የአፍሪቃ መሪዎችና የ HRW ቅሬታ፣ | ዓለም | DW | 21.01.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የአፍሪቃ መሪዎችና የ HRW ቅሬታ፣

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት Human Rights Watch በዓለም ዙርያ ያለዉን የሰብአዊ መብት ይዞታ በሚመለከት በ 600 ገጽ የተቀናበረ ዘገባ አቅርቦአል።

default

ዋና ጽሕፈት ቤቱን በ New York ያደረገዉ፣ ይኸዉ ድርጅት፣ የአፍሪቃ መሪዎች፣ ከሱዳን መሪ ከዖማር ሃሰን አልበሽር ጎን መቆማቸዉ ቅር ያሰኘዉ መሆኑን ገልጾአል። ኢትዮጵያ ዉስጥ ፣ በመጭዉ ግንቦት ወር ከሚካሄደዉ ምርጫ በፊት በመደረግ ላይ ያለዉ የሰብአዊ መብት አያያዝ ማሽቆልቆል አሳስቦኛል ሲልም ገልጾአል። ስለ ድርጅቱ ወቅታዊ ዘገባ፣ ተክሌ የኋላ፣ በብራስልስ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ቅርንጫፍ ተጠሪ የሆኑትን አነጋግሮ ይህን ዘገባ አድርሶልናል። በብራሰልስ የ HRW ተጠሪ ሪድ ብሮዲ በመጀመሪያ የአፍሪቃ መሪዎች ስለተሰነዘረባቸው ወቀሣ እንዲህ ነበረ ያሉት። «ባለፈው ዓመት ፣ እርግጥ ነው ፣ ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መርማሪና ብይን ሰጪ ፍርድ ቤት፣ የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ፣ በዳርፉር ክፍለ ሀገር በሰብአዊነት ላይ የግፍ ተግባር ሳይፈጽሙ አልቀሩም በመባሉ ተይዘው ለፍርድ ይቀርቡ ዘንድ የማዘዣ ጥሪ ማስተላለፉ የሚታወስ ነው። ይህ፣ የግፍ ሰለባዎቹን ፣ ሰብአዊ መብታቸው የተገፈፈባቸውን ወገኖች ለመጠበቅ ዐቢይ የድርጊት እንቅሥቃሤ ነበረ። የሚያሳዝነው ግን፣ ብዙዎች የአፍሪቃ መሪዎች፣ በዚሄሁ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንደመርካትና እንደመተባበር፣ አፍሪቃውያኑን የግፍ ሰለባዎችንም እንደማገዝ፤ ህዝቡን ችላ ብለው ከዖማር ሐሰን ኧል በሺር ጎን ነው የቆሙት።

Sudan bricht diplomatische Beziehungen zum Tschad ab

ፕሬዚዳንት ዖማር ሃሰን አልበሽር

ይህ በተጨማሪ ለ HRW ተግባር ፈታኝ ሆኖ ነው የተገኘው። ለሰብአዊ መብት የሚታገለው ድርጅት ባለፉት 20 ዓመታት የሰብአዊ መብት እንቅሥቃሤ እያደገ እየተስፋፋ፣ የጦር ወንጀለኞችን መርማሪውን ፍርድ ቤት የመሳሰሉ ተቋማትንም በየቦታው እየተከለ ነበረ የመጣው--መብታቸው ለተገፈፈ ሰዎች ለመታገል ማለት ነው---። ግን አለመታደል ሆኖ፣ በዚህ ዓመት ብርቱ ሳንኮች አጋጥመውታል፤ ፍርድ ቤቱ ብቻ ሳይሆን የሰብአዊ መብት ታጋዮችም እንዲሁ--! የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎችና ታጋዮች ፣ በዓለም ዙሪያ በብዙ አገሮች ተገድለዋል። ሰብአዊ መብት እንዲከበር የሚጥሩ ተቋማትም ጥቃት ተሠንዝሮባቸዋል።

የ HRW ወቅታዊ ዘገባ ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከመጪው ግንቦት ወር ምርጫ ወዲህ የሰብአዊ መብት አያያዝ እየተባባሰ ነው ሲል ፣ ያሳሰበው መሆኑን ገልጿል። ሪድ ብሮዲ--

«የሚያሳዝን ነው፣ የሰብአዊ መብቱ አያያዝ ፤ የፓርላማ ምርጫ በዚህ ዓመት ሊካሄድ በመቃረብ ላይ ሳለ፣ የሰብአዊ መብት ሁኔታ እየተበላሸ በመሄድ ላይ ነው። በተደራጁ ተቃሚዎች ላይ ሰፊ የሆነ ጭቆና ነው በመካሄድ ላይ ያለው። የተቃውሞ ፓርቲ መሪዎችን፣ ብርቱካን ሚደቅሳን የመሳሰሉትን ማሠር --እንሆ እርሷ ተይዛ ከታሠረች ከአንድ ዓመት በላይ ሆኗል።

Dürre in Ostafrika: Äthiopien

ባለፈው ዓመት ፣ መንግሥት፣ የሲቭሉን ኅብረተሰብ በአርግጥ የሚያስጨንቅ ህግ አውጥቷል። ባለፈው ዓመት በጥር የወጣው ህግ፣ እገዳ በማስተዋወቅ ረገድ ፣ በዓይነቱ ወደር የሌለው ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ በነጻ የሰብአዊ መብት ተግባርን ለማከናወን የማያስችል ነው። ባለፈው ሐምሌም የወጣው ፀረ-አሸባሪነት ህግ መንግሥት፣ የፖለቲካ ተቃውሞ ለማሰማት አደባባይ የሚወጡ ሰዎችን እንዲሁም ያለ ነውጥ ቅሬታቸውን የሚያቀርቡትን ፣ የአሸባሪነት ተግባር የፈጸሙ ይመስል ለፍርድ እንዲያቀርባቸው የሚያደርግ ነው። ያሳዝናል! ሁኔታው በጣሙን የሚያስደስት አይደለም። »

HRW በዓለም ዙሪያ የሰው ልጅ መብት እንዲከበር ጥረት ያደርጋል። ይጮኻል፣ ያጋልጣል፣ ግን የሰውን ልጅ መብት መርገጡ፣ እርስዎም አሁን እንደጠቆሙት ሊያስቆም አልቻለም ። እንዲያውም የሰብአዊ መብት ረገጣው እየተባባሰ ነው የሄደው። ሰብአዊ መብት የሚረግጡትን ፤ ከዚሁ ተግባራቸው እንዲታቀቡ ማድረግ አልቻለም። ሰብአዊ መብትን የየመንግሥታቱ ጥቅም እያሸነፈው ይሆን!?

«ይመስለኛል፣ ይመስለኛል። ለጋሽ መንግሥታት ፣ የሰብአዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች፣ በድርቅና በምግብ እጥረት የተጎዱትን ለመርዳት መግቢያ እንዳያጡ ይሠጋሉ እንደሚያውቁት፣ በዓለም ውስጥ፣ የአርዳታ እጅግ ጥገኞች ከሆኑት አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ናት። የሚያሳዝነው ታላላቆቹ ለጋሽ መንግሥታት፣ ፣ መንግሥት የሚያደርገውን የጭቆና አሠራር እንዲገታ ፣ ለምን? ብለው በመጋፈጥ ለማስቆም ፈቃደኞች ሆነው አልተገኙም፣--ጭቆናው ይበልጥ እየተባባሰ ቢሄድም እንኳ!። የልማት ተራድዖ ድርጅቶችንም ፣ መንግሥት ከለጋሽ መንግሥታት አንጻር መጠቀሚያ ነው የሚያደርጋቸው። መንግሥታቱ፣ «የሰብአዊ መብት ተጣሰ! ብለን ብንቃወም፣ እርዳታው ይበልጥ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ይጉዳሉ» ባዮች ናቸው። ይህ በተለይ ጎልቶ የሚታየው በብሪታንያ መንግሥት አሠራር በኩል ነው።

ተክሌ የኋላ/ሒሩት መለሰ