የአፍሪቃ ልማት ባንክና አዲስ ፕሬዚደንት ፍለጋው | ኤኮኖሚ | DW | 21.07.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአፍሪቃ ልማት ባንክና አዲስ ፕሬዚደንት ፍለጋው

የአፍሪቃ ልማት ባንክ አስተዳዳሪዎች ዛሬና ነገ ቱኒዝ ላይ ተሰብስበው አዲሱን የተቋሙን ፕሬዚደንት ለመምረጥ እንደገና ይጥራሉ።

ከሥምንት ሣምንታት በፊት ናይጄሪያ ርዕሰ-አተማ አቡጃ ላይ ተካሂዶ በነበረው ጠቅላይ ጉባዔ በመጨረሻ የቀሩት ሁለት ዕጩዎች አስፈላጊውን የብዙሃን ድምጽ ሊያገኙ ባለመቻላቸው ምርጫው መክሸፉ ይታወሣል። በወቅቱ የሚፈለገው ከአሥር ዓመታት በፊት በመጀመሪያው ምርጫ እንደታየው አንድን የከሰረ ተቋም የሚጠግን ፕሬዚደንት አይደለም። ምክንያቱም በዚሁ ሥልጣን ላይ የቆዩት የሞሮኮው ተወላጅ ኦማር ካባጅ ተቋሙን የሚሰናበቱት ይዞታውን በሚገባ አሻሽለው መሆኑ ነው።

የአፍሪቃ የልማት ባንክ በነጻነት ማግሥት ከ 41 ዓመታት በፊት ሕያው ይሆናል። ሊቋቋም የበቃውም የወጣቶቹ አፍሪቃውያን መንግሥታት መሪዎች የክፍለ-ዓለሚቱን ዕድገት ለማራመድ ራሳቸው የሚቆጣጠሩትንና በጀት የሚቆርጡለትን ባንክ መመስረት በመፈለጋቸው ነበር። ይሁን እንጂ የአፍሪቃው የልማት ባንክ እንደ ብዙዎች የክፍለ-ዓለሚቱ ፕሮዤዎች ሁሉ ችግር ላይ ለመውደቅ ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም። ግን በዚሁ የተነሣ ደግሞ ጨርሶ ሕልውናውን እስከማጣት አልደረሰም።

አፍሪቃውያኑ መንግሥታት ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ ባንኩን ለሌሎች ክፍለ-ዓለማት ከከፈቱ 23 ዓመታት ገደማ አልፈዋል። ዛሬ በልማት ባንኩ የሚሳተፉት የአውሮፓ፣ የአሜሪካና የእሢያ መንግሥታት አርባ በመቶ የመዋዕለ-ነዋይና የድምጽ ድርሻ አላቸው። ለአፍሪቃ ከዓለም ባንክ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ጠቃሚ በሆነው የልማት ተቋም ተግባር ላይ ጀርመንም በፌደራሉ የልማት ተራድኦ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ባለሥልጣን በኡሺ አይድ አማካይነት የምትወከለው አንዷ አገር ናት።

የአፍሪቃው ባንክ ጀርመን ከክፍለ-ዓለሚቱ ጋር ለምታካሂደው የልማት ትብብር ጠቃሚ መሣሪያ እንደሆነ በጀርመን ቴክኒካዊ ተራድኦ ድርጅት GTZ ለአፍሪቃ ሃላፊ የሆኑት የምጣኔ-ሐብት ባለሙያ ሄልሙት አሸ ይናገራሉ። በባለሙያው አባባል፤
“የአፍሪቃ ልማት ባንክ ከዓለም ባንክ ሲነጻጸር በተወሰኑ አፍሪቃን በሚመለከቱ የፊናንስ ተግባራትና የአሠራር ሂደቶች ለጀርመን የቀረበና የተመቸ ነው። ሠራተኞቹ 80 በመቶ አፍሪቃውያን በመሆናቸውም ቀጥተኛው ግንኙነት የተለየ ጠቀሜታ ይኖረዋል።”

የአፍሪቃ የልማት ባንክ ለብዙ ዓመታት የጎደፈ ዝና ይዞና ታማኝነት አጥቶ መቆየቱም ሌላው አጅቦት የኖረ ሃቅ ነው። እስከ አሥር ዓመታት በፊት ድረስ ባንኩ በሥልጣን ብልግና፣ በሙስናና በብቃት ጉድለት የሚታማ እንደነበር የሚያስታውሱት የዘርፉ ጠበብት ብዙዎች ናቸው። ይህን እንጂ የእስካሁኑ ፕሬዚደንቱ ኦማር ካባጅ በዚሁ ጊዜ ተቋሙን ከወደቀበት እንደገና ሊያነሱት በቅተዋል።

የአፍሪቃ የልማት ባንክ ዛሬ ከፊናንስ ይዞታው አንጻር ብቻ ሣይሆን በአጠቃላይ በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የዓለም የምጣኔ-ሐብት አዋቂዎች እየመሰከሩ ነው። ካባጅ የባንኩን መዋቅራት ጠበብ አድርገው በመጠገን የፖለቲካውን ተጽዕኖም ማስወገዱ ተሳክቶላቸዋል። የልማት ባንኩ ከዚያን ወዲህ ለአፍሪቃ መዋቅራዊ ዕድገት መዋዕለ-ነዋይ እንዲየፈላልግና እንዲያቀርብ የተቋቋመበትን ዓላማ በመወጣቱ ተግባር በሚገባ ማተኮር ችሏል። በአንዳንድ መስኮችም፤ ለምሳሌ በእርሻ ልማት ዘርፍ ከዓለም ባንክ ሲነጻጸር የበለጠ ጥንካሬን እያሳየ ነው።
በተለይ ይሄው የእርሻ ልማት መስክ በሌሎች የገንዘብ ተቋማት ዘንድ ባለፉት ዓመታት ትኩረት እያጣ ነው የመጣው። የአፍሪቃ የልማት ባንክ አሁን ከዚሁ በተጨማሪ ደግሞ በውሃ ሐብት ዘርፍ ጠቃሚና ሥልታዊ ቦታን እየያዘ በመሄድ ላይ ይገኛል። ጥያቄው የሞሮኮው ተወላጅ ፕሬዚደንት ኦማር ካባጅ ባለፈው አሥር ዓመት ያስቀመጡትን በጎ አርአያ ተከትሎ ተግባሩን ቀጣይ ሊያደርግና ሊያስፋፋ የሚችል ተተኪ መገኘቱ ላይ ነው።

ሃላፊነቱን ለመረከብ ተሥፋ አላቸው ተብለው የሚገመቱት ሁለት ባለሥልጣናት የሩዋንዳው የገንዘብ ሚኒስትር ዶናልድ ካቤሩካና ናይጄሪያዊው ኦላቢሲ ኦጉንጆቢ ናቸው። ሁለቱም ብቁ መሆናቸው ሲነገር ካቤሩካ አሜሪካንና አውሮፓን የመሳሰሉት አፍሪቃዊ ያልሆኑት ወገኖች የብዙሃን ድጋፍ አላቸው ነው የሚባለው። የአፍሪቃን የልማት ባንክ ከ 25 ዓመታት በላይ ሲያገለግሉ የቆዩት ኦጉንጆቢ በአንጻሩ በአፍሪቃውያኑ ይበልጥ የሚመረጡት ዕጩ ናቸው። ያም ሆነ ይህ የሚመረጠው አዲስ ፕሬዚደንት ተግባሩን በሚገባ እንዲያራምድ ከአጠቃላዩ የባንኩ ተሳታፊዎች የድምጽ ድርሻ የብዙሃኑን ድጋፍ ብቻ ሣይሆን የአፍሪቃውያኑን ተስማሚነት ማግኘትም ያስፈልገዋል።