የአፈ-ጉባኤው ሥራ መልቀቂያና የብር መዳከም | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 13.10.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የአፈ-ጉባኤው ሥራ መልቀቂያና የብር መዳከም

ሰሞኑን በርካቶችን ካነጋገሩ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ርእሰ-ጉዳዮች መካከል አቶ አባዱላ ገመዳ ከአፈ-ጉባኤነት ሥልጣን ለመልቀቅ መወሰናቸውና በኦሮሚያ ዳግም የመንግሥት ተቃውሞ መቀስቀሱ እንዲሁም የብር ምንዛሪ ዋጋ መዳከም ዋናዎቹ ናቸው።

ምርኮኛ ወታደር ነበሩ። የጀነራልነት ማዕረግም አግኝተዋል። ማዕረጉን አውልቀው የኦሮሚያ መስተዳደር ፕሬዚዳንት እስከመሆንም ደርሰው ነበር። ከክልል ፕሬዝዳንትነት መንበራቸው ተነስተው ላለፉት ሰባት ዓመታት የምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ሆነውም ቆይተዋል። አፈጉባኤ አባ ዱላ ገመዳ። በየሳምንቱ አንድ የመነጋገሪያ ርእስ የማይታጣበት የማኅበራዊ መገናኛዉ መንደር ሳምንቱን የተንደረደረው ባልተጠበቀ ዜና ነበር። የአፈጉባኤ አባ ዱላ ገመዳ የሥራ መልቀቂያ እወጃን በማሰማት። አፈጉባኤው የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ ስለማስገባታቸው በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው ካረጋገጡም በኋላ ስለ እሳቸው መወራቱ፣ ከእዚህም ከዚያም ትንታኔ መሰጠቱ ቀጥሏል። የሰውዬው ሥልጣን ለመልቀቅ መጠየቅ ፋይዳና እርባናቢስነት ለየቅል በሚደመጥበት ወቅት ድንገት የብር የመግዛት አቅም መዳከም መነገሩ ሌላ የመወያያ ርእስ ሆኖ ወጥቷል። 

ቅዳሜ መስከረም 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ነበር «አዲስ ስታንዳርድ» የተባለው ድረ-ገጽ  ያልተጠበቀውን ክስተት በሰበር ዜናው ይፋ ያደረገው።  አቶ አባዱላ ገመዳ ከምክር ቤት አፈ-ጉባኤነታቸው ለመልቀቅ ደብዳቤ ስለማስገባታቸው በእንግሊዝኛ ቋንቋ የቀረበው የአዲስ ስታንዳርድ ዜና የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሰፊ መነጋገሪያ የሆነውም በቅጽበት ነበር። ድረ-ገጹ አቶ አባዱላ መልቀቂያ ያስገቡት «የፌዴራል የጸጥታ ተቋማት በምሥራቅ ኢትዮጵያ የተከሰተውን ኹከት የያዙበትን መንገድ ጨምሮ የቅርብ ጊዜያት ፖለቲካዊ ኩነቶችን በመቃወም ነው» ብሏል። የአፈጉባኤው ውሳኔ «በኢሕአዴግ ውስጥ ያለውን ጥልቅ ቀውስ ያመላክታል» ሲልም አክሏል። በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች በበርካቶች ዘንድ አድናቆትና ትችት የተሰጠበትን ውሳኔ አፈ ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ ይፋ ያደረጉት በዚህ መልኩ ነበር። «…በዚህ ኃላፊነት ለመቀጠል የማያስችሉኝ ምክንያቶች በመኖራቸውና ፍላጎቱም ስለሌለኝ ለመልቀቅ ድርጅቴንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ጠይቄያለሁ…» 

አቶ አባዱላ ገመዳ ከአፈ ጉባኤነት ሥልጣናቸው ለመነሳት ያቀረቡት ጥያቄ በተለያዩ የፖለቲካ አቀንቃኞች ዘንድ የድጋፍ እና የነቀፌታ አስተያየቶች እንዲሰጡ ሰበብ ኾኗል። ገዢው ኢህአዴግ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተነሱበት ተቃውሞዎች አጣብቂኝ ውስጥ ባለበት በአሁኑ ወቅት አፈጉባኤው «ገለል ለማለት መወሰናቸው ያስመሰግናቸዋል»፤ ውሳኔያቸውም «ደፋር ያስብላቸዋል» የሚሉ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል። 
በዛው መጠን ደግሞ «የለም፤ ድሮም ቢሆን የያዙት ሥልጣን ጥርስ አልባ ነበር» ቀደም ሲልም «ለኦሮሞ ተወላጆች የፈየዱት ነገር የለም» ስለዚህም «እንደ ጀግና መታየታቸው ትርጒመ-ቢስ ነው» ሲሉ አንዳንዶች ተደምጠዋል። 

ሚቴ አቡኬ በትዊተር ገጹ ባሰፈረው አጠር ያለ  የእንግሊዝኛ ጽሑፉ እንዲህ ተሳልቋል። «አባዱላም ሆኑ በጽ/ቤታቸው የመሸጉ አሻንጉሊቶች  በኢትዮጵያ ፖለቲካ ያን ያኽል ፋይዳ ይኖራቸዋል ብዬ አልገምትም ነበር።»

ዮሐንስ እውነቴ‏ በበኩሉ፦ «በአባ ዱላ መልቀቂያ እና አንደምታው ላይ አሁንም ድረስ የቀን ቅዠት ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሰዎች አሉ። ከዜሮ ተነስተው በአንዲት ጀንበር ጀግና የኾኑ ናቸው» ሲል አፈ-ጉባኤውን አወድሷቸዋል። 

አቶ አባዱላ ገመዳ ከአፈ ጉባኤነት ሥልጣናቸው ለመነሳት ጥያቄ ቢያቀርቡም በኦሮሚያ ክልል ለሌላ ሥልጣን መታጨታቸው ተሰምቷል። ከአንድ የውጭ ድርጅት ጋርም ኦሮሚያን ወክለው በኢኮኖሚ ጉዳይ ላይ ፊርማ ሲፈራረሙ በሚል ጽሑፍ የታጀበ ፎቶ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተሰራጭቷል። አፈጉባኤው እንደውም ከፌዴራል ሥልጣናቸው እንዲነሱ የተደረገው «መንግሥት በኦሮሚያ ክልል የደረሰበትን ቀውስ በቅርበት እንዲከታተሉለት ስለፈለገ ነው» የሚሉም አልታጡም። ጭራሹኑ «ትርጉም በሌለው ጉዳይ ላይ አታድርቁን ስለዛ መስማት አንፈልግም» የሚሉ አስተያየቶችም ተንጸባርቀዋል።

ጋሻው አገኘ በፌስቡክ ገጹ፦ «...ጎንደር ዙሪያ ያለውን የጣናን ክፍል ማየት አለብን። የኛ ሚዲያዎች አፍ ስሌለው አፈ ጉባኤ አባ ዱላ ገመዳ ሄደ መጣ ሲያደነቁሩን ይውላሉ» ሲል ጽፏል። «የሚጠቅመንና የማይጠቅመንን ለይተን እስካላወቅን ድረስ ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ሁነን ብቻ መቅረታችንን ልብ እንበል። ጣና ዘላቂ መፍትሄ ይሻልና ትኩረት ለጣና!!» የሚልም አስተያየት አክሏል። ወደ 200 የሚጠጉ በጎ ፈቃደና ወጣቶች ከኦሮሚያ ወደ ባሕር ዳር ጣናን ለመታደግ መጓዛቸውም ተጠቅሷል። 

ዋይ ኦሮሚያ በበኩሉ አቶ አባዱላ በፌዴራል መንግሥቱ ጉልኅ ስፍራ እንደነበራቸው በመጥቀስ በፌስቡክ ገጹ ጽፏል። «መለስ በጣም የሚፈራውን ሰው በቅርበት እየተቆጣጠረ ያስቀምጥ ነበር» ያለው ዋይ ኦሮሚያ፦«አባዱላንም ያለ ሥራ አፈ ጉባኤ አደረጎ የሰየመው በወቅቱ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ትልቅ ተቀባይነትን እያገኘ በመምጣቱ ነው» ሲል አስተያየቱን አስፍሯል።

አብርሃም ይስሐቅ ከዋይ ኦሮሚያ ፍጹም ተቃራኒ የሆነ ሐሳብ ነው የሰነዘረው፤ እንዲህ ሲል ይንደረደራል፦ «ወያኔ ላይ እየተፈጠረ ያለውን መደናበር የፈጠረው አባዱላ አይደለም፤ ኦህዴድ አደለም ህዝቡ ነው።» ቀጠል አድርጎም፦«ወያኔ ቤት ለሚፈጠረው ትርምስምስ ሁሉ ክሬዲቱን ሞተው ቆስለው ታስረው ላሉት ጀግኖች ሁሉ ስጡ እንጂ ተመልሳቹ ማምለጫ ጠፍቶት ሂሳቡን ሠርቶ መልቀቂያ ላስገባ ደንባራ አትስጡ፤ አታሞግሱት፤ አታጨብጭቡለት» ብሏል። «ከህዝብ ጋር ያልቆመን ከህዝብ የቆመ አስመስላቹ አታቅርቡ» ሲልም ጽሑፉን ደምድሟል።

በዚሁ ሳምንት ከአቶ አባዱላ ገመዳ የሥልጣን መልቀቅ ጥያቄ በተጨማሪ በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች ዳግም የመንግሥት ተቃውሞ ተቀስቅሶ የሰው ሕይወት መጥፋቱም ተገልጧል።  የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባረጋገጠው ብቻ ረቡዕ ዕለት በሻሸመኔ በተካሄደ ሰልፍ ላይ የ3 ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፤ 30 የሚሆኑም ቆስለዋል።   በምዕራብ ሐረርጌው ሰልፍም የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን እና ሌሎች ሦስት መቁሰላቸውም ተገልጧል። 

የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች የሐኪም ቤት ፎቶግራፎችን በማያያዝ የረቡዕ ዕለት ሟቾች ቁጥር ቢያንስ ስምንት እንደሆነ ገልጠዋል። ወሊሶ፤ ሻሸመኔ፣፤ ዶዶላ እና አምቦ ከተሞች እንዲሁም በምዕራብ ሐረርጌ ቦኬ አካባቢ ተቃውሞ ተደርጎባቸዋል ከተባሉ ከተሞች ውስጥ ይገኛሉ። 

የብር ከዶላር አንጻር ቀድሞ ከነበረው አቅሙ በ15 በመቶ እንዲዳከም የመደረጉ ዜና ሌላኛው የማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች የመነጋገሪያ ርእስ ሆኗል። በውሳኔው መሠረት 1 ዶላር የሚመነዘርበት ዋጋ ወደ 27 ብር ግድም ከፍ ብሏል። ቀድሞ 1 ዶላር ይመነዘር የነበረው በ23 ብር ነበር።  

ይኽ አዲስ መመሪያ «የውጭ ንግድን ለማበረታታት ታስቦ ነው» ቢባልም፦ «ባለው የኑሮ ውድነት ላይ የዋጋ ንረትን በማስከተል ተጨማሪ ጫና ይፈጥራል» ሲሉ ትንታኔ ለማቅረብ የሞከሩ በርካቶች ናቸው። ይህንኑ መመሪያ ተከትሎ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል በዋትስአፕ አድራሻችን የደረሰንን እናስቀድም።

«ብራችን ዝቅ ካለ የመግዛት አቅሙ ይወርዳል፤ ሰለዚህ 1000 ብር 5 ቀን ነው የሚያውለው፤ መንግሥት የራሱን ጥቅም ሲያስብ ህዝብን እየጨቆነ ነው፡፡ ደሀ መኖሪያ ይጣ። ቱርከ፤ ስዊዲን፤ ኳተር ለህዝብ 10 የሚሸጠውን ዕቃ ድጎማ በማድረግ 5 ብር ይሸጣል የኛ መንግሥት...» ሲል አስተያየቱን በእንጥልጥል ትቶታል።

መስፍን ነጋሲ በፌስቡክ በሰጠው አስተያየት፦ «የብር የመግዛት አቅም 15 በመቶ ተዳከመ፤ አገሪቱ 11 በመቶ እድገት ላይ ነች፤ እውነቱ የቱ ነው?» ሲል አጠይቋል።

ቢኒ ስንታየሁ ደግሞ፦ «ምንም ማስረዳት የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም ባንክ የስቀመጥከው 100 ብር ከዛሬ በኋላ የመግዛት አቅሙ 85 ብር ሆኗል። ጥቂቶችን ለመጥቀም የተሠራ ሥራ ነው» ብሏል።

መሐመድ ሰኢድ፦ «የከፍታው ዘመን ጀመረኮ፤ አንድ ኪሎ ሽንኩርት ለመግዛት 10 ኪሎ ብር ተሸክሞ መሄድ ነው፤ የከፍታው ዘመን መገለጫ። አይ ሀገሬ በመፈክር ሳይሆን በተግባር ከፍ የምትይው መቼ ይሆን?» ሲል የብር አቅም መዳከምን መንግሥት በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ይዞት ከተነሳው መፈክር ጋር በማያያዝ ጠይቋል። 

ኤሚ ደሚቱ ደግሞ «ከፍታ አሉ ከፍታ አፍ እንደመክፈት ቀላል መስሏቸው የከፍታ ዘመን አሏ» ብሏል። 

ሞሐመድ ነጋ ፦ «‘ልማታዊ ባለ ለሀብቶችን ለማበረታታት በጨዋነት ዝም ያለውን ህዝብ መርገጥ !!! እንዲህ ነው ፍትህአዊነት...» የሚል አስተያየት ሰጥቷል።  
ቢኒ ማን የአይኒ በበኩሉ፦ «100 ብር ቢገባ አንድ ዶላር ትለምዱታላቹ፤ 3 ቀን ዋይ ዋይ ከዛ በቃ!!»

«ኢህአዴግን ያቆይልን እንጂ ዚምባቡዌ ላይ መድረሳችን አይቀርም» ያለው ራስ ዳሸን ነው።» ዚምባብዌ እንደ ብሉምበርግ ዘገባ ከሆነ የዛሬ ስምንት ዓመት ግድም መገበያያ ገንዘቧ እጅግ ከፍተኛ ግሽበት ገጥሞት ነበር። ከፍተኛ ጣሪያ በነካው ግሽበት ምክንያትም ዚምባብዌ ዋጋቢስ የኾነው የመገበያያ ገንዘቧን ከአገልግሎት ውጪ ለማድረግ መገደዷ ይታወሳል።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች