1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዲስ ህገ መንግስት ጥሪ ለኢትዮጵያ

ሐሙስ፣ ሰኔ 20 2016

ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ተከስቶባቸዋል ካሉት አስከፊ ችግር ለማላቀቅ አዲስ ህገ መንግስት መንደፍና መተግበር መሰረታዊ ጉዳይ ነው ሲሉ ተቀማጭነታቸው በአሜሪካ የሆኑ የኢትዮጵያውያን ሲቪክ ድርጅቶች ገለጹ።ድርጅቶቹ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ተቋማት ባሰራጩት መግለጫ፣ አዲስ ህገ መንግስት የሚረቀቅበትን ስልት መንደፋቸውንም አስታውቀዋል።

https://p.dw.com/p/4hZcF
Logo of Ethiopian American Organization, Ethiopiawinnet
ምስል Tariku Hailu /DW

ለኢትዮጵያ የአዲስ ህገ መንግስት ጥሪ

"ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ዲሞክራሲ፣ አንድነትና ልማት ስለሚያስፈልጉ መፍትሔዎች" በሚል ርዕስ መግለጫውን ያወጡት፣ ሰባት የሲቪክ ድርጅቶች ናቸው። በአሜሪካ ከሚገኙት እነዚህ ሲቪክ ድርጅቶች መኻከል ኢትዮጵያዊነት፣ የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት፣ የአሜሪካ ኢትዮጵያውያን የሕዝብ ጉዳዮች ምክር ቤትና የኢትዮጵያውያን ህብረት ይገኙባቸዋል።

ስለጉዳዩ ዶይቸ ቨለ የጠየቃቸው  ዶክተር ዕርቁ ይመር፣የኢትዮጵያዊነት ሊቀመንበር ሲሆኑ፣ ለኢትዮጵያ አዲስ ሕገ መንግስት አሁን ማዘጋጀት ለምን እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።

አንገብጋቢው የህገ መንግስት ጥያቄ

" በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ከገጠማት ችግሮች ዋነኛውና መደበኛው፣ የህገ መንግስቱ ጥያቄ ነው። የህገ መንግስቱ ጥያቄ በጣም በጣም አንገብጋቢ እና ብዙ ሰዎችም የሚጠይቁት፣ በየጊዜው አስተያየት የሚሰጥበት ነው፤ ድርጅቶች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች የሲቪክ ድርጅቶች የሚጠይቁት ነው።

ለእዚህ ምክንያቱ ደግሞ፣ ድርጅቶቹ በመግለጫቸው እንዳብራሩት፣ በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ሰፍኖ የሚገኘው ህገ መንግስት፣ሕዝቡን በቋንቋ እና በጠባብ ዘረኝነት በተመሠረተ ባሉት የክልል ስርዓት ከፋፍሎ፣ ባስከተለው የእርስ በርስ መናቆር፣አለመተማመን፣ መከፋፈል፣ አለመተባበር እጅግ አሰቃቂ ስቃይና እልቂት ስላስከተለ ነው።በፌዴራል ስርዓቱና ህገመንግስቱ ላይ የተደረገ ዳሰሳዊ ጥናት

የህገ መንግስት ጉባዔ

ስለሆነም ብቁ በሆኑ ባለሙያዎች የተሟላ ረቂቅ ህገ መንግስት እንዲዘጋጅና፣አንድ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በጥልቀት እንዲመለከተው ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ለመላው ህዝብ እና ለሚመለከታቸው ድርጅቶች ቀርቦ እንዲመረመር፣ በመጨረሻም ተቀባይነት በሚኖረው ብሔራዊ ጉባኤ ህገ መንግስቱ እንዲጸድቅ የሚያስችል ስልትም ነድፈዋል። "የእኛ ትኩረት፣የህገ መንግስት ለውጥ አስፈላጊነቱ እና እንዴትስ መለወጥ እንዳለበት፣ ሂደቱ ምን መሆን አለበት የሚለውን በተለያዩ ጉባኤዎች አቀርበናል፤በህትመት የወጡ ነገሮችም አሉ።"

የሽግግር ፍኖተ ካርታ

አቶ ገለታው ዘለቀ፣ የኢትዮጵያን ነባራዊ የፖለቲካ ሂደት በቅርበት የሚከታተሉ ሲሆን፣ አማራጭ ዐሳቦች መቅረባቸው ወሳኝ ነው ይላሉ።

Äthiopien Ato Geletaew Zeleke
ገለታው ዘለቀ፤ የፖለቲካ ተንታኝ ምስል Tariku Hailu/DW

" ያነሳሷቸው ነጥቦች ወሳኝ ናቸው።ሽግግር ሲባል መሰረታዊ ነገሮች አሉ። አንደኛው የአመራር ጉዳይ ነው።እና አመራሩ ምን መምሰል ነው ያለበት? ምን ዓይነት ሞዴል መከተል አለብን በተለይ ካለፉት ጊዜያት ተምረን።"

አቶ ገለታው  እንደሚሉት፣ ለኢትዮጵያ አማራጭ ቅርጸ መንግስት ያለው የሽግግር ፍኖተ  ካርታ ያስፈልጋታል።"በፌደራል ስርዓተ መንግስቱ ላይ ያነጣጠረ፣ የህገ መንግስት የማሻሻያ ዐሳብ ነው፤ለውይይት ቁጭ ሲባል እንደ አማራጭ ሆኖ የሚቀርብ ነው፤ ጣምራ ፌዴራሊዝም ይባላል።"

“ህገ መንግስቱን እና ፌደራላዊ ስርዓቱን ለማዳን” በትግራይ የተጠራ ጉባኤ

የጣምራ ፌዴራሊዝም ጠቀሜታ

ይህ የጣምራ ፌዴራሊዝም፣በማንነት ላይ ያለን ሩጫ የሚያስቀር እንደሆንም አቶ ገለታው ያስረዳሉ። "የጣምራ ፌዴራሊዝም ያልኩት፣ በተለይ በማንነቶች መኻከል ያለን እሽቅድምድም፣አንዱ በአንዱ ላይ ሳይረማመድ በዜግነትና በብሔር ማንነት ላይ ያለውን መሽቀዳደም መስመር ፈጥሮ የሚያስተናግድ የፌዴራል ስርዓት ነው።" 

ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት አይኖርም

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ፣ በቅርቡ አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደው ሃገር አቀፍ የምክክር ሂደት ማስጀመሪያ ስነስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣በኢትዮጵያ ሽግግር መንግስት እንደማይኖር መናገራቸው አይዘነጋም።ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሽግግር መንግስት እንዲመሠረት የሚሹ ወገኖች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖረው  በምርጫ የተመሰረተ መንግስት ብቻ ነው ብለዋል። 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ታሪኩ ሀይሉ

ነጋሽ መሀመድ

ፀሀይ ጫኔ