የአፍሪቃና የአውሮጳ ኅብረት ጉባኤ | ዓለም | DW | 11.12.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የአፍሪቃና የአውሮጳ ኅብረት ጉባኤ

እሁድ ህዳር ሃያ ዘጠኝ በተጠናቀቀው የአፍሪቃና የአውሮጳ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የምጣኔ ሀብት ትብብር ስምምነት ከፍፃሜ ላይ ሊደርስ አልቻለም።በርካታ የአፍሪቃ አገራት መሪዎች ስምምነቱን ውድቅ አድርገውታል።

የአውሮጳ ዩኒየን ሠንደቅ ዓላማ

የአውሮጳ ዩኒየን ሠንደቅ ዓላማ

ዝምታን የመረጡ ይመስላሉ።ሆኖም ግን ከገፅታቸው ላይ ቁጣ የሚባል ነገር አይነበብም።የሴኔጋሉ ፕሬዚዳንት አብዶላይ ዋዴ፤ዕሁድ ህዳር ሃያ ዘጠኝ በተጠናቀቀው የአፍሪቃ እና የአውሮጳ ኅብረት ስብሰባ ላይ።

እ.ኤ.አ. ከሁለት ሺህ ሁለት ዓ.ም. አንስቶ አውሮጳውያን ከተለያዩ የአፍሪቃ አገራት ጋር የነፃ ንግድ ስምምነት ለማድረግ ሲጥሩ ቆይተዋል።ስምምነቱ ታዲያ በዚህ ዓመት ከአንድ ደረጃ ሊደርስ ይገባዋል።ከዚያም በዓለም የንግድ ድርጅት ስር መጠቃለል ይኖርበታል።ያም የአፍሪቃ፣ካሪቢክ እና ፓሲፊቅ አገራት በአውሮጳ ገበያ ላይ በነፃነት የሚንቀሳቀሱበትን ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።ይህ ከመሆኑ በፊት ግን በዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ የአፍሪቃ አገራት የዓለም የንግድ ድርጅት የሚያወጣውን ህግ ተቀብለው ማፅደቅ ይኖርባቸዋል ተብሏል።

ከሃምሳ ሶስቱ የአፍሪቃ አገራት ሴኔጋልን ጨምሮ ሰላሳ አራቱ በዝቅተኛ የምጣኔ ሀብት ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው። የእነዚህ አገራት ፍራቻ፤ምናልባት ከስምምነቱ በኃላ ወደየአገራቸው በነፃነት የሚገቡትን የአውሮጳ ሸቀጦች ተቓቁሞ በንግዱ ተጠቃሚ የመሆኑ ነገር ነው።ከዚያም በላይ አውሮጳውያኑ የጥሬ ዕቃ አቅርቦቱ ወዳለበት የአፍሪቃ አህጉር ገበተው ኢንዱስትሪዎቻቸውን ማቓቃም ይፈልጋሉ።የሴኔጋሉን ፕሬዚዳንት አብዶላይ ዋዴን ጨምሮ የበርካቶቹ የአፍሪቃ መሪዎች ፍራቻ ከዚህ የመነጨ ነው።
ሆኖም የአውሮጷ ኅብረት ፕሬዚዳንት ጆሴ ማኑኤል ባሮሶ እስከዚህ ዓመት መጨረሻ ድረስ መታገስ አለብን እያሉ ነው።

በሌላ ጎኑ በአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ድህረ ገፅ ላይ የተሰራጨው ፅሁፍ እንደሚገልፀው ይህ የኢኮኖሚ ትብብር ስምምነት የመጨረሻ ቢዘገይ እ.ኤ.አ.ጃንዋሪ አንድ ሁለት ሺህ ስምንት መፈረምና መጠናቀቅ አለበት።እሁድ ስብሰባው ሲጠናቀቅ የአውሮጳና የአፍሪቃ ኅብረት አገራትን ብዙ ያነጋገረው የምጣኔ ሁብት ትብብር ስምምነት ጉዳይ መቓጫ አልተበጀለትም። ስምምነቱ ምናልባት ሳምንት፣ወራት አለያም ዓመታት ሊጠይቅ ይችል ይሆናል።በሊዝበኑ ስብሰባ ላይ ግን ይህ ከፍፃሜ ሊደርስ አልቻለም።