የአዲሲቱ ጋምቢያ ግንባታ ሂደት | አፍሪቃ | DW | 17.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የአዲሲቱ ጋምቢያ ግንባታ ሂደት

ከ22 የአምባገነንነት ዓመታት በኋላ ጋምቢያ አሁን እያንሰራራች ነዉ። በቀድሞዉ ፕሬዝደንት ያህያ ጃሜ ዘመነ ሥልጣን በደል የደረሰባቸዉ ወገኖች አዲሱ የሀገሪቱ መንግሥት ፍትህ እንዲሰጣቸዉ ጥያቄ ጀምረዋል። በትንሽቱ አፍሪቃዊት ሀገር የተፈጸመዉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በእዉነት አጣሪ ኮሚሽን አማካኝነት እንዲፈታ መንግሥት አስቧል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:03

የአዲሲቱ ጋምቢያ ግንባታ ሂደት

ለዚህ ደግሞ አዲሱ መንግሥት ትዕግሥት እንዲኖር እየለመነ ነዉ። መስኮቱ በባለ አበባ መጋረጃ ተሸፍኗል። ጋምቢያዊዉ ጋዜጠኛ ማዴ ሳሲ ሻዩን ፉት እያለዙሪያዉን ቃኘ። ከመናገሩ አስቀድሞ ተነሳና በመጋረጃዉ መስኮቱ በደንብ መሸፈኑን፣ በየጥጉም ምንም ነገር አለመኖሩን አረጋገጠ፤ ከዚያም ንግግሩን ማንም እንደማይሰማዉ ጠየቀ። የአገዛዙ ጆሮዎች በሁሉም ቦታ ናቸዉ። አንዲት ትችት አዘል አስተያየት በማግስቱ የገባበት ደብዛዉ እንዲጠፋ ለማድረግ በቂ ናት። የዛሬ 23 ዓመት በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን የያዙት አምባገነኑ ያህያ ጃሜህ ብሔራዊ የስለላ ተቋሙን እና የፖሊስን ኃይል በመጠቀም የምክር ቤት አባላት እና የአገዛዙ ጠላቶች የሚሏቸዉ ትችት እንዳይሰነዝሩ ሲያስፈራሩና ሲዋክቡ ቆይተዋል። ለዚህ የተጋለጡም በአብዛኛዉ ተቺ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች እና ግብረ ሰዶማዉያን ሲሆኑ ለጃሜህ እነዚህ የጋምቢያን ሃይማኖት፣ ባህል እና ወግ የጣሱ ናቸዉ። ለአብዛኞቹም ስደት ብቸኛዉ አማራጭ ነበር። ትንሺቱ አፍሪቃዊት ሀገር 1,5 ሚሊየን ዜጎች ብቻ ቢኖሯትም፤ በአህጉሩ ሲታይ ከፍተኛ ስደተኛ ዜጎች አሏት።

አብዛኞቹም ጋምቢያ እስር ቤቶች ዉስጥ ሊደርስባቸዉ ከሚችል ቁም ስቅል ያመለጡ መሆናቸዉ ይነገራል። ሀገሪቱም ብትሆን እረጭ ያለች ነበረች። ፖለቲካዊ አስተያየቱን ለመግለጽ ለሚፈልግ ጣጣዉ ብዙ ነበር። ከእነሱ አንዱ ማዲ ሲሲ ነዉ። እሱና ባልደረቦቹ የዛሬ 11 ዓመት ዘ ኢንዲፔንደንት በተሰኘዉ የጋምቢያ ጋዜጣ ላይ መንግሥትን የሚተች ዘገባ አተሙ። ጋዜጣዉ ተዘጋ ጋዜጠኞቹም በሙሉ ታሠሩ። ለአንድ ቀን ተኩል ምርመራ ተካሄደባቸዉ፤ የጋዜጣዉ ዋና አዘጋጅ ሲሲ ብሔራዊ የስለላ ተቋሙ ሥር ወዳለ አሰቃቁ ወህኒ ቤት ተወረወረ። እዚያ ለሦስት ሳምንታት ቆይቷል። በየዕለቱ ከተኛበት ጭንብል ባለጠለቁ ሰዎች እየተወሰደ ተደብድቧል፣ ቁም ስቅልም ደርሶበታል። መንግሥት ለማን እንደሚሠራ ማወቅ ነዉ የፈለገዉ። 
«በጣም የሚዘገንን ተሞክሮ ነዉ ያለኝ፤ ለሦስት ሳምንት እስር ቤት ነበርኩ። በጣም አስከፊ ተሞክሮ ነዉ። በየቀኑ ሁለት ጊዜ እንደበደብ ነበር፤ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ወደተኛንበት መጥተዉ ያስወጡን እና ወደምንደበደብበት ስፍራ ይወስዱናል። ሁልጊዜም ጭምብል ያጠልቁ ነበር።»
ጋዜጠኛዉ ከዉጭ በሚያገኘዉ ገንዘብ እየተደረገፈ የጃሜህን መንግሥት ለማናጋት ይሠራል የሚወለዉ ወሬ ብዙ ተዛምቷል። ዕድል ቀናዉ እና ከሦስት ወራት በኋላ ከእስር ተለቀቀ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ በደረሰበት ስቃት እየሰጋና እየማቀቀ ፍትህ እየጠበቀ ይኖራል። 
አዲሲቱ ጋምቢያ
ይህቺ እስከ ጎርጎሪዮሳዊዉ 2016ዓ,ም ድረስ የነበረችዉ አሮጌዋ ጋምቢያ ናት። ለ23ዓመታት በዚያ መልክ የቆየችዉ የጃሜህ ጋምቢያ በአዳማ ባሮ አማካኝነት ጥምረት በፈጠሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የጋራ ጥረት ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሻግራለች። ፍርሃትም ሆነ ጭቆና የሌለባት ጋምቢያ፤ ተደብቆ ፖለቲካ የማይወራባት ጋምቢያ ሆናለች የሚለዉ የብዙዎች ተስፋ ነዉ። እንቅስቃሴ በሚበዛበት ምዕራባዊ መናፈሻ አካባቢ በሚገኘዉ የአዉቶቡስ መቆሚያ ሁለት ወጣቶች የተለያዩ ፓርቲዎች የመሠረቱት ጥምረት ይዘልቃል ወይስ አይዘልቅም በሚል የጋለ ክርክር ይዘዋል። በ20ዎቹ የዕድሜ መጀመሪያ የሚገኙት ወጣቶች በመሪነት የሚያዉቁት የጋምቢያዉን ገዢ ያህያ ጃሜህን ብቻ ነዉ። አሁን በግልጽ ለሀገራቸዉ መጻኤ ዕጣ እና ለአዲሲቱ ጋምቢያ ይነጋገራሉ። ስጋት ያደረባቸዉ ቤተሰቦች በጋዜጣ ላይ ዘመዶቻቸዉ ምን እንደገጠማቸዉ በይፋ ይጠይቃሉ። ማብራሪያም ይሻሉ። በፖለቲካ ጉዳይ የተከሰሱ ሰዎች ጉዳይ የሚመለከተዉ ባንጁል የሚገኘዉን የፍትህ ሚኒስቴር ነዉ። አዲሱ የጋምቢያ ፍትህ ሚኒስትር አቡበከር ታምባዱ እዉነት አጣሪ ኮሚሽን ማቋቋም ከሁሉም ቅድሚያ የሚሠጡት ተግባር ነዉ።

 
«ባለፈዉ ለተፈጸመዉን የሰብዓዊ መብት ጥሰት የግድ አንድ ነገር ማድረግ ይኖርብናል። ይህን ለማከናወን ማድረግ የሚገባን ግንባር ቀደሙ ነገር ደግሞ የእዉነት እና የእርቅ ኮሚሽን ማቋቋም ነዉ።»
እንዲህ ያለዉን ኮሚሽንለማቋቋም አሁን የጋምቢያ የፍትህ ሚኒስቴር የሌሎች ሃገራትን ተሞክሮ እያጠና ነዉ። በተለይ ደግሞ ለዓመታት ከነበሩበት የአምባገነን ሥርዓት እና የጦርነት ሂደት ወጥተዉ ወደ ዴሞክራሲ መሸጋገር ከቻሉ ሃገራት ማለት ነዉ። ጥሩ ለምሳሌ ደቡብ አፍሪቃ ከአፓርታይድ አገዛዝ በኋላ በእዉነት አጣሪ ኮሚሽን አማካኝነት ለጥፋተኞች ምህርት በማድረግ ትታወቃለች። የኮሚሽኑ ትኩረት በማኅበረሰቦች መካከል እርቅ ማዉረድ  እንጂ ቅጣት መጣል አልነበረም። ይህ ለጋምቢያ ምሳሌ ይሆን ይሆን? የፍትህ ሚኒስትር ታምባዱ ደቡብ አፍሪቃ እና ጋምቢያ የባህልና የታሪክ ልዩነት እንዳላቸዉ በመጥቀስ የተወሰነ ተምሳሌት ብቻ በመያዝ ሥራዉን መጀመር እንደማይቻል ያስረዳሉ። የተሻለ ሥራ ለመሥራት እንዲችሉም ህዝቡ ትዕግሥት እንዲኖረዉ ይማጸናሉ።
«ጠንክረን እየሠራን ነዉ። ለዚህ ለዉጥ ድምፃቸዉን በሰጡ ጋምቢያዉያን ዘንድ ብዙ የመጠበቅና ትዕግሥት የማጣት ነገር አለ። ይህን መረዳት ይቻላል። ነገር ግን አዲስ መንግሥት ስለተመረተ ብቻ ሊደረግ የታሰበዉ ማሻሻያ በአንድ ጀንበር ሊከናወን እንደማይችል እንዲረዱ በበኩላችን ለማድረግ እየሞከርን ነዉ።»


ሸዋዬ ለገሰ / ቪንሰንት ሀገር
ነጋሽ መሃመድ 
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች