የአፍሪቃና የአሜሪካ ንግድ | ኤኮኖሚ | DW | 25.07.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአፍሪቃና የአሜሪካ ንግድ

የአፍሪቃ የጨርቃ-ጨርቅ ፋብሪካዎች ለአሜሪካ ታላላቅ መደብሮችና ባለሞዶች አልባሳትንና ሌሎች ምርቶችን ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ በአሕጽሮት አጎአ ተብሎ በሚጠራው በአሜሪካ መንግሥት «ግሮውዝ ኤንድ ኦፖርቹኒቲ አክት» የዕድገትና የዕድል ሕግ» አማካይነት ነው።

የአፍሪቃ የጨርቃ-ጨርቅ ፋብሪካዎች ለአሜሪካ ታላላቅ መደብሮችና ባለሞዶች አልባሳትንና ሌሎች ምርቶችን ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ በአሕጽሮት አጎአ ተብሎ በሚጠራው በአሜሪካ መንግሥት «ግሮውዝ ኤንድ ኦፖርቹኒቲ አክት» የዕድገትና የዕድል ሕግ» አማካይነት ነው። የአፍሪቃ ሃገራት ጨርቃ-ጨርቅ አምራች ፋብሪካዎች ይሄው ሕግ በጠቀለለው አንድ አንቀጽ በመጠቀም ከቀረጥና ከኮታ ነጻ ሆነው ምርቶቻቸውን ወደ አሜሪካ ለማስገባት ይችላሉ።

ደምቡ ጥሬው ጣቃ ከሶሥተኛ ወገን ለምሳሌ ከቻይና ወይም ከሕንድ የመነጨ ቢሆንም እንኳ አፍሪቃውያኑ ምርቶቻቸውን ወደ አሜሪካ እንዳይልኩ አያግድም። ይሄው ጠቃሚ ሆኖ የቆየ ደምብ ታዲያ አሁን በቅርቡ በፊታችን መስከረም ወር የሚያከትም ሲሆን የአሜሪካ ሤኔትም ሆነ ሸንጎ በሚራዘምበት ሁኔታ ላይ ሳይወስን ዝም ብሎ እንደቀጠለ ነው። ይሄው ያስከተለው የአስተማማኝ ሁኔታ እጦት ደግሞ ገና ከአሁኑ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ በዘርፉ ተሰማርተው የቆዩ አፍሪቃውያንን ለሥራ ፈትነት እየዳረገ ሄዷል።

አሜሪካ ውስጥ ዛሬም ቢሆን የጨርቃ-ጨርቁን ምርት ገበያ በሰፊው የሚቆጣጠሩት እርግጥ እሢያውያን ናቸው። ይሁን እንጂ በዋጋ ረገድ የአፍሪቃ ፋብሪካዎችም ዕድሜ አጎአ ለተሰኘው የአሜሪካ የንግድ ሕግ በዋጋ ረገድ ርካሽ ምርት ከሚያቀርቡት መፎካከር ይችላሉ። በዚሁ ሕግ ውስጥ የሰፈረ አንድ አንቀጽ አፍሪቃውያን ርካሽ ጨርቅንና መሰል ምርቶችን ከቻይና ወይም ከሕንድ በማስገባት ለአሜሪካ ገበዮች ያለቀ ምርት ለምሳሌ የአልጋ ልብሶች፣ ሸሚዞች፣ ጂንስ ወዘተ እንዲልኩ ይፈቅዳል።

ሆኖም በደምቡ መራዘም መጓተት ላይ በተፈጠረው መረበሽ የተነሣ አፍሪቃ ውስጥ በየጨርቃ-ጨርቁ ፋብሪካ ከሣምንታት ወዲህ ብዙ የስፌት መኪናዎች መስራት አቁመው ነው የሚገኙት። ተቀማጭነቱ ናይሮቢ ላይ የሆነው የአፍሪቃ የጨርቃ-ጨርቅና የአልባሳት ፋብሪካዎች ማሕበር ሊቀ-መንበር ራጂቭ አሮራ እንዳስረዱት ታላላቁ የአሜሪካ ደምበኞችም ከመስከረም በኋላ ላለው ጊዜ አሁንም ገና ምርት እንዲቀርብላቸው አላዘዙም።

«በዚሁ የተነሣ የሃምሣ ሚሊዮን ዶላር ኪሣራ ደርሶብናል። ከዚሁ ሃያ ሚሊዮኑን ያጣችውም ኬንያ ናት። ምክንያቱም ኬንያ በውጩ ንግድ ሰፊ ድርሻ ስላላት ነው። አሁን በዚሁ የተነሣ ይበልጥ ተጎጂዋም ሆናለች»

አሮራ ከግብጽ እስከ ደቡብ አፍሪቃ የሃያ የአፍሪቃ ሃገራትን የጨርቃ-ጨርቅ ፋብሪካዎች ይወክላሉ። በዚሁ ተልዕኳቸውም ባለፉት ሁለት ዓመታት አዘውትረው ወደ አሜሪካ በመጓዝ ውሉ እንዲራዘም የሚመለከታቸውን ወገኖች ለማግባባት ሞክረዋል። ሆኖም ችግሩ በአሜሪካ ሤኔትና ሸንጎ ዘንድ ተሰሚነት አለማግኘታቸው ነው። ለመሆኑ የአሜሪካን ዝምታ ምን አመጣው? የዋሺንግተን ብሩኪንግ ኢንስቲቲዩት ባልደረባ ዊትኒይ ሽናይድማን ነገሩን እንዲህ ለማብራራት ሞክረዋል።

«መጓተቱ የአሜሪካ ብሄራዊ ሸንጎ አጠቃላይ በድንነት ውጤት ነው። የሕጉ መራዘም አሜሪካን ሆነ አፍሪቃን የሚጎዳ መሆኑን አንድም የተናገረ ሰው የለም። በአንጻሩ ጠቃሚነቱን እያንዳንዱ ያውቀዋል። ግን የሚያሳዝን ሆኖ ጥቃቅን ነገሮች ሂደቱን ዝግተኛ አድርገውት ነው የሚገኘው»

የሕጉ አለመራዘም ብዙዎች አምራቾችን እያሳሰበ ሳለ በወቅቱ ከአሜሪካ በኩል ያለው የአቅርቦት ትዕዛዝም በሽናይድማን ስሌት በ 35 ከመቶ መጠን ነው የቀነሰው። በዚሁ የተነሣም በርካታ የአፍሪቃ ጨርቃ-ጨርቅ አምራቾች በአሜሪካ ፖለቲከኞች ችላ የመባል ስሜት ሳያድርባቸው አልቀረም። ይሄ ሁሉ አሜሪካ በአፍሪቃ ካላት «በዕርዳታ ፈንታ ንግድ» የሚል ፍልሥፍና ጋር ታዲያ እንዴት እንደሚጣጣም መለየቱ የሚያዳግት ነው። አስተሳሰቡ በ 2000 ዓመተ-ምሕረት በፕሬዚደንት ክሊንተን ተፈርሞ የጸናው የአሜሪካን ገበዮች ከስድሥት ሺህ ለሚበልጡ የአፍሪቃ ምርቶችና ዕቃዎች ያለ ቀረጥና ኮታ በር የከፈተ የአጎአ ገቢርነት ዋና አካልም ነበር።

ዋናው ምርት እርግጥ ለአሜሪካ ስልታዊ ጠቀሜታ ያለው ነዳጅ ዘይት ሲሆን እርግጥ የጨርቃ-ጨርቅና የአልባሳት ኢንዱስትሪውም በረጅም ጊዜ ትልቅ ክብደት የተሰጠው ነው። የአሜሪካ ኩባንያዎች አፍሪቃ ውስጥ ይህንኑ ሲያስመርቱ ቆይተዋል። በአንጻሩም ይህም ሥራ ፈጥሯል፤ በተለይም ለሴቶች! እንዲያም ሲል ኤኮኖሚን ለማሳደግ፣ ድህነትን ለመታገልና ዴሞክራሲንም ለማራመድ እንደሚያስችል ነው የታመነበት። ዊትኒይ ሽናይድማን እንደሚሉት ከአጎአ በስተጀርባ ያለው ራዕይም ይሄው ነው።

«አጎአ 300 ሺህ የሥራ ቦታዎችን ለመፍጠር አስችሏል። ከዚሁ በተጨማሪ በተዘዋዋሪ የተገኙ 1,5 ሚሊዮን የሥራ ቦታዎችም አሉ። ይህ ሁሉ ደግሞ በአሥር ሚሊዮን ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ ላይ ለውጥን አስከትሏል። ለኤኮኖሚ ዕድገት፤ እንዲሁም ከቀድሞው የለጋሽ-ተለጋሽ ግንኑነት ለመላቀቅ፤ በጥቅሉ ለሁለቱም ወገን ጥቅም ትልቅ እሰተዋጽኦ አድርጓል ብዬ ነው የማምነው»

ይሁንና ከዚህ ተከፈተ ከሚባለው የሥራ መስክ አሁን ብዙው እየተዘጋ ሲሄድ ነው የሚታየው። የአምራቾቹ ማሕበር ባልደረባ ራጂቭ አሮራ እንደሚናገሩት በጨርቃ-ጨርቁ ዘርፍ እስካሁን 15 ሺህ ሰዎች ሥራቸውን አጥተዋል። ይህም በተለይ በኬንያ፣ በሌሶቶ፣ በስዋዚላንድ፤ በሞሪሺዬስና በኢትዮጵያ ነው የሚያመዝነው።

«የታሰበው ከጥጥ እስከ ሞድና አልባሳት ሁሉን የጠቀለለ የተሟላ የጨርቃ-ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለማነጽ ነበር። ግን ይህ ቀጣይነት ባለመኖሩ አልሰራም። ይህም የአሜሪካው ደምብ ለሶሥት ወይም አራት ዓመታት የሚራዘም የአጭር ጊዜ ዕቅድ በመሆኑ ነው።

ለማንኛውም የአሜሪካ መንግሥት ሕጉን እንደሚራዘም የብዙዎች ዕምነትና ተሥፋም ነው። እርግጥ እንደ ራጂቭ አሮራ በረጅም ጊዜ ዕድገትና ልማትን ዕውን ለማድረግ ከ 15 እስከ 20 ዓመት ጊዜ ተገቢ በሆነ ነበር።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic