የአፋር ክልል ነዋሪዎች በመዋጮ ተማረዋል | ኤኮኖሚ | DW | 16.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአፋር ክልል ነዋሪዎች በመዋጮ ተማረዋል

በአፋር ክልል የመንግስት ሰራተኞች እና ነጋዴዎች በመጪው ኅዳር ወር ለሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ዝግጅት ከአቅማችን በላይ መዋጮ ተጠየቅን እያሉ ነው። ለበዓሉ ዝግጅት በ1.6 ቢሊዮን ብር ግንባታ የሚያካሒደው የክልሉ መንግስት በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:27
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:27 ደቂቃ

የመንግስት ሰራተኞች እና ነጋዴዎችን ያማረረው መዋጮ በአፋር ክልል

በመጪው ኅዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ከወረዳ እስከ ፌድራል መንግሥት ባለሥልጣናት ድረስ በአፋር ክልል ዋና ከተማ ሰመራ ይከትማሉ። ላለፉት አስራ አንድ አመታት በዚህ ቀን በዓሉን እንዲያዘጋጁ በተመረጡ ከተሞች ጭፈራው ይደራል። አውራ ጎዳናዎች ያለ ወትሯቸው ጸድተው በሰንደቅ ዓላማም አሸብርቀው ይታያሉ። በሚቀጥለው ኅዳር ተራው የሰመራ ነው። ዝግጅቱ ግን እንደ አቶ ሑሴን አሊ ላሉት የመንግሥት ሰራተኞች ከፈቃዳቸው ውጪ ገንዘብ እንዲያወጡ አስገድዷቸዋል። በዳዌ ወረዳ የአቅም ግንባታ ፅ/ቤት ሰራተኝነት የሚያገለግሉት አቶ ሑሴን እንደሚሉት በፈቃደኝነት የተጀመረው መዋጮ በግዳጅ ቀጥሏል። ለብሔር ብሔረሰቦች በዓል በሚያዝያ ወር የደሞዛቸውን 30 በመቶ እንዳዋጡ የሚናገሩት አቶ ሑሴን በሐምሌ ወር ደግሞ "አስተዳደር እና ካቢኔዎች ብትፈልጉም ባትፈልጉም ግማሽ ትቆርጣላችሁ" እንዳሏቸው ይናገራሉ።

የሰመራ ከተማው ነዋሪ አቶ ሐቢብ ሰዲቅም የመንግሥት ሰራተኛ ናቸው።  አቶ ሐቢብ ከወር ደሞዛቸው ወደ 400 ብር ገደማ ላለፉት አምስት ወራት ለዚሁ ዝግጅት ሲቆረጥባቸው ቆይቷል።

"ባንስማማም ምንም የምናመጣው ነገር የለም።"የሚሉት አቶ ሐቢብ "የብሔር ብሔረሰቦች ተቆርጧል ተብሎ ነው {ደሞዝ} እጃችን የሚደርሰው" ሲሉ ያማርራሉ። በክልሉ የአብዓላ ወረዳ የመንግሥት ሰራተኛ የሆኑ ሌላ አስተያየት ሰጪ የደሞዛቸው 30 በመቶ ለሶስት ወራት ተቆርጦባቸዋል። ፈቃድ ልንጠየቅ ይገባ ነበር የሚሉት እኚህ የመንግስት ሰራተኛ መዋጮውን "ፍትኃዊ አይደለም" ሲሉ ይወቅሳሉ።

የብሔር ብሔረሰቦችን በዓል ለማክበር ሽር ጉድ የሚለው የአፋር ክልላዊ መንግሥት ከመንግሥት ሰራተኞች የሚሰበስበው መዋጮ ተመሳሳይ አይደለም። ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ መምህር ለበዓሉ ዝግጅት የተቆረጠባቸው የደሞዛቸው አምስት በመቶ ብቻ ነው። የእዋ ወረዳው መምህር በትርፍ ጊዜያቸው ይነግዳሉ። እርሳቸው ፈቃደኛ ባይሆኑም በነጋዴነታቸው ተጨማሪ 400 ብር ለበዓሉ ዝግጅት እንዲያዋጡ ትዕዛዝ ተጥሎባቸዋል።

በመጪው ኅዳር 29 ቀን የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ዝግጅት በፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የክልሉ መንግሥት ባቋቋመው ማሥተባበሪያ ፅ/ቤት በጥምረት ይዘጋጃል። ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው በአፋር ክልል የማስተባበሪያ ፅ/ቤቱ ኃላፊ አቶ መሐመድ አወል በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።

የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ለጥያቄው ምላሽ መስጠት ያለበት የአፋር ክልላዊ መንግሥት ነው ይበል እንጂ ከፌድራል መንግሥት ለበዓሉ ዝግጅት የሚመደብ በጀት መኖሩን ግን አረጋግጧል። አጠቃላይ የበዓሉ አከባበር ምን ያህል ይፈጃል? የክልሉ መንግሥት ከአጠቃላይ ወጪው ምን ያክሉን ይሸፍናል? የፌድራሉስ መንግስት ድርሻ ስንት ነው? ምላሽ ያጡ ጥያቄዎች ናቸው።በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የመስጠት ሥልጣን የለኝም ያሉን የምክር ቤቱ ባልደረባ ምክር ቤቱ በበዓሉ አከባበር ላይ ያለው ሚና "የማስተባበር" ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል።

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለዚሁ በዓል ዝግጅት እንደቀደሙት ክልሎች ሁሉ በስብሰባ አዳራሽ፤ ስታዲየም እና የእንግዶች ማረፊያዎች ግንባታ ተጠምዷል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው የክልሉ መንግሥት ለዚህ በዓል ብሎ ለሚገነባቸው እቅዶች ብቻ 1.6 ቢሊዮን ብር ወጪ አድርጓል። 

ይህ ግን የሰመራ ታሪክ ብቻ አይደለም። ከዚህ ቀደም በዓሉን ያከበሩ ከተሞች በድንገተኛ ግንባታዎች ሲጥለቀለቁ ተስተውሏል። ይኸንንው በዓል የጋምቤላ ከተማ ለአስረኛ ጊዜ ስታዘጋጅ ቀድሞ ያልነበሯትን የእንግዳ ማረፊያ ስፍራዎች ገንብታለች። ከ35 ሺህ በላይ ተመልካቾችን የማስተናገድ አቅም ያለው ዘመናዊ ስታዲዬም፤ የመሰብሰቢያ አዳራሽና የባህል ማእከል፤ የመንገድና የትራፊክ መብራቶችም ለዚሁ በዓል ተብለው ተሰርተዋል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic