የአፍሪቃ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤና አላማዉ | አፍሪቃ | DW | 02.07.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የአፍሪቃ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤና አላማዉ

የአፍሪቃ መሪዎች ሥር የሰደደዉን ምናልባትም አሰቸኳይ እልባት የሚያስፈልጓቸዉን የአሕጉሪቱን ችግሮች በይደር ይዘዉ-የማይሆን ለሚመሥለዉ ሁነት ቅድሚያ መስጠታቸዉ ሉደር ሻዶምስኪ እንደሚለዉ የቤቱ መሠረት ከመጣሉ በፊት ጣራዉን ለማዋቀር የመጣደፍ ያክል ነዉ።

የአፍሪቃ ሕብረት ሲመሠረት

የአፍሪቃ ሕብረት ሲመሠረት


የአፍሪቃ ሕብረት አባል ሐገራት መሪዎች አመታዊ ጉባኤ ትናንት አክራ-ጋና ተጀምሯል። ለሰወስት ቀን የሚዘልቀዉ ጉባኤ በሊቢያዉ መሪ ሙአመር ቃዛፊ ግፊት በቀረበዉ «የተባበሩት የአፍሪቃ መንግሥታት» በሚመሠረትበት ሐሳብ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ይነጋገራል። የተባበሩት አፍሪቃ መንግሥታት እንዲመሠረት ሐሳቡን ለመጀሪያ ጊዜ ያፈለቁት የነፃይቱ ጋና የመጀመሪያ ፕሬዝዳት ክዋሚ ንክሩማ ነበሩ። አሁን ንኩሩማ ሐገር የተሰበሰቡት የአፍሪቃ መሪዎች በሐሳቡ መስማማታቸዉ ግን ብዙ እንዳጠራጠረ ነዉ።የዶቼ ቬለዉ ባልደረባ ሉድገር ሻዶምስኪ እንደታዘበዉ ሐሳቡ ገና ካሁኑ ደቡብ አፍሪቃን ከመሳሰሉ ጠንካራ የሕብረቱ አባል ሐገራት ተቃዉሞ ገጥሞታል።የሻዶምስኪን ዘገባ ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

የአክራዉ ጉባኤ አብይ የመነጋገሪያ ርዕሥ የዳርፉር ዉዝግብ፣ የሶማሊያ ቀዉስ ወይም የድፍን አፍሪቃዊዉ ችግር-ቻጋር የሚቃለልበት ብልሐት አይደለም-የአፍሪቃ ፌደራላዊ መንግሥት ምሥረታ እንጂ።የአፍሪቃ መሪዎች ሥር የሰደደዉን ምናልባትም አሰቸኳይ እልባት የሚያስፈልጓቸዉን የአሕጉሪቱን ችግሮች በይደር ይዘዉ-የማይሆን ለሚመሥለዉ ሁነት ቅድሚያ መስጠታቸዉ ሉደር ሻዶምስኪ እንደሚለዉ የቤቱ መሠረት ከመጣሉ በፊት ጣራዉን ለማዋቀር የመጣደፍ ያክል ነዉ።

ከቀኝ ተገዢ የአፍሪቃ ሐገራት ነፃነትዋን ቀድማ የተቀዳጀችዉ የጋና የመጀመሪያ ፕሬዝዳንት ክዋሚ ንክሩማ አፍሪቃ የጋራ መንግሥት እንዲኖራት ሐሳቡን ባፈለቁበት ዘመን በአፍሪቃ ሐገራት ወይም መሪዎች መካካል የነበረዉ ልዩነት የዛሬዉን ያክል የሰፋ አልነበረም።በዚሕም ምክንያት ሐሳቡ ያኔ በርግጥ ራዕይ ይመስል ነበር።ዛሬ ተቃራኒዉ ነዉ-ሐቁ።የአፍሪቃ ችግሮች ከመቃለል ይልቅ በተባባሰበት፤ መንግሥታቷ ከመቀራረባቸዉ ይልቅ መራራቃቸዉ፤ ከመደጋገፋቸዉ ይብስ መናቆራቸዉ በጎላበት ባሁኑ ወቅት የሊቢያዉ ሽንጣቸዉን ገትረዉ የሚሟገቱለት ሐሳብ ከራዕይ ይልቅ ተምኔታዊ ነዉ-የሚመስል።

ቃዛፊ ባለፈዉ ጥር አዲስ አበባ ላይ ተሰይሞ በነበረዉ የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ለመካፈል ኢትዮጵያ ሲገቡ በደርዘን የሚቆጠሩ ዘመናይ አዉቶሞቢሎች እና የወርቅ ቡችሎች አስጭ ነዉ ነበር ።የኢትዮጵያ የጉምሩክ ተቆጣጣሪዎች የያዙት ዉድ ዕቃ ቃዛፊ ሐሳባቸዉ ተቀባይነት እንዲያገኝ ለአፍሪቃ መሪዎች ሊከፋፋሉ ያቀዱት ሥጦታ ነበር።

ቃዛፊ ዛሬ ለአፍሪቃ መሪዎች ሊያድሉ አክራ ይዘዉት የሔዱት ሥጦታ ካለ አይነቱ በዉል አልታወቀም። የቀድሞዉ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት በአፍሪቃ ሕብረት እንዲተካ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር በ1999 ሲርት ሊቢያ ላይ ተሰይሞ የነበረዉ የአፍሪቃ ልዩ የመሪዎች ጉባኤ ከወሰነ ወዲሕ የሚያቀነቅኑትን ሐሳብ የጉባኤዉ ዋና ርዕሥ ማድረጉ ግን በርግጥ አልከበዳቸዉም።

አብዮታዊዉ መሪ ሴኔጋልን የመሳሰሉ መልካም አስተዳደር የመሠረቱ ሐገራትን ድጋፍም አላጡም። ራሳቸዉ በመሠረቱት የሳሕል ሳሕራ መንግሥታት ሕብረት በኩል ተፅዕኖ ማሳረፍም አላቃታቸዉም። ያም ሆኖ በምጣኔ ሐብት የደረጁት ደቡብ አፍሪቃና ናጄሪያ፣ ዩጋንዳም ጭምር ሐሳቡን አልተቀበሉም።

ከካይሮ ሰሜናዊ ጫፍ እስከ ኬፕታዉን ደቡባዊ ጥግ ያሉትን ሐገራት የሚያተናብረዉ ማሕበር ለአፍሪቃ ችግሮች መወገድ ሁነኛ እርምጃ ባለመዉሰዱ «የወሬ መድረክ» በሚል ቅፅል ይተቻል። አፍሪቃ በሌሎች ብዙ ቅድሚያ መፍትሔ በሚያስፈልጋቸዉ ችግሮች እንደተተበተበች፤ መሪዎችዋ በተለያዩ ጉዳዮች እንደተለያዩ ነዉ።የጋዛፊ ሐገሳብ የተጨማሪ ልዩነት ምክንያት ይሆን? መንበሩን ሐንቡርግ-ጀርመን ያደረገዉ የአፍሪቃ ጥናት ተቋም የበላይ ዶክተር አንድርያስ ሜለር አይ-አዎ ብጤ ነዉ መልሳቸዉ።

«ባሁኑ ወቅት ቃዛፊን በግልፅ የሚቃወም ሐሳብ መንሰንዘሩ አጠራጣሪ ነዉ። የዚያኑ ያክል የአፍሪቃ ሕብረት አሁን ከያዘዉ በሌላ አቅጣጫ ይጓዝ የሚለዉን ለመቀበል የተዘጋጀም አይኖረም።ከዚሕ ይልቅ ከሆነ አግባቢ ሐሳብ ላይ ለመድረስ ነዉ የሚሞከረዉ።የአክራዉ ጉባኤ በመንግሥቱ ቅርፅ ላይ ይወያይ ይሆናል።ይሕ (የተባበሩት የአፍሪቃ መንግሥትን) ለመመስረት ሙከራ እየተደረገ ለመሆኑ ምልክት የሚሰጥ ነዉ።»

የዳርፉርን እና የሶማሊያን የመሳሰሉ ችግሮችን ለመፍታት የአፍሪቃ መሪዎች አለመቻል ወይም ብዙ አለመጣራቸዉ ለአፍሪቃ መጥፎ ገፅታ አሰጥቷታል።ይሕንን የአፍሪቃን ገፅታ ለዉጦ ክፍለ አሐጉሪቱን አንድ ለማድረግ የደቡብ አፍሪቃዉ የስልታዊ ጥናት ተቋም የበላይ ዶክተር ጃኪ ሲሊየር እንደሚሉት አብነቱ አካባቢያዊ ማሕበራትን ማጠናከር ነዉ።

«አፍሪቃ ለወደፊቱ እንድትዋሐድ የመጀመሪያዉ እርምጃ መሆን ያለበት እነዚሕን የተለያዩ አካባቢያዊ ምጣኔ ሐብታዊ ማሕበረሰባትን ይበልጥ ማቀራረብ ነዉ።በተጨባጭ እንደ አካባቢያዊ የምጣኔ ሐብት ማሕበረሰብ በመንቀሳቀስ ላይ ያሉት ኤኮዋስና ሳዴክ ብቻ ናቸዉ።ሌሎቹ ብዙዎቹ ባለዉ ሁኔታ ላይ ተፅዕኖ ለማሳረፍ ብዙም የማይፈይዱ የፖለቲካ ተቋማት ናቸዉ።»

የአክራዉ ጉባኤ ተሳታፊዎች ቃዛፊ እንደሚሉት የተባበሩት የአፍሪቃ መንግሥታትን ከመመሥረት ይልቅ ሲሊየር እንደሚያምኑት ያሉትን የአፍሪቃ ሕብረት ተቋማትን ለማጠናከር ነዉ የሚወስኑት።

«የአክራዉ ጉባኤ የሚደርስበት ዉሳኔ የአፍሪቃ ሕብረት የተለያዩ መዋቅሮች መጠናከር እንዳለባቸዉ ነዉ።የሕብረቱ ኮሚሽን፤ ምክር ቤት፤ ሌሎች በመመሥረት ላይ ያሉ የልዩ ልዩ ተቋማት መዋቅር እንዲጠናከሩ ነዉ።ሥለዚሕ እንደሚመስለኝ የጉባኤዉ የመጨረሻ ዉሳኔ ተቋማቱን ራሳቸዉን ማጠናከር ነዉ።እርግጥ አፍሪቃን ይበልጥ ማዋሐድ የሚለዉ ምኞት እንዳለ ነዉ።ይሕ ግን እንደ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ እቅድ የሚታይ ነዉ።»