የአፋርና ኢሳ የግዛት ዉዝግብ | ኢትዮጵያ | DW | 13.11.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የአፋርና ኢሳ የግዛት ዉዝግብ

በአፋርና ኢሳ ብሔረሰቦች መካከል በተለያዩ ጊዜያት አለመግባባትና ግጭት ሲከሰት ኖሯል። በምሥራቅ ኢትዮጵያ በአብዛኛዉ በከብት ርባታ ላይ ኑሯቸዉ የተመሰረተ ወገኖች የግጦሽ መሬትና ዉኃ ሲያጋጫቸዉ መኖሩ ግልፅ ቢሆንም ጠንካራ በሆነዉ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስልታቸዉም በሀገሪቱ በግምባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸዉ።

እንዲያም ሆኖ ግን አሁንም ዉዝግቡ እልባት አላገኘም። ከሳምንታት በፊት ኢሳዎች የወሰን አከላለል ጉዳይ በሚመለከት ለፌደራል መንግስት አቤቱታ አቅርበዋል፤ የአፋር ተወላጆች በበኩላቸዉ ቦታዉ የማን እንደሆነ ለመረዳት ከመንግሥት ዶሴዎች በተጨማሪ ስያሜያቸዉን ማየት ነዉ ይላሉ።

አፋርና ኢሳ በምሥራቅ ኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢ ተጎራብተዉ የሚኖሩ ብሔረሰቦች ናቸዉ። ከቋንቋ በቀር ሃይማኖትን ጨምሮ በአኗኗር ዘይቤያቸዉ ማለትም በባህል፤ በኤኮኖሚ ምንጭና በመሳሰሉት አንዱን ከሌላዉ ለመለየት ያዳግታል። በመካከላቸዉ በግጦሽ ቦታና ዉሃ ምክንያት ግጭቶች ይነሱ ነበር ዛሬም አልጠፋም። ወትሮ የነበረዉን ባህላዊ ግጭት የሚሉት የዚያዉ አካባቢ ተወላጆች ማለት ነዉ የተለመደና እያደርም ሲሰክን የታየ ጉዳይ ነዉ። ከጣሊያን ወረራ ወዲህ ግን ይላሉ ከአፋር ተወላጆች አንዱ የሆኑት አቶ ዑመር አሊ ይዘቱ ተለዉጧል፤

እነዚህ ወገኖች ከመሠረተ ልማት አንፃር አኗኗራቸዉ ያልተሻሻለ፤ የኑሯቸዉ መሠረት የሆኑት ከብቶቻቸዉ እንኳ በቂ ግጦሽ እና ዉሃ የሚያገኙበት ሁኔታ ዉሱን መሆኑን ያመለከቱት አቶ ዑመር እኩል ችግር የሚያዩ ቢሆኑም አንዱ የሌላዉን ወሰን ሳይገፋ ለመኖር አለመቻላቸዉን ነዉ የገለጹት።

አፋርና ኢሳ በሚገኙበት እያንዳንዳቸዉ የራሴ የሚሉት የታወቀ አካባቢ አላቸዉ። አካባቢዉን በሚገባ እንደሚያዉቁ የሚናገሩት አቶ ዑመር የቦታዎቹ ስም አሰያየምም ራሱ የትኛዉ አካባቢ የአፋር ወይም የኢሳ መሆኑን ይናገራል።

በእነዚህ ማስረጃነትም የሁለቱ የክልል መንግሥታት አለመግባባቱን መፍታት ይችላሉ ሲሉም ይገልጻሉ። አዳዲስ የወሰን አከላለል እና የቦታዎች ይገባኛል ጥያቄዎች ከጀርባቸዉ የያዙት ነገር አለ ሲሉም አቶ ኡመር አሊ እንዲህ ያስረዳሉ። የኢሳ ብሄር አባላት በቅርቡ ለፌደራል መንግሥት ያቀረቡት ደብዳቤ የወሰን አከላለልን ይመለከታል። በወቅቱም በጉዳዩ ላይ ተሰባስበዉ መወያየታቸዉን መዘገባችን ይታወሳል። አፋርና ኢሳ አንድ ከሚያደርጓቸዉ ነገሮች መካከል ባህላዊ የግጭት አፈታት ስልታቸዉን መጥቀስ ይቻላል። በብዙ መንገድ የተሳሰሩት እነዚህ ወገኖች መቋጫ ያጣ የሚመስለዉን ዉዝግብ ይህን ስልት ተጠቅመዉ ለመፍታት አልሞከሩ ይሆን?

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic