የአዲስ አመት ተስፋ በኩባ | ኤኮኖሚ | DW | 31.12.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአዲስ አመት ተስፋ በኩባ

ኩባ አገር ዉስጥ ያለዉ ወቅታዊ የምጣኔ ሃብት ሁኔታ ከፈጠረዉ የኑሮ ይዘት የመላቀቅ ተስፋን ሰንቃ በተመሳቀለ ስሜት ነዉ አሮጌዉን 2004 አ.ም. ሸኝታ አዲሱን አመት ለመቀበል ተዘጋጅታለች።

በአገሪቱ የስታትስቲክስ ባለሙያዎች ተጠንቶ የቀረበዉ የምጣኔ ሃብቷ እድገት ሁኔታ የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ የማሻሻል ተስፋን የሚፈነጥቅ ይሆናል ተብሎ ነዉ የታሰበዉ።
ከዚሁጋ በተያያዘም ሶሻሊስቱ ፕሬዝዳንት ፊደል ካስትሮና መንግስታቸዉ ከቬኒዝዌላ መንግስት የግራ ክንፍ ፕሬዝዳንት ሁጎ ቻፌዝና ከቻይና ጋር ከመቼዉም በበለጠ የመቀራረብ ሁኔታ በመፈጠሩ የደስታ ፅዋቸዉን በአዲሱ አመት ዋዜማ ያነሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ካስትሮ በጥቅምት ከቬንዙዌላና ከቻይና ጋር የኒኬልና የነዳጅ ዘይት ኢንዱስትሪን በማሳደግ ረገድ በተፈራረሙት ዉል ሳቢያ ከነበረባቸዉ ችግር ሙሉ በሙሉ አገግመዋል ማለት ይቻላል።
ሆኖም ኩባዉያን በገቢያቸዉ ማነስ ሳቢያ እንኳን አመታዊ በአላትን ከቤተሰቦቻቸዉ ጋር በፈንጠዝያ ለማሳለፍ ቀርቶ የየእለት ኑሯቸውም ለመግፋት መቸገራቸዉን ነዉ የሚገልፁት።
የ65 አመቱ አዛዉንትና ጡረተኛ የሆኑት አንድ አባት የገና በአልን ያከብሩ የነበረዉ ለልጆቻቸዉ ብቻ ሲሉ መሆኑን በመግለፅ አሁን ግን ማክበር እንዳቆሙ ነዉ የገለፁት።
የሳቸዉ አይነቱ ቅሬታ በኩባ የተለመደ ነዉ። ሌላኛዉ የ59 አመት ጡረተኛም የሚያገኙት የጡረታ ገቢ 150ፔሶ ሲሆን ያ ማለት ደግሞ በአገሪቱ ህጋዊ ምንዛሪ150 ዶላር ቢሆንም የሚሰጠዉ አገልግሎት ግን የ6 ዶላር ያህል ብቻ በመሆኑ የእሳቸዉንና የባለቤታቸዉን ፍላጎት ማሟላት እንደማይችል ነዉ የገለፁት።
ይህ እንግዲ በወር በአማካኝ 260 ፔሶ በግምት 10 ዶላር ገቢ የሚያገኝ የሁሉም ኩባዊ ቤተሰብ ችግር ነዉ።
አዛዉንቱ የሚሉት ኩባ ዉስጥ ሁሉም ነገር ዉድ ነዉ። በተናጠል ሲታይ ቀላል የሚመስለዉ የስልክ የኤሌክትሪክና የጋዝ ክፍያ በወር ተጠራቅሞ ሲመጣ ከገቢያቸዉ አንፃር ከአቅም በላይ ሆኖባቸዋል።
ያም ሆኖ እንደ ጤና ያለዉ መሰረታዊ አገልግሎት በነፃ ቢሆንላቸዉም የኑሮ ሁኔታቸዉን የሚፈርጁት ድህነት ዉስጥ ነዉ።
የአዛዉንቱን ቅሬታ የሚደግፉ የአሃዝ መረጃዎችም አሉ። ከአንድ አመት በፊት የአገሪቱ የኤኮኖሚ ምርምር ድርጅት ያካሄደዉ ጥናት ዉጤት እንኢያመለክተዉ በቂ ያልሆነ ገቢና የምግብ እጥረት የሚያስከትለዉ ችግር በኩባ የብዙሃኑን ህይወት የሚያጠቃ ዋናኛ ችግር ነዉ።
የኤኮኖሚ ጠበብቶች እንደሚተነብዩት በቡሽ አስተዳደር በግንቦት የተጣለዉ ወደ ኩባ የመጓዝም የገንዘብ ዝዉዉር እገዳ የአገሪቱን የህዝቡን ኑሮም ሆነ ብሄራዊ የምጣኔ ሃብቷ ሁኔታ ጫና ማሳደሩን በመጪዉ 2005 አ.ም.ም ይቀጥላል።
ይህ ሁሉ ነባሪዊ ሁኔታና ትንበያ እንዳለ ሆኖ ግን በዚህ አመት ብቻ ኩባ 2ሚሊዮን ቱሪስቶችን ለማስተናገድ ችላለች።
የዘይት ክምችትን በተመለከተም ከሃቫና 55ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መኖሩ የታወቀዉ ሃብቷም ከዉጪ በማስገባት ላይ ብቻ የተመረኮዘዉን ሁኔታዋን በመለወጡ ረገድ ተስፋ ያጫረ ሆኗል።
ባለሙያዎች እንደሚሉት ያለዉ ክምችት ከ100 ሚሊዮን ቶን በላይ ሲሆን የስፔን፤ የካናዳ፣ የፈረንሳይ፤ ያስዊድን አገር ኩባንያዎች ለማዉጣት ተፈራርመዋል።
ይህ ነዳጅ ወጥቶ ጥቅም ላይ እስኪዉልም ከቬንዙዌላ ጋር በተፈራረመችዉ ዉል መሰረት ለኩባ መሰረታዊ ፍላጎቶች ለማዋል የሚረዳ 53,000በርሜል የነዳጅ ድፍ ድፍ ታገኛለች።
በተጨማሪም ኩባ፤ ቬንዙዌላና ቻይና ግንባር በመፍጠር ቬንዙዌላ ዉስጥ ከሚመረተዉ የብረት ምርት ኩባ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስችልና ቬንዙዌላም በኩባ ያለዉ የነዳጅ ማጣሪያ የጋራ ባለቤትነት እንዲኖራት ድርድር በመካሄድ ላይ ነዉ።
የነዳጅ ማጣሪያዉ የኩባ የንግድና የምጣኔ ሃብት ተቀዳሚ አጋር ሶቭየት ብረት ከተበታተነች ከዛሬ 14 አመት ወዲህ በጅምር ቀርቶ ነበር።
የኩባ ሌላኛዉ የምጣኔ ሃብቷ የተመሰረተበት የኒኬል ሃብቷንም በተመለከተ ከቻይና ጋር ባደረገችዉ ስምምነትም ለዉጡን በመደገፍ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረዉ ይጠበቃል።
ኩባ በአለም በኒኬል አምራችነታቸዉ የመሪነቱን ስፍራ ከያዚት አገሮች መካከል አንደኛዋ ስትሆን መጪዉ የፈረንጆቹ 2005 ታመርታለች ተብሎ የተገመተዉ 77,000 ቶን ነዉ።
ከዚሁ ጋ ተያይዞም እስካሁን ያለዉ በአንድ ቶን የሚከፈለዉ 14,000 ዶላር ዋጋ አመቱን ሙሉ ይዘልቃል ተብሎ ይጠበቃል። ያ ማለት ደግሞ ኩባ በመጪዉ አመት ከነበረባት ችግር በመጠኑ የምታገገምበት ጥሩ የዉጪ ምንዛሪ ይኖራታል።
አሁን የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆርጅ ቡሽ ለሁለተኛዉ ዙር የስራ ዘመናቸዉ ወደኋይት ሃዉስ ሲገቡ የሚጋፈጡት በተፈራረመችዉ ጠንካራ ዉሎች በመታገዝ ብቻ ሳይሆን ከ20 አመት ወዲህ ባጠናከረችዉ የመከላከያ ኃይሏ በመተማመን ወደ አዲሱ አመት ከምትሸጋገረዉ ኩባ ጋር ይሆናል።