1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃውያን የጀርመን ቪዛ የማግኘት ጠባብ እድል

ማክሰኞ፣ ሰኔ 12 2010

ወደ ጀርመን ለመምጣት ቪዛ የሚጠይቁ አፍሪቃውያን ብዙ ችግር ያጋጥማቸዋል።  ዶይቸ ቬለ በአፍሪቃ ያሉ የጀርመን ኤምባሲዎች የቪዛ አሰጣጥን ሂደት በተመለከተ ያካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው፣ ከየአምስቱ የቪዛ መጠየቂያ ማመልከቻዎች መካከል አንዱ ተቀባይነት አያገኝም። ይህ ከሌሎች አህጉሮች ጋር ሲነጻጸር በጣም ከፍ ያለ ነው።

https://p.dw.com/p/2zp6j
Symbolbild Deutschland-Visum
ምስል DW

Datenanalyse: Deutsche Visa-Politik in Afrika - MP3-Stereo

እውነታኛ ስሟን መግለጽ ያልፈለገችው ራሷን ግሬስ ቦአቴንግ ብላ ያስተዋወቀችው የጋና ዜጋ ቪዛ ማግኘትን ቀላል አድርጋ ነበር የይመስላት ነበር። የ26 ዓመቷ ከሶስት ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የቪዛ ማመልከቻ ባስገባችበት ጊዜ ፣ ወደ ጋና መመለሷ አጠራጣሪ ነው በሚል  ምክንኢት ማመልከቻዋ ውድቅ እንደተደረገባት ለዶይቸ ቬለ ገልጻለች። የባንክ ቁጠባ ሂሳቧን ያሳየችው፣ በመዲናይቱ አክራም የራሷ ቤት እና ቤተሰብ እንዳላት፣ ማለትም፣ የተጠየቀባትን ሁሉ ማሟላቷን ለኤምባሲው  ብታረጋግጥም፣ ማመልከቻዋን እንደገና ውድቅ ያደረገው ኤምባሲ ከርሷ ምን እንደሚፈልግ  እንዳልተረዳች ተናግራለች። ይህen ተከትሎ ያስገባቻቸው ሁለት ማመልከቻዎችም ተቀባይነት ሳያገኙ ነበር የቀሩት። ቪዛ ያገኘችው በአራተኛ ሙከራዋ ነበር። ግሬስ ከአፍሪቃ መሆኗ ቪዛ ማግኘቱን አዳጋች እንዳደረገው ታምናለች።
« የሌሎች ሀገራት ዜጎች ለምንድነው በቀላሉ ወደ ጀርመን መምጣት የሚችሉት? ለአፍሪቃውያን ለምን  አዳጋች ሆነ? በአፍሪቃዊ እና ከቻይና፣ ከአውስትሬሊያ በሚመጣው ሰው መካከል ምንድን ነው ልዩነቱ? ሁላችንም ሰብዓዊ ፍጡሮች ነን፤ ተመሳሳይ ክፍያ እንከፍላለን፣ የምትጠይቋቸውን ተመሳሳይ ጥያቄዎች እናሟላለን። »
ግሬስ ቦአቴንግ ብቻ አይደለችም እንዲህ የምታስበው። ይህ ወቀሳ ምን ያህል እውነት መሆኑን ለማጣራት የዶይቸ ቬለ ጋዜጠኞች በጎርጎሪዮሳዊው 2014 እና 2017 ዓም የጀርመን ኤምባሲዎችን የቪዛ አሰጣጥ ሂደት፣ በተለይ፣ በብሔራዊ ቪዛ፣ የትምህርት፣ የስራ ወይም ቤተሰብ የማገናኘት ቪዛ ላይ ትኩረት በማድረግ ግምገማ አካሂደዋል። ግምገማው ለአጭር ጊዜ ጉብኝት የሚሰጠውን የሸንገን ቪዛን አላካተተም።
ከየአምስቱ ማመልከቻዎች አንዱ ተቀባይነት አያገኝም
በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚገኙ የጀርመን ኤምባሲዎች እና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች በ2014 እና በ2017 ዓም መካከል ውሳኔ ያገኙ ማመልከቻዎች ቁጥር በ58% መጨመሩ እና ከነዚህም ተቀባይነት ያላገኙት ማመልከቻዎች ቁጥር በ131 ከፍ ማለቱ ጥናቱ በመጀመሪያ የተገነዘበው ልዩ ሁኔታ ነው። በዚሁ ጊዜ ውሳኔ ካገኙት ማመልከቻዎች መካከል ከአፍሪቃ 10% ብቻ ነበሩ። ከሌሎች የዓለም ክፍላት ውሳኔ ያገኙት ማመልከቻዎች እጅግ ብዙ ነበሩ። ከእስያ 60%፣ ከአውሮጳውያት ሀገራት 23%። ተቀባይነት ያላገኙትን ማመልከቻዎች ስንመለከት፣ አፍሪቃ ቀዳሚውን ቦታ ይዛለች፣ 22% ፣ ይህም፣ ከየአምስቱ አንዱ ማለት ነው። በአንጻሩ፣ ከአውሮጳ ከየስምንቱ አንዱ፣ ከእስያ ደግሞ ከየአስሩ አንዱ መሆኑ ነው። እንደ ጥናቱ  ከአፍሪቃ የሚቀርብ ማመልከቻ ከእስያ በሚቀርበው አኳያ ተደጋግሞ ውድቅ ይደረጋል። 
ለዚህም ተጨባጭ ምክንያት ማቅረቡ አዳጋች ነው። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በጥናቱ ግምገማ ውጤት ላይ ቃለ ምልልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም፤ ይሁንና፣ የእያንዳንዱ የጀርመን ኤምባሲ ቪዛ የሚሰጥበትን ውሳኔ በተመለከተ ከዶይቸ ቬለ ለቀረበለት ጥያቄ፣ ውሳኔው ተጨባጭ መስፈርቶችን መሰረት ያደረገ መሆኑን  ገልጿል። አመልካቾች ራሳቸውን መቻላቸውን፣ ለጀርመን ቆይታቸውም በቂ ገንዘብ እንዳላቸው ወይም በጀርመን ይህን ወጪያቸውን መሸፈን የሚችል ሰው መኖሩን በማስረጃ ማሳየት አለባቸው።ከዚህ በተጨማሪ፣  በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር እንዳስታወቀው፣ ወደ ጀርመን የሚመጡበት ዓላማን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ሊኖራቸው ይገባል። ከቤተሰብ ጋር ለመገናኘት ከሆነ ደግሞ ጀርመን የሚኖረው ግለሰብ የትዳር ጓደኛ ወይም ልጆች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ የጋብቻ  ወይም የልደት ምስክር ወረቀት ማቅረብ ይኖርባቸዋል። የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር እንዳለው፣  በተወሰነ ሀገር ማመልከቻዎች ላይ ጠንካራ ምርመራ ማድረግ ወይም ባፋጣኝ ውድቅ ማድረግ የሚል ደንብ በመሰረቱ የለም።
በሀገራቱ መካከል ትልቅ ልዩነት ይደረጋል
ያም ቢሆን ግን፣ በኦዝናብሩክ ዩኒቨርሲቲ የፍልሰት ምርምር እና ባህላዊ ጥናት መምህር ፕሮፌሰር ዮኸን ኦልትመር እንደሚያስቡት፣ በቪዛ አሰጣጡ ሂደት ላይ ዜግነት ሚና ይዟል።  
«  ጥያቄው ሁሌም አመልካች የመጣበት ሀገር ውስጣዊ ሁኔታን ይመለከታል። የአመልካች ጉዞ ለምሳሌ በሀገሪቱ ፀጥታ፣ በህዝቧ ጤንነት ወይም በማህበራዊው የድጎማ ስርዓት ላይ  አደጋ ሊፈጥር ይችል ይሆን ይሆናል ተብሎ  ሲታሰብ እንደ ስጋት ሊቆጠር ይችላል። ጥያቄው አመልካች ከበለጸገች ዴሞክራሲያዊት ሀገር ወይስ ከድሀ አምባገነን ሀገር ነው ? የሚመጣው የሚልም ነው። »
እንደ ፕሮፌሰሩ  ጀርመን ውስጥ ስለ አፍሪቃ ያለው አመለካከት ድሀ፣ እኩልነት የሌለባት እና ከፍተኛ ፍልሰት የሚከናወንባት አህጉር ነው የሚል ነው።
በሀገራት መካከል ውድቅ በሚደረጉት የቪዛ ማመልከቻዎች ቁጥር ላይ ለሚታየው ጉልህ ልዩነት ቀደም ሲል የተጠቀሱት ነጥቦች እንደ ምክንያት ሊጠቀሱ ይችላሉ። በ2014 እና 2017 ዓም በናይጀሪያ 5268 ማመልከቻዎች ሲገቡ 24% ውድቅ ሆኖዋል ፣ ደቡብ አፍሪቃ ከገቡት 4089 መካከል ደግሞ 6% ብቻ ነበሩ። 
ይህ ቁጥርሩ  የጀርመን መንግሥት በሚከተለው ይፋ ፖለቲካ እና በገሀዱ መካከል ያለውን ተጻራሪ ሁኔታ አጉልቷል፣ ምንም እንኳን የጀርመን መንግሥት ለአፍሪቃውያን የቪዛውን  አሰጣጥ እንደሚያሻሽል ካለፈው ዓመት ጀምሮ ቢናገርም። መ/መ አንጌላ ሜርክል የጋና ፕሬዚደንት ናና አኩፎ አዶ ባለፈው የካቲት ወር በርሊንን በጎበኙበት ጊዜ  ሕገ ወጥ ፍልሰትን መታገል እና ወጣት አፍሪቃውያን በሕጋዊ መንገድ የሚመጡበትን እድል መክፈት  እንደሚያስፈልግ መናገራቸው ይታወሳል። 
ግሬስ ቦአቴንግ ግን አፍሪቃውያን ውድቅ ቢደረግባቸውም ፣ በተደጋጋሚ ገንዘብ እየከፈሉ እና ከሩቅ ቦታ እየተጓዙ ማመልከቻ ማስገባታቸውን ትርጉም አልባ ብላዋለች። 

Datenvisualisierung DE Visa-Anträge Deutschland Ablehnungsraten Kontinente
Datenvisualisierung DE Visa-Anträge Deutschland Zeitverlauf

ጂያና ካሪና/ግሩን/ዳንየል ፔልስ/አርያም ተክሌ