የአፍሪቃ ልማት እና የጀርመን ምክር ቤት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 11.05.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የአፍሪቃ ልማት እና የጀርመን ምክር ቤት

የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ እንደራሴ ቲሎ ሆፐ እስካሁን እርዳታዉ የተፈለገዉን ዉጤት ባለማምጣቱ እርዳታ ተቀባዮች ብቻ መወቀሳቸዉን አልወደዱትም።ሆፐ ጀርመንም ሆነች ሌሎቹ አበዳሪ ሐገራት የራሳቸዉንም ስሕተት ማየት አለባቸዉ-ባይ ናቸዉ።

Bundestag

Bundestag


የጀርመን ሕግ-መምሪያ ምክር ቤት Bundestag አባላት ሐገራቸዉ ለአፍሪቃ በምትሰጠዉ ርዳታ እና ሥለ አፍሪቃ በምትከተለዉ ፖለቲካዊ መርሕ ላይ ዛሬ እየተከራከሩ ነዉ።ጀርመን የአዉሮጳ ሕብረትን እና የቡድን ሥምንትን የፕሬዝዳትነት ሥልጣን በያዘችበት ባሁኑ ወቅት ምክር ቤቷ ሥለ አፍሪቃ የሚያደርገዉ ክርክር እና የሚደርስበት ዉሳኔ በጀርመን ብቻ ሳይሆን በበለፀገዉ አለም መርሕ ላይም ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳረፉ አይቀርም።የዶቼ ቬለዋ ሞኒካ ዲትሪሽ ያዘጋጀችዉን ዘገባ ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

የበለፀጉት ሐገራት ሥለ አፍሪቃ የሚከተሉት መርሕ የእርዳታ ሰጪ-ተቀበባይ ወይም የበታች-የበላይነት ከመሆን ተላቅቆ የአቻ-ላቻ አይነት እንደሚሆን መነገር ከጀመረ-በርግጥ አመታት ተቆጠረ። ይሕን መርሕ ይበልጥ ማጠናከር ገቢር ማድረግ ቢያንስ ጀርመኖች አሁን በጣም አስፈላጊ መስሎ ሳይታያቸዉ አልቀረም።

ጀርመን ከአፍሪቃ ጋር ሥለ ገንዘብ ርዳታ፤ ሥለ ልማት መርሐ ግብር ሥለ ፖለቲካ ግንኙነት የምታደርገዉ ግንኙነት እና ድርድር በሙሉ በጥንቃቄ ግን በእኩልነት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን የግድ የሚሏት ብዙ ምክንያቶች አሉ።የአፍሪቃ ሐገራት ከአዉሮጳ ጋር የቅርብ ትስስርና ግንኙነት ያላቸዉ ሳይቀሩ በእስካሁኑ የለጋሽ ሐገሮች በቅድመ ግዴታ የታጠረ መርሕ ብዙ አለመርካታቸዉ አንዱ ነዉ።

በምጣኔ ሐብት እየጎለበቱ የመጡት ሕንድና ቻይና እንደ ነባሮቹ የምዕራብ ለጋሾች ቅድመ-ሁኔታ ሳያበዙ አፍሪቃን መርዳት እና የአፍሪቃን ገበያ መሻማታቸዉ ደግሞዉ ሌላዉ ትልቁ ምክንያት ነዉ።የዛሬ ወር እዚሁ ጀርመን ሐይሊገዳመ የሚሰየመዉ የቡድን ስምንት አባል ሐገራት የመሪዎች ጉባኤ ከሚነጋገርባቸዉ ርዕሶች አንዱ ሥለ አፍሪቃ የሚከተሉት መርሕ ነዉ። የጀርመን የልማት እና ተራድኦ ሚንስትር ሐይደማሪ ቪቾሬክ-ሶይል ዛሬ ለምክር ቤታቸዉ እንደነገሩት የቡድን ስምት ጉባኤ ጀርመንም ሆነች ሌሎቹ በኢንዱስትሪ የበለፀጉት ሐገራት የአፍሪቃ አቻ ወዳጅ መሆናቸዉ በግልፅ ማሳየት አለበት።

የዚያኑ ያክል ቪቾሬክ ሶይል ለምክር ቤት እንደራሴዎቹ እንደነገሩት የአፍሪቃ መንግሥታት ድሕነትን የመዋጋት ሐላፊነታቸዉን መቀበል አለባቸዉ።

«እዚያ ለልማት የሚዉለዉ ገንዘብ ከየለጋሹ (ሐገር) ሕዝብ የተሰበሰበ ግብር ነዉ።ከሌላ ከዉጪ ሐገር የሒሳብ ቁጥር የተገኘ አይደለም።ሥለዚሕ ከጥሬ አላባዎች የሚገኘዉ ሐብት ሐገርን መልሶ ለመገንባት መዋል ይገባዋል። በዉጤቱም፣ ለምሳሌ የኮንጎዉ ለየሐገሩ ሕዝብ፣ ለያንዳዱ ቤተሰብ በትክክል መዳረስ መቻል አለበት።»

የበለፀጉት ሐገራት ለአፍሪቃ የሚሰጡትን የልማት እርዳታ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር እስከ 2010 በእጥፍ ለመጨመር ከዚሕ ቀደም ቃል ገብተዉ ነበር።እስካሁን ግን ሙሉ በሙሉ ገቢር አልሆነም። ሚንስትር ቪቾሪክ-ሶይል እንደሚሉት ያ ቃል መከበር አለበት ብለዋል።FDP በሚል የጀርመንኛ ምሕፃረ-ቃል የሚጠራዉ የለዘብተኛዉ የነፃ ዲሞክራቲክ ፓርቲ እንደራሴ ካርል አዲክስ የሚንስትሯን ሐሳብ ይጋራሉ።

አዲክስ እንደሚሉት የሰሜን አፍሪቃ ሐገራት በአንፃራዊ መመዘኛ ሲታይ የተሻለ ደረጃ ላይ ናቸዉ።ከሰሐራ-በስተ ደቡብ ያሉት ግን ብዙ እርዳታ ይሻሉ።በዚሕም ምክንያት የሚሰጠዉ እርዳታ ከየተረጂዉ ሐገር ተጨባጭ ሁኔታ ጋር መጣጣም አለበት ባይ ናቸዉ።-አዲክስ።

«--ሥለዚሕ ጀርመን የምታደርገዉ የልማት ትብብር ከያንዳዱ ሐገር እዉነታ ጋር የሚጣጣም መሆን አለበት።ለየትኛዉ ሐገር የበጀት ድጎማ ማድረግ እንዳለብን በትክክል ማጥናት፤ እና አተኩረን ማየት አለብን።እነዚያ (ተረጂዎቹ) ደግሞ ለየሕዝባቸዉ አስተማማኝ፣ ሐላፊነት የሚሰማቸዉ መንግሥታት መሆን አለባቸዉ።»

የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ እንደራሴ ቲሎ ሆፐ እስካሁን እርዳታዉ የተፈለገዉን ዉጤት ባለማምጣቱ እርዳታ ተቀባዮች ብቻ መወቀሳቸዉን አልወደዱትም።ሆፐ ጀርመንም ሆነች ሌሎቹ አበዳሪ ሐገራት የራሳቸዉንም ስሕተት ማየት አለባቸዉ-ባይ ናቸዉ።

«በቅኝ አገዛዝ ከተፈፀመዉ ታሪክ የተወረሰዉ፣ አለም አቀፉ የገዘብ ድርጅት የሚያቀርበዉ ግዴታ መርሕ ያስከተለዉ አጓጉል ዉጤት፤ ያልተሳካዉ የነፃ ምጣኔ-ሐብት መርሕ፤ ፍትሕ አልባዉ ብድር በሙሉ ለዉድቀቱ እንደ ምክንያቶች ናቸዉ።የበለፀጉት ሐገራት ለገበሬዎች የሚሰጡት ድጎማ በአዳጊዎቹ ሐገሮች ላይ ያሳደረዉ ተፅዕኖ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ እየተዋቀ እንደዘበት ነዉ የታለፈዉ።የአዉሮጳ ሕብረት የሚሰጠዉ ቀጥተኛ እርዳታ በቅራኔ የተሞላ ነዉ።ባንድ በኩል አዳጊ ሐገሮችን እያለማ በሌላ በኩል የሚያቆረቁዝ ነዉ።»

የምክር ቤቱ ክርክር እንዲሕ እያለ ቀጠለ።