የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ | ኢትዮጵያ | DW | 02.07.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ

በሲርት ሊብያ ጉባዔ የተቀመጡት ከግማሽ የሚበልጡት የአፍሪቃ ህብረት አባል ሀገሮች መሪዎች በሶማልያ ጸጥታ፡ በባህር ላይ ውንብድና እና በአህጉሩ ውህደት ጉዳይች ላይ ዛሬም ውይይታቸውን ቀጥለዋል።

default

በአህጉሩ ኤኮኖሚያዊው መረጋጋት ማስገኘት የሚቻልበትም ሀሳብ ከውይይቱ አጀንዳዎች መካከል አንዱ ሲሆን፡ ለዚሁ ገሀዳዊነት የአስተናጋጅዋ ሀገር የሊብያ መሪ ኮሎኔል ሞአመር ጋዳፊ ካሁን ቀደም ያቀረቡት የተባበረው የአፍሪቃ መንግስት ምስረታ ሀሳባቸው ዘላቂውን መፍትሄ ያስገኛል ባይ ናቸው። ይህን አስተሳሰባቸውን ግን ሁሉም አቻዎቻቸው አይጋሩትም። የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ

የሊብያ መሪ ኮሎኔል ጋዳፊ በመከላከያው፡ በንግዱና በውጭ ግንኙነቶጭ ረገድ ሀምሳ ሶስቱን የህብረቱን አባል ሀገራትን ወክሎ መናገር የሚችል አንድ አካል እንዲቋቋም ነው የሚጥሩት። እርግጥ፡ አንድ የተባበረ የአፍሪቃ መንግስት ይመስረት ባሉት ሀሳባቸው ዙርያ ህብረቱ ከተቋቋመ ወዲህ ክርክሩ እንደቀጠለ ሲሆን፡ በዚሁ ዕቅዳቸው ዙርያ ሶስት የተለያዩ ሀሳቦች እንደሚሰሙ በጀርመን የላይፕሲህ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪቃ ጉዳዮች ክፍል ፕሮፌሰር ኡልፍ ኤንግል አስረድተዋል።

« ባሁኑ ጊዜ በዚሁ ሀሳብ ላይ የሚከራከሩ ሶስት ቡድኖች አሉ። ሊብያና የአፍሪቃ ህብረት ዓመታዊ የአባልነት መዋጮአቸውን የምትከፍልላቸው ሀገሮች አንድ የተባበረው አፍሪቃ መንግስት ምስረታ ሀሳብን ይደግፋሉ። ሌላው የአፍሪቃ ህብረት ስራውን በሚገባ ማከናወኑን በማጠያየቅ፡ ህብረቱ እንዲያከናውናቸው ከታሰቡት የፖለቲካ ተሀድሶዎች፡ ማለትም፡ ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን በተመለከተ እስካሁን አስር ከመቶውን እንኳን በተግባር አልተረጎመም በሚል ሂስ ይሰነዝራል። ይህንኑ ሂስ በተመለከተ ሶስተኟው ቡድን ደግሞ ህብረቱ ቴክኒካዊ ችግሮች እንዳሉት በመጠቆም፡ የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽንን በማጠናከር ወደ አፍሪቃ ህብረት ባለስልጣን በመለወጥ፡ ከአውሮጳ ህብረት ጋር የሚነጻጸር ስልጣን የሚኖረው አካል እንዲቋቋም ይፈልጋል። »

በአህጉሩ ትልቋ የኤኮኖሚ ኃይል የሆነችው ደቡብ አፍሪቃ፡ እንዲሁም፡ ናይጀሪያና አንጎላን የመሳሰሉ ትልቆቹ ነዳጅ ዘይት አምራች ሀገሮች የጋዳፊን ሀሳብ በመቃወም፡፡ከውህደቱ በፊት ያካባቢ ድርጅቶች የሚጠናከሩበትን ሀሳብ አጉልተዋል።

ሌላው በሊብያው ጉባዔ ላይ የሚነሳው የሶማልያ ጊዚያዊ የጸጥታ ሁኔታና ህብረቱ በዚያ ያሰማራው ሰላም አስከባሪ ኃይል የሚጠናከርበት ጉዳይ ነው። አባል ሀገራት ጓዱን የሚጠናክርበትን ውሳኔ ያሳልፉ ይሆናል በሚል ዲፕሎማቶች ተስፋቸውን ገልጸዋል። ይሁንና፡ ይህ ብቻውን በሶማልያ የሚካሄደውን ውዝግብ ማብቃቱን የላይፕሲህ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪቃ ጉዳዮች ክፍል ፕሮፌሰር ኡልፍ ኤንግል ገልጸዋል።

« ጉባዔው የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች የተወሰኑ ነው የሚሆኑት። ምክንያቱም በወቅቱ የሚታዩት ችግሮች በዚያ መፍትሄ አያገኙም፤ ምንም እንኳና የአፍሪቃ ህብረት ቁጥር ከፍ ቢልም፡ በሶማልያ የሚፋለሙትን የጦር ባላባቶች ውጊያ ለማብቃት አይችልም፡ አሁን ባለው ጦር መጠን ዘላቂ መፍትሄ ይገኛል ተብሎ አይታሰብም። »

በሊብያ የአፍሪቃ ህብረት ጉባዔ በዋና ጸሀፊው አምር ሙሳ የተወከለው የዐረቡ ሊጋ ለሶማልያ የሽግግር መንግስት ድጋፍ ሊሰጥ የሚችልበት ሁኔታ መኖሩም ተሰምቶዋል። ይሁንና፡ ፕሮፌሰር ኤንግል የዐረቡ ሊጋ ድጋፍ የሚያስገኘውን ውጤት ማጠያየቃቸው አልቀረም።

አርያም ተክሌ

ተክሌ የኋላ