የአፍሪቃ መሪዎች ጉባኤና የክፍለ ዓለሙ ፀጥታ | አፍሪቃ | DW | 28.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የአፍሪቃ መሪዎች ጉባኤና የክፍለ ዓለሙ ፀጥታ

የአፍሪቃ ህብረት አባል ሃገራት የመሪዎች ጉባኤ ክፍለ ዓለሙን በሚፈታተኑ ችግሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚነጋገር ይጠበቃል ። ቦኮሃራም ፣ኤቦላ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ እና ደቡብ ሱዳን ጉባኤው ከሚያተኩርባቸው ርዕሶች ውስጥ ይጠቀሳሉ ።ጉባኤው በአባል ሃገራት መዋጮ የሚሰማራ ፀረ ሽብር ኃይል ማቋቋም የሚቻልበትን መንገድም ይፈልጋል ።

ከጥር 22 እስከ ጥር 23 2007 ዓም አዲስ አበባ ውስጥ የሚካሄደው የአፍሪቃ ህብረት አባል ሃገራት የመሪዎች ጉባኤ መሪ ርዕስ «ሴቶችን ለከፍተኛ አመራር ማብቃት የሚቻልበት ዘመን እና የአፍሪቃን የተፈጥሮ ሃብት በትክክለኛ መንገድ ለዜጎች ጥቅም የማዋል ዓላማ ያለው አጀንዳ 2063 የተባለው መርሃ ግብር ነው ።» ሆኖም ጉባኤው ባለፉት 6 ወራት በክፍለ ዓለሙ በተከሰቱ ቀውሶች ላይ ይበልጥ እንደሚያተኩር ነው የሚጠበቀው ። በተለይ ባለፈው መስከረም ናይይሮቢ ኬንያ በተካሄደው የህብረቱ የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት ጉባኤና በሌሎችም ስብሰባዎች ላይ በአፍሪቃ እየተስፋፋ የሄደውን የሽብር ጥቃት በአፍሪቃውያን አቅምና ገንዘብ ለመከላከል የቀረበው ሃሳብ ሰፊ ውይይት የሚካሄድበት አጀንዳ እንደሚሆን ይገመታል ። በዓለም ዓቀፉ የፀጥታ ጥናት ተቋም በእንግሊዘኛው ምህፃር ISS የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት የሪፖርት ሃላፊ ዶክተር ሰሎሞን ደርሶ እንደተናገሩት ጉባኤው ይህ ሃሳብ በተግባር የሚተረጎምበትን ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል ።ይሁንና ለዚህ የሚያስፈልገው የገንዘብ ምንጭ በርግጠኝነት አይታወቅም ።

«የናይሮቢው ጉባኤ የህብረቱ የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት አባላት ጉባኤ ብቻ ነበር እነርሱም 15 አባላት ናቸው ። አሁን የሚሰበሰቡት የአፍሪቃ ህብረ ት አባል ሃገራት በሙሉ ናቸው ።ለዚህ ሃሳብ የሚያስፈልገውን ድጋፍ ለማጠናከር ነው ጉዳዩ በአባል ሃገራት መሪዎች ደረጃ በሚካሄደው ጉባኤ ላይ የሚቀርበው ። ይህ ሃሳብ በዚህ ጉባኤ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል ። ሆኖም የገቢ ምንጮች መገኘት አለመገኘታቸው ወይም ደግሞ አባል ሃገራት ለዚህ ዓላማ የሚውል ገንዘብ ማዋጣት አለማዋጣታቸው ወደፊት የሚታይ ነው የሚሆነው ።»

በዶክተር ሰሎሞን ግምት ሃሳቡን ካቀረቡት ሃገራት አንዷ የሆነችው ኬንያ ገንዘብ ለማዋጣት ወደኋላ የምትል አይመስልም ። በተለይ ቦኮሃራም በናይጀሪያና በሌሎችም የምዕራብና ማዕከላዊ አፍሪቃ ሃገራት ያስፋፋው ጥቃት የሚገታበት መላ የጉባኤው ትኩረት መሆኑ አይቀርም ።የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በሰጡት መግለጫ እንዳሳሰቡት ቦኮሃራም ለምዕራብና ለመካከለኛው አፍሪቃ ሃገራት ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላዩ የአፍሪቃ ክፍለ ዓለምም አደጋ ሆኗል ። በቡድኑ ላይ የተጠናከረ ዓለም ዓቀፋዊ እርምጃ እንዲወሰድም ዙማ ጥሪ አቅርበዋል ። ሆኖም ዶክተር ሰሎሞን እንደሚሉት የቦኮሃራም ጥቃት ዋነኛ ሰለባ የሆነችው ናይጀሪያ ዓለም ዓቀፋዊ ወታደራዊ ድጋፍ አልጠየቀችም ።

«ናይጀሪያ በግዛቷ ውስጥ ማንኛውንም ዓለም ዓቀፋዊ ወታደራዊ ትብብር አያስፈልገኝም ብላለች ።ከቦኮሃራም በኩል የተጋረጠባትን ፈተና በራሷ እንደምትወጣው ነው የምትናገረው ። ይህ ከናይጀሪያ በኩል በተደጋጋሚ ሲሰማ የቆየ ፖለቲካዊ መልዕክት ነው

ስለዚህ ናይጀሪያ ፈረንሳይን የመሳሰለ የውጭ ኃይል በግዛቷ ውስጥ ወታደራዊ ዘመቻ እንዲያካሂድ ትፈቅዳለች ብዮ አልገምትም ።ይህ ርግጠኛ ነው ። ምናልባት ናይጀሪያ ልትጠይቅ የምትችለው ከተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ኃይሎች ልዩ ልዩ ድጋፎችን ሊሆን ይችላል ። »

የአፍሪቃ ህብረት አባል ሃገራት መሪዎች በደቡብ ሱዳን ግጭትና ምዕራብ አፍሪቃን ባስጨነቀው በኤቦላ ወረርሽኝ ላይም ይመክራሉ ።በጉባኤው መክፈቻ ላይ የሚገኙት የተመድ ዋና ፀሃፊ ባን ኪሙን የአፍሪቃ ህብረት የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት ስለ ደቡብ ሱዳን ስለ ቦኮሃራማና ስለ ኤቦላ በሚያካሂዳቸው ሌሎች ስብሰባዎች ላይም ይካፈላሉ ተብሎ ይጠበቃል ።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic