የአፍሪቃ ሕብረትና ጀርመን | አፍሪቃ | DW | 12.07.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የአፍሪቃ ሕብረትና ጀርመን

የአፍሪቃን የተፈጥሮና የሰዉ ሐይል ሐብትን ለማልማት ደግሞ የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳት እንደሚያምኑት አፍሪቃ እራሷን ከርዳታ ተቀባይነት ወደ ንግድ ተሻራኪነት፥ ወደ ወረት መስሕብነት ቀስ በቀስ እየቀየረች ነዉ። በተለይ በወረት ፍሰት እና ወጣቶችን በማሰልጠኑ መስክ ጀርመን እንድትሳተፍ ዙማ ጋብዘዋል።

G

ሜርክልና ዙማ

ጀርመን ከአፍሪቃ ጋር ያላትን የንግድ፥ የመዋዕለ ንዋይ እና የትምሕርት ወይም የሥልጠና ግንኙነት አጠናክራ እንድትቀጥል የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳት ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ጠየቁ።ትናንት በርሊንን የጎበኙት ዙማ ከጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት ከአንጌላ ሜርክር ጋር ባደረጉት ዉይይት አፍሪቃ ቀስበቀስ ከተረጂነት ወደ ንግድ ተሻራኪነት እየተለወጠች ነዉ።የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት አንጌሌ ሜርክል በበኩላቸዉ አፍሪቃዉያን እራሳቸዉን ለማልማትና ለማበልፀግ የሚያደርጉትን ጥረት ጀርመንም አዉሮጳም ይደግፋሉ።ሁለቱ መሪዎች የግብፅን ፖለቲካዉ ቀዉስ አንስተዉም ተወያይተዋል።


«ሃያ-አንደኛዉ ምዕተ-ዓመት የአፍሪቃ ነዉ።» አሉ ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ትናንት-ከበርሊን፥ የጀርመንዋን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ካነጋገሩ በሕዋላ።አፍሪቃ ክፍለ ዘመኑን የአፍሪቃ የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች አሏት።የተፈጥሮ ሐብት፥ ሥልታዊ አቀማመጥ፥ እና ወጣት፥ ጠንካራ ሠራተኛ ሕዝብ።የአፍሪቃን የተፈጥሮና የሰዉ ሐይል ሐብትን ለማልማት ደግሞ የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳት እንደሚያምኑት አፍሪቃ እራሷን ከርዳታ ተቀባይነት ወደ ንግድ ተሻራኪነት፥ ወደ ወረት መስሕብነት ቀስ በቀስ እየቀየረች ነዉ።በለዉጡ ሒደት በተለይ በወረት ፍሰት እና ወጣቶችን በማሰልጠኑ መስክ ጀርመን እንድትሳተፍ ዙማ ጋብዘዋል።

«ባሁኑ ጊዜ እኛ እርዳታ ከመቀበል ወደ ዉረታ፣ ንግድ እና ወጣቶቻችንን ወደ ማሰልጠኑ እያዘገምን ነዉ።የጀርመን ኩባንዮች አፍሪቃ ዉስጥ ይበልጥ ሲሳተፉ ማየት እንፈልጋለን።ምክንያቱም አፍሪቃ ለወደፊቱ አመቺ የሆኑ በርካታ ዕድሎች ያላት፥ ይበልጥ የምትዳብር፥ ቁጥሩ በፍጥነት የሚያደግና ቀልጣፋ ወጣት ሕዝብ ያላት አሐጉር ናትና።»

ዙማ እንደሚሉት አፍሪቃዉያን በተለይ በኤሌክትሪክ ሐይል እና በመትራንስፖርቱ መስክ ከጀርመኖች እዉቀትና ሙያ መቅሰም ይፈልጋሉ።የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልም የእንግዳቸዉን ሐሳብ ይጋራሉ።ሜርክል እንዳሉት የአፍሪቃ መበልፀግ ለጀርመን በተናጥል፥ ለአዉሮጳ በጥቅል በጣም ጠቃሚ ነዉ።ሁለቱ አሐጉራት ጎረቤቶች ናቸዉና።

«የአፍሪቃ መበልፀግ ለኛ ልዩ ትርጉም አለዉ።እኛ አዉሮጳና እና አፍሪቃ ጎረቤታሞች ነን።በዚሕም ምክንያት የአፍሪቃ ጥሩ ልማት ለሁለታችንም ጠቃሚ ነዉ።»

Joachim Gauck und Nkosazana Dlamini-Zuma 18.03.2013

ዙማ እና ጋ ዉክ

ጀርመን በቅርቡ ሐምሳኛ ዓመቱን ላከበረዉ ለአፍሪቃ ሕብረት ለሰጠችዉ ድጋፍ እና እገዛ የሕብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝዳት አመስግነዋል።ሐምሳ አራት አባል ሐገራትን የሚያስተናብረዉ የአፍሪቃ ሕብረት ከአዉሮጳ ሕብረት ጋር ተመሳሳይ ቅርፅና መዋቅር አለዉ።የገንዘብ አቅሙ ግን ዉስን በመሆኑ የለጋሾች ድጋፍ አሁንም ያስፈልገዋል።

ሕብረቱ ለመክፈት ያቀደዉን የመላዉ አፍሪቃ ዩኒቨርስቲን ለመርዳት ጀርመን ቃል ገብታለች። ግንባታዉ ቅርቡ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀዉን የአፍሪቃ የሠላምና የፀጥታ ምክር ቤት ሕንፃን ወጪ የሸነችዉም ጀርመን ናት።መራሒተ መንግሥት ሜርክል መንግሥታቸዉ ለሕብረቱ የሚሰጠዉ ድጋፍ ወደፊትም እንደሚቀጥል ለዙማ ቃል ገብተዉላቸዋል።

«ብዙ ችግሮች ሥላሉ የተጣለበወት ሐላፊነት ቀላል እንዳልሆነ እናዉቃለን።ሥለዚሕ እርስዎን፥ ሥራዎንና የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽንን አቅማችን በፈቀደ መጠን ለደገፍ እንፈልጋለን።»

የግብፅ ፖለቲካዊ ቀዉስ ሁለቱ መሪዎች ከተነጋገሩባቸዉ ጉዳዮች አንዱ ነበር።የግብፅ ጦር የሐገሪቱን ተመራጭ ፕሬዝዳት መሐመድ ሙርሲን ከሥልጣን ማስወገዱን በመቃወም የአፍሪቃ ሕብረት ግብፅን ከአባልነት አግዷል።ዙማ እንዳሉት እገዳዉ የሚነሳዉ ግብፅ ተመራጭ ፕሬዝዳት እና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ሲኖራት ነዉ።

«ግብፅ ወደነበረበችበት ተመልሳ የተመረጠ ወይም በሕገመንግስታዊ ሒደት ሥልጣን የሚይዝ አመራር ከመሠረተች የአፍሪቃ ሕብረት ፍላጎት ይሟላል።»

ሜርክል በበኩላቸዉ ግብፅ ዉስጥ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓት ዳግም ለመመሥረት የሚደረገዉ ጥረትና ሒደት የሐገሪቱ ፖለቲከኞች በሙሉ የሚያሳትፍ መሆን አለበት።

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ
Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች