የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት በኢስታምቡል ቱርክ | ዓለም | DW | 19.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት በኢስታምቡል ቱርክ

ቱርክ ኢስታንቡል ከተማ ውስጥ በአጥፍቶ ጠፊ በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት ቢያንስ 5 ሰዎች ሲገደሉ 36 ደግሞ መቁሰላቸውን የሀገሪቱ መንግሥት አስታወቀ። አደጋው የደረሰው በኢስታምቡል ከተማ ወደ ዋናው የመንገድ ዳር የገበያ ማዕከል በሚያቀናው ኢስቲክላል መንገድ ላይ ነው።

በአጥፍቶ ጠፊ ጥቃቱ ከተገደሉት ሰዎች መካከል ሦስቱ እስራኤላውያን አንዱ ኢራናዊ መሆናቸው ተዘግቧል። ከቁስለኞች መካከል ደግሞ 12 ያህሉ የውጭ ሀገር ዜጎች መሆናቸውን የቱርክ የጤና ሚንሥትር አስታውቋል። የእስራኤል መንግሥት ጉዳት የደረሰባቸውን የሀገሩን ዜጎች ወደ እስራኤል ለማጓጓዝ ሁለት አውሮፕላኖችን ወደ ቱርክ መላኩ ተሰምቷል።

የቱርክ መንግሥት ለጥቃቱ ተጠያቂ የሚያደርገው ራሱን «እስላማዊ መንግሥት» ሲል የሚጠራው አማፂ ቡድንን ወይም የኩርዶች የሠራተኞች ፓርቲን በእንግሊዝኛ ምህፃሩ (PKK) ነው። ለጥቃቱ እስካሁን ኃላፊነት የወሰደ ቡድን የለም።

በአሁኑ ወቅት በቱርክ የፀጥታው ሁኔታ የተረጋጋ አይደለም። ፖሊስ አደጋ የደረሰበትን ቦታ አጥሮ በሂሊኮፕተር ቅኝት ማድረጉ ተጠቅሷል። ጥቃቱ በደረሰበት አካባቢ የነበሩ ፖሊሶች እንደተናገሩት ከሆነ፦ አንድ ማንነቱ ያልታወቀ ግለሰብ ኢስቲክላል እና ባሎ ሶካክ ጎዳናዎች ጠርዝ ላይ በታጠቀው ፈንጂ ነጉዷል። የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃt የደረሰበት አካባቢ የክፍለ ከተማው አስተዳደር ጽ/ቤት ይገኝበታል ተብሏል።

ሰኞ እለት የሚከበረው የኩርዶች አዲስ ዓመት በተቃረበ ቁጥር ሌሎች ጥቃቶች ይጣሉ ይሆናል የሚል ስጋት አለ። ባለፈው እሁድ እና ከአንድ ወር በፊት አንካራ ላይ በደረሱ ጥቃቶች ከ60 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ባለፉት ጊዜ ለደረሱት ሁለት ጥቃቶች ጽንፈኛው የኩርዶች የሠራተኞች ፓርቲ ኃላፊነት ወስዶ ነበር።

ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተዛማጅ ዘገባዎች