የአፋር ተወላጆች መገናኛ መረብ ማሳሰቢያ | ኢትዮጵያ | DW | 11.07.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የአፋር ተወላጆች መገናኛ መረብ ማሳሰቢያ

በዉጭ የሚኖሩ የአፋር ተወላጆች መገናኛ መረብ የተሰኘዉ ስብስብ በሶማሌ ተወላጆችና በአፋሮች መካከል በመሬት ይገባኛል ምክንያት የሚነሳዉን ግጭት የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ትኩረት አልሰጠዉም ሲል ወቀሰ።

የተጠቀሰዉ ስብስብ በኢንተርኔት ባሰራጨዉ ጋዜጣዊ መግለጫም በሶማሌ ክልል መስተዳድር ይደገፋሉ ያላቸዉ የሶማሌ ኢሳ ጎሳ ሚሊሺያ ኃይሎች በስልት ወደአፋር ክልል በሚያደርጉት መስፋፋት ግድያና መፈናቀልን እያስከተሉ እንደሆነ አመልክቷል። እንደመግለጫዉ የመሬት ይዞታን የማስፋፋቱ ዓላማ የታላቋን ሶማልያ የከሸፈ ሕልም እዉነት ከማድረግ ጋ የተገናኘ ነዉ።

ታላቋ ሶማሊያ የመገንባት ሕልም ቅዠት ሆኖ ከቀረ ዓመታት መቆጠራቸዉ እየታየ ነዉ። ዛሬ ያን ሃሳብ ይዘዉ የተንቀሳቀሱ የሶማሊያ መሪዎች እራሳቸዉ የሚገኙበት በግልፅ አይታወቅም። ሀገሪቱ ግን ከገባችበት የእርስ በርስ ግጭት ጦርነት ሳትላቀቅ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ነጉደዋል።

በዉጭ የሚኖሩ የአፋር ተወላጆች መገናኛ መረብ ማለትም አፋር ዲያስፖራ ኔትወርክ ከትናንት በስተያ ያሰራጨዉ መግለጫ የአፋርን መሬት ለመቀራመት ይደረጋል ያለዉ ስልታዊ ግድያና ማፈናቀል ያንን የከሸፈ ሕልም እዉን ለማድረግ ያለመ ነዉ ይላል። መግለጫዉ አያይዞም ይህ መስፋፋት የሶማሊያን ድንበር አዋሽ ወንዝ ድረስ ማድረስ የሚለዉን እንደሚያካትት ይገልጻል። እንዲህ ያለዉን እንቅስቃሴና መሬታቸዉን ለመዉሰድ ሲባል በአፋር ተወላጆች ላይ ይደርሳል ያለዉን በደል ለኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ደጋግሞ ማመልከቱን በመግለፅም ተገቢ ምላሽ አለማግኘቱንም ያትታል። የኢትዮጵያ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ ወርቁ መረጃዉ የተሳሳተ ሳይሆን አይቀርም ይላሉ።

ሁለት ገፅ በሆነዉ በዉጭ የሚኖሩ የአፋር ተወላጆች መገናኛ መረብ መግለጫ መሠረት በአፋርና በኢሳ ሶማሌ መካከል ያለዉ ግጭት ተራ የመሬትና የዉሃ ይገባኛል ጥያቄ ብቻ ሳይሆን በወረራ መሬትን የመዉሰድ ነዉ። የዚህን ወረራ ድብቅ ዓላማም ደጋግሞ ለኢትዮጵያ መንግስት ሁሉ ማጋለጡንም ያስረዳል። የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ የፖለቲካ ኃይሎች ጉዳዩን በጥንቃቄ እንዲመከቱትም ያሳስባል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic