የአፍሪቃ መሪዎችና የአፍሪቃ እዉነታ | ዓለም | DW | 01.02.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የአፍሪቃ መሪዎችና የአፍሪቃ እዉነታ

ከነገ-በሕዋላ የአፍሪቃ መሪዎች አዲስ አበባ መጡ፥ አወሩ ሔዱ እንጂ-ሰላም ለማስፈን፥ ግጭት ጦርነትን ለማስወገድ፥ ልማትን ለማስፈን ሁነኛ እርምጃ ወሰዱ ማለትን እንደናፈቅን-ሁለት ሺሕ አሥር አምና ሲሆን-ዤን ፔንግ ወይም ብጤዎቻቸዉ የሚሉትን ለመስማት ያብቃን።

default

አሕ አባል ሐገራት ባንዲራዎች

01 02 10

የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዘዳንት ዤን ፔንግ ባለፈዉ ሳምንት ሮብ እንዳሉት ሕብረታቸዉ የጎርጎሮሳዉያኑን 2010 የአፍሪቃ ትንሳኤ፣ የሰላምና የልማት አመት ብሎ ሰይሞታል።ፔንግ የመሩት የአምባሳደሮች ስብሰባ ማክሰኞና ሮብ የመከረበትን፣ፔንግ የተካፈሉበት የሚንስትሮች ስብሰባ አርብና ቅዳሜ የተስማማበትን ስያሜ፣ፔንግ ዘገባ ያቀረቡበት የመሪዎች ጉባኤ አስፅድቆ-ለገቢራዊነቱ ቃል ሊገባ ዛሬ-ሁለት ቀን አለ።አዲስ አበባ።ስያሜዉ በርግጥ የብዙዉ የአፍሪቃዊ የዝንተ አለም ምኞት ነፀብራቅ ነዉ።ምኞት በስም መንፀባረቁ፣ መፅደቅ ቃል መገባቱ የድርጊት የሩቅ ተስፋ ብልጭታ አንኳን አለመሆኑ ነዉ ቀቢፀ ተስፋዉ።ጉባኤዉ መነሻ፣ የአፍሪቃ እዉነታ ማጣቀሻ፣ የምኞት ስያሜዉ አንድነት፣ የስያሜ-ቃል ድርጊቱ ልዩነት መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

ፔንግ ዘመኑን የአብዛኛዉን አፍሪቃዊ ምናልባትም የራሳቸዉንም ጭምር ምኞት በሚያንፀባርቅ ስም መሰየሙ ዉስብስቡን የአፍቃ ችግር ለመፍታት ብዙም እንደማይተክር በርግጥ አላጡም። አፍሪቃዊዉ በተለይ መሪዎቹ ዉስብስቡን ችግር በቅጡ አጢነዉ ግጭትን ለማስወገድ፣ልማትን ለማፋጠን፥ ፍትሐዊ አስተዳደርን ለመመሥረት ቃል እንዲገቡ፣ ለቃላቸዉ ገቢራዊነት እንዲጥሩ ወይም የሚደረጉ ጥረቶችን እንዲያበረታቱ ስያሜዉ ይጠቅማል ባይ ናቸዉ።

ሐሳቡ በርግጥ ድንቅ እንጂ ሌላ-ሊባል አይችልም፧በፓሪሱ ሻንስፖ ዩኒቨርስቲ የአፍሪቃ ጉዳይ አጥኚ ፕሮፌሰር ሮናልድ ማርሻል እንደሚሉት ግን-የአዲስ አበባ ጉባኤተኞች ስሙን ከማፅደቅ ቃል ከመግባት ባለፍ በተለይ ግጭቶች ለማስወገድ መቻላቸዉ አጣራጣሪ ነዉ።

እንደ ገና ግጭት፥ጦርነትን ለማስወገድ መመኘት ማለሙ በርግጥ ተገቢ ነዉ።ግን አንድ አመት ለሁሉም ጉዳይ ሠይሞ፥ የዝንተ አለም ዉስብስብ ችግርን ለማስወገድ ይረዳል ማለት በርግጥ ያደናግራል።
በዚሕ መሐመል በሮናልድ ማርሻል ቋንቋ አዲስ አበባ ዉስጥ ግራ ቀኝ ያስደነሰ፥የአለም አቀፉን መገናኛ ዘዴዎች ትኩረት የሳበ ጉዳይም ነበር።-የቃዛፊ ተጨማሪ ዘመነ-ሥልጣን።
ዛሬ በርግጥ ነበር ነዉ።ዳንሱ-እንደ ፕሮፌሰር ማርሻል፥ የዲፕሎማሲያዊዉ መጓተት -እንደ እዉነታዉ፥ አብቅታል።የሊቢያዉ አብዮታዊ መሪ የአፍሪቃ ሕብረትን ለተጨማሪ አመት ለመምራት የነበራቸዉ ፍላጎት፥ ያደረጉት ጥረትም ከሸፏል።በነባሩ ደንብ መሠረት የማላዊዉ ፕሬዝዳት የሕብረቱን አመታዊ የመሪነት ሥልጣን ተረክበዋል።

ጋዛፊ ሕብረቱን ለተጨማሪ አመት የመምራት ምኞት-ጥረታቸዉ ቢከሽፍም የተባበሩት የአፍሪቃ መንግሥታት መመሥረት አለበት የሚል የረጅም ጊዜ ትግላቸዉን በርግጥ አልተዉትም።እንዲያዉም ባሁኑ ፍትጊያ መሸነፋቸዉን በትልቁ ለማሸነፍ እንደ ሥልት መጠቀመቻዉ አይቀርም።

ጦርነት፥ ግጭት፥ ምጣኔ ሐብታዊ ችግር፥ ምናልባት የየገዢዎቹ በትር ያስመረረዉ አፍሪቃዊ በሊቢያ በኩል ወደ አዉሮጳ ለመሻገር ሲሞክር እያስያዙ፥ እያሰቃዩ ወደየመጣበት የሚያስግዙት አብዮታዊ መሪ አፍሪቃ ፌደራላዊ መንግሥት ታቁም ማለታቸዉ በርግጥ ግራ አጋቢ እንዳጋባ ነዉ።ማርሻል እንደሚሉት ደግሞ ጋዛፊ-የሞራል መሠረት የላቸዉም።የአፍሪቃ እዉነታም ፌደራላዊ መንግሥት ለመመሥረት አይደቅም።

በእዉነትም ፕሬዝዳት ኢሳያስ አፈወርቂ ኤትራን እንደ ነፃ ሐገር መምራት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ-እስከ ጎርጎሮሳዊያኑ 1998 ጠዋት ማታ ይመላለሱባት የነበረችዉን አዲስ አበባን በጉባኤዉ ሰበብ እንኳን መርገጥ አልፈለጉም።ወይም አልቻሉም።ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመሩትን የኤርትራን የነፃነት ትግልን ከሞራል፥ ከዲፕሎማሲ ድጋፍ ባለፍ በነፍጥ ዉጊያ የደገፉት ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ዛሬ ኢትዮጵያ ከፕሬዝዳት ኢሳያስዋ ኤርትራ ጋር በአንድ መንግሥት መተሳሰሯን አይደለም ከቀድሞ ወዳጃቸዉ ጎን መቀመጡን እንኳን አይፈቅዱትም።

ሎራ ዲዜሪ ካቢላ የሞቦቱ ሴሴኮን መንግሥት እንዲያሰግዱ ከጦር ሠፈር እስከ ገንዘብ-ከራዲዮ ጣቢያ እስከ እስከ ጦር ሐይል ዙሪያ መለስ ድጋፍ ይሰጧቸዉ የነበሩት ፕሬዝዳት ዩዌሪ ሙሳቬኒ እና ፖል ካጋሚ ሠልፍ ለዉጠዉ የካቢላን ጠላቶች ለመደገፍ አለመነቱም።ካቢላን ከተኩት ከልጃቸዉ ከጆሴፍ ካቢላ ጋር ተባብሮ ለመስራት አይደለም እንደ ዲፕሎማሲዉ ወግ እንኳን በቅጡ መመነጋገር መፍቀዳቸዉ አጠራጣሪ ነዉ።

ከጥቂት አመታት በፊት ከነ እንቤኪ፥ ከነቡተፈሊቃ፥ ከነ ኦባሳንጆ ጋር የአፍሪቃ ዲሞክራት፥ ብልሕ መሪ ይባሉ የነበሩት የሴኔጋሉ ፕሬዝዳት አብዱላሒ ወዴ ብዙዎቹ የአፍሪቃ አቻዎቻቸዉ ያወገዙ፥ ያገለሏቸዉን የጊኒ ወታደራዊ መሪ ሻምበል ሞሳ ካማራን ከዕቅፋቸዉ እንዳስገቡ ነዉ።

አፍሪቃ ጠንካራ ትብብር እንዲኖራት ከንክሩማ፥ እስከ አፄ ሐይለ ሥላሴ፥ ከኔሬሬ ካዉንዳ የነበሩ መሪዎች ብዙ መልፋት፥ መጣራቸዉ አልቀረም።ያኮብ ዙማም እንደ ጥቁሮች መብት እኩልነት ታጋይ፥ እንደ ጥንት የአፍሪቃ መሪዎች ራዕይ አክባሪ የምጣኔ ሐብት ጠንካራዋ ሐገራቸዉ የአፍሪቃን ጠንካራ አንድነት ትደግፋለች ማለታቸዉ በርግጥ አይቀይርም።ጊዜዉ ግን ለሁሉም መሪዎች ምናልባትም ለየሕዝቡም ዛሬ አይደለም።

የዙማ የቅርብ እቅድ ትኩረት-የአለምን እግር ኳስ ዋንጫ ማስተናገድ ነዉ።ምዕራቡ አለም ለዘመነ-ሥልጣናቸዉ ፍፃሜ ብዙ የታገለባቸዉ ፕሬዝዳት ሮበርት ሙጋቤ የቃዛፊን ሐሳብ መቃወም-አይችሉም።ከዲፕሎማሲዉ ሽንገላ ባለፍ እዉነተኛ ሐሳብ-ምኞታቸዉ እስካሁን ድጋፋቸዉን ያልነፈጓቸዉ የአፍሪቃ መሪዎች ወደ ባላንጣቸዉ ሞርጋን ችቫንገራይ እንዳይዞሩ ማከላከል ነዉ።

የአለም አቀፉ ፍርድ ቤት የእስራት ዋራንት የቆረጠባቸዉ ዑመር አልበሽር ወጥሮ የያዘዉ ከመታሰር የሚመልጡበትን ብሐል፥ ዳርፉር፥ ደቡብ ሱዳን እና በመጪዉ ሚያዚያ የሚደረገዉ ምርጫ እንጂ የተባበሩት የአፍሪቃ መንግሥታት አይደለም።

ከቪላ ሞቃዲሾ-እስከ አዉሮፕላን ማረፊያ ከሚያደርሰዉ የሞቃዲሾ አዉራ-ጎዳና በስተቀር እንደ ፕሬዝዳት ሶማሊያን አይደለም በደሕናዉ ጊዜ እንዳሻቸዉ እየዞሩ የኖሩ፥ የሠሩ፥ የመሩባትን መቃዲሾን ማየት የማይችሉት ሼኽ ሸሪፍ-ወደ ቪላ ሞቃዲሾ በሰላም መመለሳቸዉ ማሰላሰል አቁመዉ ሥለ አንድ የአፍሪቃ መንግሥት መመስረት ያስባሉ ማለት በርግጥ ጅልነት ነዉ።ሌሎቹም እንዲሁ።

በዚሕ ላይ ማርሻል የአለም ዋና ዋና ተዋኞች ካላቸዉ መካከል የዳርፉርን ግጭት የአለም ታላቅ ሰብአዊ ድቀት የሚለዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ባን ኪሙን መዋጮ አታጓድሉ ይላሉ።አፍሪቃን ለመርዳት የሚያቅማማዉ የአለም ባንክ ፕሬዝዳት ሮበርት ዘሊየክ ምጣኔ ሐብታችሁን አሳድጉ ይላሉ።


በፕሬዝዳት ሙጋቤ መንግሥት ላይ ማዕቀብ ካስጣሉት ዋና የጋራ ብልፅግና ሐገራት አንዷ የካናዳዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሎዉሬንስ ካኖን-እንሻረክ ባይ ናቸዉ።ከሁሉም በላይ ደግሞ የአለም አድራጊ ፈጣሪዋ የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር-ጂም ካርሰን ብዙ ይላሉ።ሁሉም አዲስ አበባ ናቸዉ።የአሜሪካ ዋና አለማ ግን ማርሻል እንደሚሉት ሁለት ነዉ።

እና ጉባኤዉ ነገ-ያበቃል።ከነገ-በሕዋላ የአፍሪቃ መሪዎች አዲስ አበባ መጡ፥ አወሩ ሔዱ እንጂ-ሰላም ለማስፈን፥ ግጭት ጦርነትን ለማስወገድ፥ ልማትን ለማስፈን ሁነኛ እርምጃ ወሰዱ ማለትን እንደናፈቅን-ሁለት ሺሕ አሥር አምና ሲሆን-ዤን ፔንግ ወይም ብጤዎቻቸዉ የሚሉትን ለመስማት ያብቃን።ነጋሽ መሐመድ ነኝ።እስኪ ለዚያ ያድርሰን።
Interv.Mit Pro.Ronald Marchal
Negash Mohammed


Audios and videos on the topic