን የሚሰጥ ሰው እንደሌለ ነው የነገሩን። ብዙ ሰበቦች ሲፈጠሩ ታዝበናል። እኛ ብቻም ሳንሆን ይህንን የአፍሪቃ ሚዲያ ጉባኤ ያዘጋጁትም ጭምር እስረኞችን ለመጎብኘት ሞክረው ነበር ። ነገር ግን የቃሊቲን ወህኒ ቤት ሁኔታ ከመታዘብ ሌላ እነሱም ከእስረኞቹ ጋ እንዲገናኙ አልተፈቀደላቸውም።»

ልደት አበበ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች