የአዲስ መንግሥት ምሥረታ በጀርመን | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 26.09.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

 የአዲስ መንግሥት ምሥረታ በጀርመን

መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ፓርቲያቸውን ሴዴኡን ወትሮ ከሚታወቅበት የወግ አጥባቂ አስተሳሰብ ወደ ለዘብተኛ እና ወደ ግራ መስመር መውሰዳቸው የመሀል ግራ አቋም ያለው ኤስፔዴም ወደ ቀኝ ማዘንበሉ ፓርቲዎቹ ከቀድሞው ምርጫ ያነሰ ውጤት ለማግኘታቸው በምክንያትነት ይጠቀሳሉ ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:12
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:12 ደቂቃ

አዲስ መንግሥት ምሥረታ በጀርመን

ባለፈው እሁድ አጠቃላይ ምርጫ ባካሄደችው በጀርመን የአዲስ መንግሥት ምሥረታ ሂደት እያነጋገረ ነው። በምርጫው ሁለተኛ ደረጃ ያገኘው እና ላለፉት 8 ዓመታት ከአሸናፊዎቹ ከእህትማማቾቹ የክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት እና የክርስቲያን ሶሻል ህብረት ፓርቲዎች ጋር ጀርመንን ተጣምሮ የመራው የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ፣ ወደፊት ተቃዋሚ እንጂ የመንግሥት አካል አልሆንም ማለቱ እስከዛሬ በፌደራል መንግሥት ደረጃ ያልተሞከረ ጥምረት እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል እየተባለ ነው። በሌላ በኩል ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ በጀርመን ምክር ቤት ቡንደስታግ መቀመጫዎችን ማግኘቱም በሰፊው እያወያያ ነው። ጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ካካሄደች ከሁለት ቀናት በኋላም አዲስ መንግሥት እንዴት ሊመሰረት እንደሚችል ማነጋገሩ ቀጥሏል። በዚህ ምርጫ እህትማማቾቹ የክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት ፓርቲ በጀርመንኛው ምህጻር ሴዴኡ እና የክርስቲያን የሶሻል ህብረት ፓርቲ በጀርመንኛው ምህጻር ሴ ኤስ ኡ 33 በመቶ ድምጽ በማሸነፍ አንደኛውን ደረጃ ሲይዙ የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ደግሞ 20.5 በመቶ ድምጽ አግኝቶ ሁለተኛ ወጥቷል። ይሁን እና እነዚህ

ሁለቱ አውራ ህዝባዊ ፓርቲዎች በእሁዱ ምርጫ ያገኙት ድምጽ ከዛሬ አራት ዓመቱ ውጤት ጋር ሲነፃጸር ዝቅተኛ ነው። የሴ ዴ ኡ እና የሴ ኤስ ኡ የአሁኑ ውጤት በዛሬ 4 ዓመቱ ምርጫ ካገኙት በ8.5 በመቶ ያንሳል፤የኤስፔዴ ደግሞ በ5.2 በመቶ ወርዷል። በአንጻሩ የግራዎቹ ፓርቲ በ0.6 በመቶ ፣ የአረንጓዴዎቹ 0.5 እንዲሁም አማራጭ ለጀርመን የተባለው ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ በ5.9 በመቶ የበለጠ ድምጽ አግኝተዋል። የህዝቡ ድምጽ ከሁለቱ አንጋፋ ፓርቲዎች እየራቀ ለመሄዱ በርካታ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ጀርመን የተማሩት እና የሚሰሩት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር እና የህግ ባለሞያው ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ዋናው ምክንያት መንግሥት ሲመሩ የነበሩት ሁለቱ ፓርቲዎች ልዩ ልዩ ማህበራዊ ችግሮችን መፍታት አለመቻላቸው ነው ይላሉ። 

ከዚህ ሌላ ሁለቱ ፓርቲዎች ለህዝቡ የገቡትን ቃል ወደ ጎን ማለታቸው ለመራጮቻቸው ቁጥር መቀነስ ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን ዶክተር ለማ ገልጸዋል። መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል

ፓርቲያቸውን ሴዴኡን ወትሮ ከሚታወቅበት የወግ አጥባቂ አስተሳሰብ ወደ ለዘብተኛ እና ወደ ግራ መውሰዳቸው የመሀል ግራ አቋም ያለው ኤስፔዴም ወደ ቀኝ ማዘንበሉ ፓርቲዎቹ ከቀድሞው ምርጫ ያነሰ ውጤት ሊያገኙ የቻሉባቸው ምክንያቶች መሆናቸውንም አስረድተዋል።  በዚህ ምርጫ ዋናው አነጋጋሪ ጉዳይ እንደተጠበቀው«አማራጭ ለጀርመን»የተባለው ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ የጀርመን ፓርላማ ውስጥ ለመግባት የሚያስችል ድምጽ ማሸነፉ ነው። ሦስተኛ ደረጃ የያዘው ይኽው ፓርቲ 94 የምክር ቤት መቀመጫዎችን ወስዷል። ፓርቲው ከ16 ቱ የጀርመን ፌደራል ክፍለ ግዛቶች በ13ቱ የምክር ቤት መቀመጫዎች አሉት። ፓርቲው በአሁኑ ምርጫ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ የሴዴኡ እና የሴ ኤስ ኡ መራጮችን ድምጽ ወስዷል። እስካሁን በምርጫ ያልተሳተፉ በእሁዱ ምርጫ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ድምጻቸውን የሰጡ የተጨማሪ አንድ ሚሊዮን ዜጎችን ድምጽም አግኝቷል።  ይህ  እንዴት ሊሳካለት ቻለ? የበርሊኑ ወኪላችን ይላማ ኃይለ ሚካኤል ፓርቲው ያነሳቸው ጉዳዮች የህዝብን ስሜት የሚነኩ መሆናቸው ለድል አብቅቶታል ይላል። ሴዴኡን እና ሴኤሱን ወክለው የተወዳደሩት

የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ቢያሸንፉም በዚህ ምርጫ ያገኙት ውጤት የሚያረካ አልሆነም። ከዚህ ሌላ ለ8 ዓመታት የጀርመን ጥምር መንግሥት አካል የነበረው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ኤስ ፔዴ ከአሁን በኋላ እንደ እስከዛሬው አልቀጥልም፤ ተቃዋሚ ነው የምሆነው ማለቱ ፈተና ውስጥ ከቷቸዋል። ሜርክል አሁን መንግሥት ለመመስረት ያላቸው አንድ አማራጭ ብቻ ነው ይላሉ ዶክተር ለማ ፤ ከሴዴኡ ጋር የሚቀራረብ አቋም ካለው ከነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ እና ከአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ጋር መጣመር። ይህ ዓይነቱ ጥምረትም ከሦስቱ ፓርቲዎች መለያ ቀለም በመነሳት የጃማያካ ጥምረት ይባላል። የሴዴኡ እና የሴኤሱ መለያ ጥቁር የነጻ ዴሞክራቶቹ  ቢጫ የአረንጓዴዎቹ ደግሞ አረንጓዴ በመሆኑ የሶስቱ ቀለም በአንድነት ከጃማይካ ባንዲራ ቀለም ጋር በመመሳሰሉ ነው ይህን ስያሜ ያገኘው። ይልማ  እነዚህ አራት ፓርቲዎች የሚያስማሟቸው ጉዳዮች እንዳሉ ሁሉ የሚለያዩባቸው ነጥቦችም ጥቂት አይደሉም እና የመንግሥት ምሥረታው

በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊሳካ አይችል ይሆናል ይላል። 246 የጀርመን ምክር ቤት መቀመጫዎችን ያገኙት አሸናፊዎቹ ሴዴኡ እና ሴኤስ ኡ ተሳክቶላቸው 80 መቀመጫ ካገኙት ከነጻ ዴሞክራቶቹ እና 67 መቀመጫዎችን ከሚይዙት ከአረንጓዴዎቹ ፓርቲዎች ጋር ከተጣመሩ በአጠቃላይ 393 መቀመጫዎች ይኖሩዋቸዋል። ይህም መንግሥት ለመምራት ከሚያስችለው ከ355 መቀመጫዎች በላይ ነው። የመጀመሪያ ሙከራ ይሆናል የተባለው ይህ ጥምረት ሳይሆን ከቀረ ደግሞ ሴዴሱ እና ሴኤስኡ ከኤፍዴፔ ጋር አናሳ መንግሥት ሊመስርቱም ይችላሉ እንደ ዶክተር ለማ። ይህ የማይሆን ከሆነ ደግሞ የመጨረሻው አማራጭ ዳግም ምርጫ ማካሄድ ነው የሚሆነው። በዶክተር ለማ አስተያየት የመጨረሻዎቹ ሁለት አማራጮች ተግባራዊ የሚሆኑ አይመስልም። 

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic