የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፈተናዎች | ኢትዮጵያ | DW | 17.02.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፈተናዎች

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት ሃዲድ በተሽከርካሪዎች ጉዳት እየደረሰበት ነው። መንገደኞችም የባቡር መከለያ አጥሮችን በመዝለል መሻገር መጀመራቸው ለተሽከርካሪ እና ባቡር ትራንስፖርቱ ስጋት ሆኗል። በአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የመንገድ ደህንነት ባለሙያ ሁኔታው ትኩረት እንደሚያሻው ተናግረዋል።

475 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ የሆነበት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር መደበኛ አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት እክል ገጥሞታል። የመከለያ አጥሩን ዘለው የሚሻገሩ እግረኞች በሰአት80 ኪሎሜትርይጓዛሉ ተብለው የሚጠበቁትን ባቡሮች መጋፋት ጀምረዋል። አቶ ቢኒያም ጌታቸው በአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የመንገድ ደህንነት ባለሙያ ናቸው። « ከሰሜን ወደ ደቡብም ከምዕራብ ወደ ምስራቅም ባለው የቀላል ባቡር ግንባታ ሂደት ላይ እግረኞች ባልተገባ ስርዓት እየዘለሉ እንደሚሄዱ ተረድተናል።» የሚሉት ባለሙያው ራቅ ራቅ ተደርገው የተሰሩት የእግረኞች መሻገሪያዎች እና የመኪና ማዞሪያዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ አለመሆኑን ይናገራሉ።አቶ ቢኒያም ጌታቸው «ነገ ባቡሩ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ አሁን ያለው ልምድ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ በከተማዋ እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ እንዲባባስ ትልቅ አስተዋጽዖ ያደርጋል።» ሲሉ ስጋታቸቸውን ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንገድ ላይ አደጋ ከሚመዘገብባቸው ሃገራት አንዷ መሆኗን የዓለም ጤና ድርጅት ይጠቁማል።በ10,000 ተሽከርካሪዎች ከ70-100 የሞት አደጋ እንደሚደርስ የገልጸው የዓለም ጤና ድርጅት በአደጋ ብዛት አዲስ አበባ ቀዳሚ መሆኗን ያትታል። ደካማ የመንገድ መሰረተ- ልማት፤የማሽከርከርፍጥነት፣የአሽከርካሪዎች ቸልተኝነት፤የመንገድ አጠቃቀም እና የተሽከርካሪዎች የጥራት ጉድለት በምክንያትነት ከተዘረዘሩት መካከል ይጠቀሳሉ።32 ኪሎ ሜትር ገደማ ርዝመት ያለው የባቡር ሃዲድ እና የመከለያ አጥር ገና ከመነሾው በተሽከርካሪዎች ጉዳት እየደረሰበት ነው።በማህበራዊ ድረ-ገጾች የተበተኑ ምስሎች የባቡር ሃዲዱን የመከለያ አጥር ጥሰው በመግባት ጉዳት ያደረሱ ሁለት ተሽከርካሪዎችን አሳይተዋል። አቶ ቢኒያም ጌታቸው የአሽከርካሪዎች የመንገድ አጠቃቀም እና የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር አገልግሎት ትኩረት እንደሚያሻቸው ይናገራሉ።

የአዲስ አበባ የእግረኛ መንገዶች ምቹ አለመሆናቸውን እና በእድሜ የገፉ ዜጎችንና የአካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ አለመሆናቸውን አቶ ቢኒያም ተናግረዋል። በመንገዶቹ ላይ የሚካሄዱ የመንገድ ላይ ንግዶች መንገደኛውን ከተሽከርካሪ ጋር እንዲጋፋ እንደሚያደርገውም አስረድተዋል። የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት ከእግረኞች እና ተሽከርካሪዎች የመንገድ አጠቃቀም የገጠመውን ችግር ለመፍታት የባቡር ትራፊክ አስተዳደር ሕግ ሊዘጋጅ መሆኑ ተሰምቷል። አቶ ቢኒያም ጌታቸው ከዚህ ቀደም የተዘጋጀ የመንገድ አጠቃቀን የሚገዛ ህግ መኖሩን ይናገራሉ።«ከስድስት ወይም ሰባት አመታት በፊት እግረኛን የሚቀጣ ህግ ተግባራዊ ተደርጎ ነበር።የቀረበት ምክንያት መጀመሪያ የግንዛቤ ስርጸቱ በደንብ አልተካሄደም።» በሚል ተግባራዊነቱ መዘግየቱን አስረድተዋል።

አቶ ቢኒያም ጌታቸው የመንገድ አጠቃቀም ግንዛቤው ዝቅተኛ ቢሆንም እውቀቱ ያላቸውም ቢሆኑ ቸልተኝነት እንደሚታይባቸው ያስረዳሉ። የመንገድ አጠቃቀሙን ግንዛቤ ከማሳደግ ጎን ለጎን ህጉን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic