የአፍሪቃ ልማትና ዓለምአቀፉ ንግድ | ኤኮኖሚ | DW | 30.03.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአፍሪቃ ልማትና ዓለምአቀፉ ንግድ

አፍሪቃ በተወሰነ ቅድመ-ሁኔታም ቢሆን ለዓለምአቀፉ ንግድ ገበዮቿን ሙሉ በሙሉ ካልከፈተች የረባ የኤኮኖሚ ዕድገት ሊከተል አይችልም። ይህን ከእሢያ ዕርምጃ ጋር በማነጻጸር የሚሉት በዚህ ጀርመናዊው ፕሮፌሰር ሮልፍ ሆፍማየር ናቸው።

default

በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም በብዙዎች መንግሥታት ዘንድ እስካሁን እየተለመደ ሆኖ የመጣው የአገርን የዕድገት ዕጣ በልማት ዕርዳታ ገንዘብ ላይ ጥገኛ አድርጎ መኖሩ ነው። ክፍለ-ዓለሚቱ ዛሬም ከድህነት፣ ከረሃብ፣ ከተመጽዋችነትና ኋላ ቀርነት ገና አልተላቀቀችም። ለአሠርተ-ዓመታት የፈሰሰው የልማት ዕርዳታ እንግዲህ የታሰበውን ዕርምጃ አላስከተለም። ምንድነው ምክንያቱ? ምን መቀየርስ ይኖርበታል? እንደ ፕሮፌሰር ሮልፍ ሆፍማየር ትልቁ ችግር መንግሥታቱ በልማት ዕርዳታ ላይ ጥገኛ መሆኑን መላመዳቸው ነው።

“ያለፉትን አሠርተ-ዓመታት መለስ ብለው ሲያስተውሉ ጉዳዩ አስቸጋሪ መሆኑ ጎልቶ ነው የሚታየው። በአፍሪቃ የራስን የኤኮኖሚ አቅም አሁንም በብቃት ገቢር ለማድረግ አልተቻለም። በአብዛኞቹ አገሮች የሚያሳዝን ሆኖ በልማት ዕርዳታ ላይ ጥገኛ መሆኑ የተለመደ ነገር ሆኗል። ስለዚህም እኔ የምለው የአፍሪቃ መንግሥታት የራሳቸውን ኤኮኖሚ ወደፊት በማራማድ በዓለምአቀፍ ደረጃ ለፉክክር እንዲበቁ ይበልጥ መጣር አለባቸው ነው”

እርግጥ ሆፍማየር የአፍሪቃ ገበዮችና ኤኮኖሚ ከበለጸጉት ሃገራት ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ገደቡ መኖሩን ስህተት አድርገው አይመለከቱትም።
“ለአፍሪቃ የጥበቃው ገደብ በተወሰነ መጠን ያስፈልጋታል። በሌላ በኩል ችግሩ መንግሥታት በልማት ዕርዳታ ላይ ጥገኛ ሆኖ መኖሩን እየለመዱት ነው የመጡት። ጉዳዩን ከእሢያ በማነጻጸር ከታሪክ ሂደት አኳያ ብንመለከት ጥልቅ ልዩነት መኖሩ ጎልቶ የሚታይ ነው። ከሃምሣ ዓመታት በፊት አብ’ዛኞቹ የእሢያ አገሮች ከአፍሪቃው’ኑ ከሞላ ጎደል በተመሳሳይ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነበሩ። ዛሬ ልዩነቱ ምን ያህል እንደሆነ ሁላችንም እናውቀዋለን”

የፖለቲካ ሣይንስና የምጣኔ ሐብት ባለሙያው ጀርመናዊ እንደሚሉት ዛሬ አፍሪቃን በራስ መቻል አቅጣጫ የሚያራምድ መዋቅራዊ ተሃድሶ ማድረጉ ግድና አጣዳፊም ጉዳይ ነው። ሆፍማየር አፍሪቃ ለዓለምአቀፉ ንግድ ገበዮቿን ጨርሳ መክፈት እንደሚኖርባትም ያስገነዝባሉ። በምሁሩ አስተሳሰብ እንዲህ ብቻ ነው ክፍለ-ዓለሚቱ የረባ የኤኮኖሚ እመርታ ልታደርግ የምትችለው።

“አባባሌ የተሳሳተ ትርጉም እንዳይሰጠው ላሳስብ እፈልጋለሁ። አሁን ድንገት ተነስቼ ከዛሬ ወደነገ ለአፍሪቃ በአርሻ ልማትም ሆነ ብዙዎቹ ባላቸው በቀላል ኢንዱስትሪ ደረጃ የጥቅም ጥበቃው ገደብ እንዲነሣ ለመጠየቅ አልፈልግም። በአፍሪቃ የኤኮኖሚ ፖሊሲ ሃላፊነት ያለባቸው ወገኖች ከዓለም የምጣኔ-ሐብት ይዞታና የንግድ ግንኙነት ሁኔታ ጋር መርሃቸውን ማጣጣም ይኖርባቸዋል። የፉክክር ግፊት መኖሩንም መቀበል አለባቸው። ይሄ በመሠረቱ በየውይይቱ የማይነሣ ነጥብ ነው። ሆኖም ለብዙሃኑ ፍጆተኛ ሲባል በቂ ምርት እስከሌለና የምርቱ ዋጋም በንጽጽር ውድ ከሆነ ጉዳዩ ሊታሰብበት ይገባል። አፍሪቃ ውስጥ የእርሻ ምርት በንጽጽር ውድ በሚሆንበት ጊዜ በታላላቅ ከተሞች የሚገኘው ፍጆተኛ ነው ተጎጂ የሚሆነው። ስለዚህም የምግብ ምርት ከአውስትራሊያ ወይም ከካናዳ በርካሽ ቢቀርብለት አይጠላም”

የአፍሪቃ አገሮች ገበዮቻቸውን ጨርሰው የመክፈታቸው ጉዳይ ጥቂትም ቢሆን ማሳሰቡ አይቀርም። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያን በመሳሳሰሉት በአብዛኞቹ የአፍሪቃ አገሮች ከ 80 በመቶ የሚበልጠው ሕዝብ የሚኖረው በገጠር አካባቢዎች ነው። የኤኮኖሚው ዋና ምሶሶም የእርሻ ልማት መሆኑ መዘንጋት የለበትም። እና የምግብ ምርት በገፍ ከውጭ ቢገባ በድሃው አርሶ-አደር ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ የማይቀር ነው።

“አፍሪቃን ለዚህ ያደረሰው ለረጅም ጊዜ የራስን ገበዮች በማገዱ ከለላ መኖሩ ነው። ያለፉትን አሠርተ-ዓመታት መለስ ብለን ብንመለከት በ 1964 ዓ.ም. ይመስሰኛል ያኔ የቅኝ አገዛዙን ዘመን በማጤን አፍሪቃውያኑ አገሮች ወደ አውሮፓ ገበዮች እንዲዘልቁ ልዩ አስተያየት ይደረጋል። ይህም ትክክለኛ ነገር ነው። ጨርሶ ትችት ለመሰንዘር አልፈልግም። በጊዜው ተገቢ ነበርና። ግን አሁን ጉዳዩን እንደገና ሲመለከቱት ለአፍሪቃ አገሮች የከፈተው ዕድል የለም”
በቀላሉ ለማረጋገጥ የሚቻለው ባለፉት አራትና አምሥት አሠርተ-ዓመታት የአፍሪቃ የዓለም ንግድ ድርሻ እያቆለቆለ መምጣቱን ነው።
“በተመሳሳይ ጊዜ የእሢያ አገሮች በሰፊው ነው የወደፊት ዕርምጃ ያደረጉት። እዚህ ላይ በዓለም ንግድ ተሳትፎ መጠን አፍሪቃ ከእሢያው ሲነጻጸር የተለየ ገጽታ ነው የሚታይባት። እነርሱ በሰፊው ነው የወደፊት ዕርምጃ ያደረጉት። የእሢያ አገሮች በነዚሁ ዓመታት እንግዲህ የአፍሪቃን የገበያ ድርሻ እየነጠቁ መምጣታቸው በግልጽ የሚታይ ነው”

በወቅቱ በዓለምአቀፍ ደረጃ ብዙ እያነጋገረና እያከራከረ ያለው አንዱ የልማት ጉዳይ የውጭ ባለሃብቶች አፍሪቃ ውስጥ በሰፊው ለም መሬት መግዛት ወይም መከራየት የያዙበት ሂደት ነው። ሆፍማየር እንደሚሉት ጉዳዩ እንዳያያዙ ለበጎ ወይም ለክፉም ሊሆን ይችላል።

“እንዴት እንደሚካሄድ በተናጠል መመልከት ያስፈልጋል። በመሠረቱ ጠቃሚም ጎጂም ብዬ ለመናገር አልችልም። ለማንኛውም በተናጠል ከነዚህ የውጭ ባለሃብቶች ጋር የሚደረጉትን ውሎች ማጤን አስፈላጊ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ በምን ግልጽነትና ሃቀኝነት ለሕዝቡ እንደሚገለጽ መታየት ይኖርበታል። ስለ ኢትዮጵያ ሳስብ መንግሥት በራሱ የገጠር ነዋሪዎች ትከሻ ከሳውዲት አረቢያ፣ ከተባበሩት አረብ ኤሚሮች ወዘተ. ባለሃብቶች ጋር ውሉን የሚፈራረም ነው የሚመስለኝ” በመጨረሻ እንደማንኛውም የንግድ ጉዳይ ሁሉ ቁም ነገሩ ያለው ከፖለቲካ አያያዙ ባሕርይ ላይ ይሆናል። ጥያቄው ትክክል ነው አይደለም ሣይሆን ለሁሉም ወገን በሚጠቅም መንገድ መጠናቀቁ ላይ ነው”

ሆፍማየር እንደሚያስገነዝቡት በመሠረቱ በብዙ የአፍሪቃ አገሮች በቂ መሬት አለ። ግን ሰዎች ይኖሩበታል። እናም በሚቋቋመው እርሻ ላይ መሥራት እንዲችሉ ወይም ወይም በአግባብ ሌላ ቦታ እንዲሰፍሩ መደረጉ ግድ ነው። ይህም ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንጂ በሃይል ሊካሄድ አይገባውም።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ