የአዲስ አበባ ዋሽንግተን መቃቃር ኢትዮጵያን እንዴት ይጫናል? | ኤኮኖሚ | DW | 10.11.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

የአዲስ አበባ ዋሽንግተን መቃቃር ኢትዮጵያን እንዴት ይጫናል?

የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት በድርድር እንዲቋጭ ግፊት በማድረግ ላይ የሚገኙት ጄፍሪ ፌልትማን ባለፈው ሳምንት መፍትሔ ካልተበጀ አገራቸው ማዕቀብ ልትጥል እንደምትችል ጥቆማ ሰጥተዋል። በአዲስ አበባ በተካሔደ ሰልፍ ላይ የአጎዋን ጉዳይ የጠቀሱት ከንቲባ አዳነች አቤቤ "ዕርዳታ እና ብድር ነጻነታችንን የሚገፈን ከሆነ፤ነጻነታችንን አንገብርም" ብለው ነበር

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:59

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የአዲስ አበባ ዋሽንግተን መቃቃር ኢትዮጵያን እንዴት ይጫናል?

ለኢትዮጵያ ቀውስ መፍትሔ ፍለጋ ከናይሮቢ አዲስ አበባ ሲመላለሱ የሰነበቱት የአሜሪካው ልዩ ልዑክ ጄፍሪ ፌልትማን ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ የሰላም ማዕከል ባሰሙት ዲስኩር አገራቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ያላት ግንኙነት ክፉኛ ለመሻከሩ ጥቆማ ሰጥተዋል። አምባሳደር ፌልትማን ወደ አዲስ አበባ ከማቅናታቸው በፊት ባለፈው ጥቅምት 28 ቀን 2014 ዓ.ም በተካሔደው እና አንድ ሰዓት ገደማ በዘለቀው መርሐ-ግብር በአለፍ አገደም አንድ አመት የሞላውን የኢትዮጵያ ቀውስ ዑደት እና በሁለቱ አገሮች ግንኙነት ላይ የፈጠረውን መቃቃር ዘርዝረዋል። 

አምባሳደር ፌልትማን የኢትዮጵያን መንግሥት መውቀስ ከመጀመራቸው በፊት በዲስኩራቸው አገራቸው እያደገ ነው የሚል ተስፋ የጣለችበት ግንኙነት ሁለቱንም አገሮች ይጠቅማል የሚል ተስፋ በዋሽንግተን ሰዎች ዘንድ እንደነበር አስረድተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከመያዛቸው በፊት እና በኋላ አሜሪካ ለኢትዮጵያ አደረገች ያሉትንም ድጋፍ ዘርዘር በማድረግ አቅርበዋል።

በጎርጎሮሳዊው "ከ2016 እስከ 2020 ዓ.ም ባሉት አመታት ዩናይትድ ስቴትስ በልማት እና በሰብዓዊ እገዛ ከ4.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አቅርባለች። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አመራር የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማጠናከር በኢኖቬቲቭ መርሐ-ግብሮች የግሉን ዘርፍ እድገት እና ኢንቨስትመንት ለማስፋፋት ያለመውን የጠቅላይ ሚኒስትሩን የኤኮኖሚ ማሻሻያዎች ለመደገፍ [የፕሬዝደንት ጆ ባይደን] አስተዳደር እና [የአሜሪካ] ኮንግረስ በአዲስ የልማ ት እገዛ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር አቅርበዋል" ሲሉ ተናግረዋል። 

"ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዴሞክራሲያዊ አስተዳደር በሰጡት ትኩረት መሠረት በዩናይትድ ስቴትስ የሚደገፉ የአቅም ግንባታ መርሐ-ግብሮች የፍትህ እና የምርጫ አካላትን እና የጠቅላይ አቃቤ ህግን ነፃነት ለማጠናከር ሰርተዋል። ሌላው ቀርቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያራመዱት ዕርቅ በኤርትራ እና በአሜሪካን ግንኙነት ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ፈጥሮ ሊያሻሽለው ይችል ይሆናል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር" ሲሉ ተደምጠዋል። 

Jeffrey Feltman UN-Untergeneralsekretär

በምሥራቅ አፍሪካ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ጄፍሪ ፌልትማን

ፌልትማን እንዳሉት የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ግንኙነት "መሰንጠቅ" የጀመረው ዋሽንግተን እና የዓለም ባንክ በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ለሚወዛገቡት ሶስት አገሮች የሥምምነት ረቂቅ ባዘጋጁበት ወቅት ነው።  ለኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ የተዘጋጀው የሥምምነት ረቂቅ በአዲስ አበባ ውድቅ ሲደረግ የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር "ኢትዮጵያ ተቃውሞዋን ቆም ብላ ልታጤን ትችላለች" በሚል እሳቤ አሜሪካ ከምትሰጠው ድጋፍ የተወሰነው ከልክሎ ነበር። ክልከላው የፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር ሥልጣን ሲይዝ ተነስቷል። 

ከአንድ አመት በፊት በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት ልዕለ ኃያሏ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወዳጅነት መልሶ አሻክሮታል። የጆ ባይደን አስተዳደር "በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል እያደገ የሔደው ቀውስ አሳስቦት እንደነበር የተናገሩት ፌልትማን "ለአገሪቱ መረጋጋት እና ለሕዝቡ አደገኛ ዳፋ ይኖረዋል" የሚል ሥጋት ተጭኖት እንደነበር አስረድተዋል።  

ከዚያ በኋላ ከዋሽንግተን በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) "ግጭቱን እንዲያቆሙ፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲፈቅዱ እና የሰላማዊ ሰዎችን ደሕንነት እንዲጠብቁ" ተደጋጋሚ ጥሪዎች ቀረቡ።  ግጭቱ እየተባባሰ ሲሔድ መፍትሔ እንዲፈለግለት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚደረረገው ጫና በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ እየበረታ ሲሔድ ታይቷል። 

ጦርነቱ አንድ ዓመት ሲሞላው "አሜሪካ እና ሌሎች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያላቸው ግንኙነት በነበረበት ሊቀጥል አይችልም። ወታደራዊው ግጭት እየተስፋፋ ከአፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች አንዷ የሆነችውን አገር መረጋጋት እና አንድነት አደጋ ላይ ሲጥል እና የዜጎቿን መሠረታዊ ደሕንነት ሲያሰጋ የነበረን ጥሩ ወዳጅነት ዘላቂ አይሆንም። ዩናይትድ ስቴትስ እና ሌሎች ለጋሾች መንግሥትን ከዚህ ጎጂ አካሔድ ለመመለስ ከፍተኛ መጠን ያለው የልማት ዕርዳታ ኢትዮጵያን ከልክለዋል" ሲሉ በምሥራቅ አፍሪካ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ጄፍሪ ፌልትማን ተናግረዋል።

  

በፕሬዝደንት ጆ ባይደን ውሳኔ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የዕድገት እና ዕድል ድንጋጌ (African Growth and Opportunity Act) በኩል ሸቀጦቿን ለአሜሪካ ገበያ የማቅረብ ዕድሏን ከታኅሣሥ 23 ቀን፣ 2014 ጀምሮ ታጣለች። በኢትዮጵያ የቴሌኮም ፈቃድ ላገኘው እና በሳፋሪኮም ለሚመራው የአምስት ኩባንያዎች ጥምረት የአሜሪካው ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (DFC) አስቀድሞ ቃል የገባውን 500 ሚሊዮን ዶላር አዘግይቷል። የኬንያው ቢዝነስ ዴይሊ ጋዜጣ እንደዘገበው ኮርፖሬሽኑ ከውሳኔው የደረሰው "በትግራይ ክልል ያለው አለመረጋጋት የፈጠረውን እርግጠኝነት ማጣት" እንደ ምክንያት በመጥቀስ ነው። 

"…በአጎዋ ሊያስፈራሩን ሞከሩ…" ከንቲባ አዳነች አቤቤ 

አሜሪካ የኤኮኖሚ እና የጸጥታ እገዛዋን ባለፈው ግንቦት ከከለከለች በኋላ ኢትዮጵያ ዋሽንግተን "በውስጥ ጉዳዬ ጣልቃ እየገባች ነው" ስትል ወቅሳለች። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በወቅቱ ባወጣው መግለጫ የአሜሪካ ዕቀባዎች ከቀጠሉ አገሪቱ "ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ያላትን ግንኙነት እንደገና ለመገምገም" እንደምትገደድ አስጠንቅቆ ነበር። ይኸ ደግሞ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አገላለጽ ከአዲስ አበባ እና ከዋሽንግተን "የሁለትዮሽ ግንኙነት ባሻገር አንድምታ ሊኖረው ይችላል።" 

ባለፈው እሁድ በአዲስ አበባ የተካሔደው እና ከፍተኛ ሕዝብ የተሳተፈበት ሰልፍ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት የደረሰበትን ደረጃ ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል። የሰልፉ ተሳታፊዎች አሜሪካንን የሚወቅሱ መፈክሮች ይዘው ታይተዋል። ትዕግሥት ለማ የተባሉ የሰላማዊ ሰልፉ ተሳታፊ "በአፍጋኒስታን እንዳደረጉት ሁሉ አገራችንን ለማፍረስ ይፈልጋሉ። አይሳካላቸውም። እኛ ኢትዮጵያውያን ነን" ሲሉ አሜሪካን የወቀሱበትን አስተያየት ለሬውተርስ ሰጥተዋል። ለሰልፈኞቹ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ካነሷቸው ሐሳቦች መካከል በቀጥታ አሜሪካንን የተመለከቱ ይገኙበታል። 

"የአድዋ ልጆች መሆናችንን ረስተው በአጎዋ ሊያስፈራሩን ሞከሩ። አድዋ ነጻነት ነው። አጎዋ ግን ዕርዳታ ነው። ዕርዳታ እና ብድር ነጻነታችንን የሚገፈን ከሆነ፤ ነጻነታችንን የሚያስገብረን ከሆነ፤ ነጻነታችንን አንገብርም። ድህነታችንን ይዘን እንሰራለን" ሲሉ አዳነች አቤቤ ተደምጠዋል። 

የአፍሪካ ኅብረት እና አሜሪካ በልዩ ልዑካኖቻቸው ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ እና ጄፍሪ ፌልትማን በኩል አንድ አመት የዘለቀውን የኢትዮጵያ ጦርነት በተኩስ አቁም እና ድርድር ለመቋጨት ግፊት እያደረጉ ነው።  ይኸን ግፊት የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት፣ የአውሮፓ ኅብረት እና የኢትዮጵያ ጎረቤት ኬንያ ጭምር ተቀላቅለውታል። እንዲያም ሆኖ መፍትሔ ሊበጅ ካልቻለ አሜሪካ ተጨማሪ ማዕቀብ ልትጥል እንደምትችል ፌልትማን ጥቆማ ሰጥተዋል።

ፌልትማን "ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ባለፈው መስከረም በፈረሙት ትዕዛዝ መሠረት ዩናይትድ ስቴትስ ይኸን ቀውስ በሚያባብሱ እና የሰብዓዊ ዕርዳታ ሥርጭት በሚያስተጓጉሉ ላይ የመጀመሪያውን ማዕቀብ ለመጣል ዝግጁ ነች። በማዕቀቡ ወንጀል የፈጸሙትን ሁሉ ዒላማ እናደርጋለን" ብለዋል። 

ከፖለቲካው ባሻገር

ከሰሜን ወደ ደቡብ የሚንደረደረው ጦርነት ኢትዮጵያን ጥሪት ብቻ ሳይሆን ለውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ-ንዋይ የነበራትን ዕድል ጭምር እየጎዳ ነው። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የምጣኔ-ሐብት ባለሙያዎች ግጭቱ በተባባሰባቸው ወራት የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ ንዋይ እየቀነሰ መሔዱን ታዝበዋል። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሲሻክር ከወደ ዋሽንግተን የሚደመጡ መልዕክቶች የባለወረቶችን ፍላጎት የበለጠ የሚያቀዛቅዙ ሊሆኑ ይችላሉ።

አቶ አብዱልመናን መሐመድ "አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷ በሻከረ ቁጥር የምትወስዳቸው እርምጃዎች ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዳያደርጉ ምልክት ይሰጣል። የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የዲፕሎማሲም ጫና እየመጣብን ነው። [ባለወረቶች] ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ኤኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሥጋቶች ሲያዩ ጥሩ ስሜት አይሰጥም። በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ የሚያስቡ ከሆነ ቢያንስ ላይቸኩሉ ይችላሉ፤ ቆም ብለው ሊያስቡ ይችላሉ" ሲሉ ተናግረዋል። 

የአውሮፓ ኅብረት እና አሜሪካ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሥራ አስፈፃሚ ቦርድ አብላጫ ድምጽ አላቸው። በዚህም እነዚህ ልዕለ ኃያላን የዓለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት ፕሮግራሞች እና ክፍያዎች ማገድ ይችላሉ። የዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትን በመሳሰሉ ተቋማት ዋሽንግተን ያላት ተደማጭነት ሌላ ኢትዮጵያን ሊያሰጋ የሚችል ጉዳይ ነው።

"አሜሪካ በሁለቱም ተቋማት ላይ ትልቅ ጉልበት አላት። ለምሳሌ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አሜሪካ 16.5 በመቶ ድምጽ አላት። ይኸ ማለት ከዓለም ከፍተኛው ድምጽ ማለት ነው። ይኸ ማለት ከቻይና ወደ 3 ጊዜ እጥፍ፤ ከእንግሊዝ አራት ጊዜ እጥፍ፤ ከኢትዮጵያ 183 እጥፍ አካባቢ ድምጽ አላት ማለት ነው። ትልልቅ የገንዘብ ተቋማት አሜሪካ በምትፈልገው መልኩ የምታሽከረክራቸው ናቸው። ኢትዮጵያ ከአሜሪካ የሚኖራት ግንኙነት በሻከረ ቁጥር ከእነዚህ የገንዘብ ተቋማት ጋር የሚኖራት ግንኙነት እየሻከረ ሊመጣ ይችላል" ሲሉ ሊኖር የሚችለውን ጫና አስረድተዋል። 

እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic