የአዲስ አበባዎቹን ስብሰባዎች ያስተጓጎሉት እነማን ናቸው? | ኢትዮጵያ | DW | 21.10.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የአዲስ አበባዎቹን ስብሰባዎች ያስተጓጎሉት እነማን ናቸው?

በአዲስ አበባ ከተማ በሁለት የተለያዩ አካባቢዎች በትላንትናው ዕለት ሊካሄዱ የነበሩ የነበሩ ስብሰባዎች በተደራጁ ወጣቶች ተስተጓጎሉ። በከተማዋ ኮዬ ፈጬ በተባለው አካባቢ በተፈጠረው ሁከት ቢያንስ 2 ሰዎች መጎዳታቸውን የዓይን እማኞች ለDW ተናግረዋል። በአቃቂ ክፍለ ከተማ የወረዳ 9 ንብረት የሆነ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ንብረትም ወድሟል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:44

የአዲስ አበባዎቹን ስብሰባዎች ያስተጓጎሉት እነማን ናቸው?

በኮዬ ፈጬ አካባቢ በተለያዩ ጊዜያት በተደራጁ ወጣቶች መንገድ ሲዘጋ እና የአካባቢውን ነዋሪዎች ለስጋት የሚዳርጉ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ቆይተዋል። ትናንት በዚሁ ስፍራ የተከሰተው ግን ከወትሮው ለየት ያለ እንደነበር እና በሁለት የተደራጁ የወጣቶች ቡድኖች መካከል የተፈጠረ እንደሆነ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ለDW ገልጸዋል። አቶ ደረጀ ቤጊ የተባሉ የዓይን እማኝ የትላንትናው ሁከት የተከሰተው ከሌሎች ስፍራዎች በተሽከርካሪ ተጓጉዘው በመጡ ሰዎች ነው ይላሉ።  

“ትናንት የእና ልጆች በኮዬ ፈጬ ወረዳ 9 ስብሰባ ነበራቸው ፤ የወረዳው ሃላፊዎች እናንተ እዚህ መሰብሰብ አትችሉም ቅሊንጦ ሂዱ አሉዋቸው። ልጆቹን አታለዋቸው ነው ወደዚያ የላኳቸው። እነርሱን ከላኩ በኋላ ግን የአማራ ልጆች እኔ የነፍጠኛ ልጅ ነኝ የሚል ከነቴራ ለብሰው በመምጣት ለእነዚያ የከለከሉትን አዳራሽ ለእነዚህ ፈቀዱላቸው። ይሄ ነው ቁጣ የቀሰቀሰው” ሲሉ ሁከቱን መንስኤ ነው ያሉትን ለDW አስረድተዋል። 

በትናንቱ የኮዬ ፈጬው ግጭት ተሳታፊ የነበረው ወጣት ሂኮ ነገራ እንደሚለው የግጭቱ መነሻ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ፤ የወረዳ 9 አስተዳደር የፈጸመው የማዳላት ተግባር ነው። የኦሮሞ ወጣቶች የኢሬቻ በአል በሰላም መጠናቀቁን ለማብሰር አስቀድመው አዳራሽ ቢጠይቁም እነርሱ ተከልክለው ለአማራ ወጣቶች መሰጠቱ በወጣቶቹ ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል ብሏል። 

“እኛ ቄሮዎች የኢሬቻ በኣል ያለምንም እንከን በሰላም መጠናቀቁን አስመልክተን እርስ በእርሳችን ለመመራረቅ ብለን ነበር ትናንት የወረዳውን አዳራሽ ስንጠይቅ ቂሊንጦ ሂዱ ብለውን ከአማራ ክልል ከጎንደር ተጓጉዘው ለመጡ ወጣቶች አዳራሹን ሰጡ። የመጡትም ወጣቶች የምኒልክ ባንዲራ ይዘው ስብሰባ ሲጀምሩ እኛም መግባት ፈለግን። በዚያው ተረባበሽን” ሲል በዕለቱ ተፈጠረ ያለውን ገልጿል።

ሂኮ የወረዳው አስተዳደር አዳራሹን “ከጎንደር ተጓጉዘው ለመጡ” ላላቸው ወጣቶች መሰጠቱ ወደ ግጭት እንዲያመሩ እንዳስገደዳቸው ቢናገርም የኮዬ ፈጬ ስብሰባን ያዘጋጀው የአማራ ወጣቶች ማህበር አባል የሆኑት አቶ አሰፋ ደለልኝ ለDW እንደተናገሩት ግን በስብሰባው ተሳታፊ የነበሩት በአዲስ አበባ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ናቸው። ማህበሩ የጠራው ስብሰባም ህጋዊ እና በወረዳው አስተዳደር ኃላፊዎች ዘንድም እውቅና የነበረው ነው ብለዋል። ኮዬ ፈጬ ኣካባቢ ትናንት ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት በተመለከተ የወረዳውን ስራ አስፈጻሚን በስልክ ለማነጋገር ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም ስራ አስፈጻሚው ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምላሻቸውን ማካተት አልቻልንም።

ከኮዬ ፈጬው ክስተት ሌላ በትላንናው ዕለት የተቃዋሚው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ የጠራው ስብሰባ እንዲሁ በተደራጁ ወጣቶች ተስተጓጎሏል። የፓርቲው ቃል አቃባይ አቶ ናትናኤል ፈለቀ ለDW እንደተናገሩት ፓርቲው በአቃቂ ክፍለ ከተማ ሳሪስ አካባቢ ከፓርቲው አባላት ጋር ሊያደርገው የነበረው ስብሰባ የተስጓጉለው “ማንነታቸው ባልታወቁ ወጣቶች” ነው።  የሳሪሱን ስብሰባ እንዳይካሄድ ያደረጉት ወጣቶች እነማን እንደሆኑ ለማጣራት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

በአዲስ አበባ በተደጋጋሚ የሚስተዋለው ይህን መሰል የጸጥታ ችግርን በሚፈጥሩ ወገኖች ላይ የከተማዋ ፖሊስም ሆነ የጸጥታ መዋቅር “ተገቢውን እርምጃ አልወሰደም” የሚል ተደጋጋሚ ትችት ይደመጣል። የከተማዋ ፖሊስ የለዘበ አቋም የያዘበትን ምክንያት ለመጠየቅ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን በተደጋጋሚ ብንደውልም ስልኮች ባለመነሳታቸው ሳይሳካ ቀርቷል።

ታምራት ዲንሳ 

ተስፋለም ወልደየስ
   

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች