የአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር አዲስ ካቢኔ | ኢትዮጵያ | DW | 20.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር አዲስ ካቢኔ

የኢፊዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዛሬዉ ዕለት የ16 የካብኔ አባላትን ሹመት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፀድቀዋል። የካብኔ አባላት ዝርዝር ዉስጥ 10 ሩ አዳዲሶችና 6 ቱ የቦታ ለዉጥ የተካሄደባቸዉ ናቸዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:21

«ህዝቡ መታወቂያ ለማዉጣት ዘመድ አዝማድ ማስደወል የማያስፈልገዉ ዜጋ መሆን ይፈልጋል» ጠ/ሚ አብይ አህመድ


ምክር ቤቱ የአስፈፃሚ አባላትን ስልጣንና ተግባር የሚወሰነዉን  ረቂቅ አዋጅ ማፀደቅና የምክር ቤቱን አፈ ጉባኤ ምርጫም አከናዉኗል።የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር  አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ከአንድ አመት ተኩል በፊት ነባሩን ካቤኔ አፍርሰዉ ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች የበዙበት የሊህቃን ካቤኔ አቋቁመዉ ነበር።ይሁን እንጅ ይህ ካብኔ በሀገሪቱ የተቀሰቀሰዉን ተቃዉሞ ማርገብ ሳይችል ቆይቷል።  በዛሬዉ ዕለት ደግሞ የአስፈፃሚ አካላትን ሪፖርት በዝርዝር  በመገምገም  ነባሩን  ካብኔ የህዝቡን ጥያቄ በአግባቡ ሊመልስ በሚችል  አዲስ ካቤኔ መተካቱን ነዉ ጠቅላይ ሚንስትሩ ዶክተር አብይ አህመድ የተናገሩት። 
ጠቅላይ ሚንስትሩ በዛሬ የምክር ቤት ዉሏቸዉ በሀገሪቱ ከሚገኙት 21 ሚንስትር መስሪያ ቤቶች ዉስጥ ለ14ቱ አዳዲስ ሚንስትሮች የሾሙ ሲሆን የአቃቤ ህግና የመንግስት ጉዳዮች ኮሚኒኬሽን ፅ/ቤት እንዲሁም አዲስ የምክር ቤቱን አፈ ጉባኤ ሹመት አስፀድቀዋል።የስልጣን ሽግሽጉ የተካሄደዉ የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግርን በማስቀረት የህዝቡን ጥያቄና ቅሬታ ለመፍታት መሆኑንም ጠቅላይ ሚንስትሩ ገልፀዋል። 


የአቅም ችግር ያላቸዉንና  ለመማር ዝግጁ የሆኑ ተሿሚ ሚንስትሮችን ለመደገፍ ዝግጁ ነዉ ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ሁለት «ቀይ መስመር »ያሏቸዉን  የሙስናና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ግን ጥብቅ ክትትል  የሚደረግ  መሆኑን  ነዉ ጠቅላይ ሚንስትሩ አስረግጠዉ የተናገሩት።«ህዝቡ የተለዩ አገልግሎት አይጠብቅም ።የሚጠብቀዉ መታወቂያ ለማዉጣት ጭማሪ ገንዘብ የማይጠይቅ ፤መታወቂያ ለማዉጣት ዘመድ አዝማድ ማስደወል የማያስፈልገዉ ዜጋ መሆን ይፈልጋል።ይህንን ማረጋገጥ ከነበሩትም ከሚሾሙትም በጥብቅ መንግስት የሚፈልግ መሆኑን በአንክሮ ማሳሰብ እፈልጋለሁ »ካሉ በኋላ ሁለተኛዉን ያስከትላሉ።«ሁለተኛዉ በቀይ መስመርነት ልናልፈዉ የማንችለዉ ጉዳይ በተደራጀና ባልተደራጀ ሁኔታ ህዝቡን እያሰቃዬ ያለዉ የሙስና ሁኔታ ነዉ ።የሙስና ሁኔታ ራሳችን ባለመሳተፍ ብቻ ሳይሆን በምንመራዉ መስሪያ ቤት ለብክነት የሚዳርግ ጊዜን ገንዘብን ንብረትን የሚያወድሙ ሁኔታወች በጥብቅ ክትትል የመምራት ሃላፊነት ቀይ መስመር መሆኑንና የተለዬ ክትትል የሚሻ መሆኑን ለነበሩትም ለአዲሶቹም ማሳሰብ እፈልጋለሁ።»


በሀገሪቱ ላለፉት ሶስት ዓመታት የዘለቀዉ  አመፅ ጠቅላይ ሚንስትሩ  ከጠቀሷቸዉ ጉዳዮች ባሻገር ሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮችን  የሚያካትት በመሆኑ  የህዝቡን ቅሬታ በመልካም አስተዳደርና ሙስናን በመዋጋት  ብቻ መፍታት አይቻልም የሚል አስተያየት  በአንዳንዶች ዘንድ ይነሳል። በኢትዮጵያ  የዉጭ ግንኙነት ስትራቴጅካዊ ጥናት ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ  አቶ አበበ አይነቴ እንደሚሉት ግን ምንም እንኳ የነባሩ ካቤኔ አባላት  የፖለቲካ አመራር  ይሁን የአቅም ችግር  ተለይቶ ባይታወቅም  እንዲሁም አዲሶቹ አመራሮች ለዉጥ ያመጣሉ ወይም አያመጡም የሚለዉ ጉዳይ አነጋጋሪና በጊዜ የሚታይ ቢሆንም  ጠቅላይ ሚንስትሩ ያሰመሩባቸዉ ሁለት ጉዳዮች ግን ተገቢና አስፈላጊ መሆናቸዉን አብራርተዋል።
ያምሆኖ ግን ህገ- መንግስቱን በማክበርና በማስከበር እንዲሁም በትክክል ወደ መሬት እዲወርድ ማድረግ የሚፈለገዉን ለዉጥ ለማምጣትም ይሁን በሀገሪቱ የሚታየዉን ችግር ለመቅረፍ የአዲሱ ካቤኔ ዋና ጉዳይ መሆን እንዳለበት ነዉ አቶ አበበ የገለፁት።
የሀገር መከላከያ ሚንስቴር፣የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ሚንስቴር  የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት  የኢትዮጵያ ገቢወችና ጉሙሩክ ባለስልጣንና   የበዛሬዉ ዕለት ጠቅላይ ሚንስትሩ የቦታ ሽግሽግ ካደረጉባቸዉ ቦታወች መካከል ይገኙበታል።ለመሆኑ ነባሩንና ልምድ ያለዉን አመራር በአዲስ መተካት በራሱ ለዉጥ ያመጣልን አቶ አበበ አይነቴ።  «እንግዲህ ሀገሪቱ በለዉጥ ሂደት ላይ ነዉ ያለችዉ።

የለዉጥ ፍላጎት አለ።ችግሮቹ ናቸዉ የለዉጥ ፍላጎት እንዲመጣ ያደረጉት።መንግስትም ያንን ለዉጥ ለማሳካትና የህብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ በሚያስችል ቁመና «ራሴን አዘጋጅቻለሁ »ለሚለዉ ማሳያ አዳዲስ ፊቶችን ማምጣትና ባሉት ላይም ሽግሽግ ማድረጉ እንደሆነ ነዉ ከዛሬዉ ሂደት መገንዘብ የሚቻለዉ ባለፈዉ አንድ ወር ጌዜ ዉስጥ ለዉጡ የስልጣን መተካካቱ ከተደረገ በኋላ በአጠቃላይ በሀገሪቱ የተፈጠረዉ መረጋጋት እና የሰላም ሁኔታ ከቀጠለ ሀገሪቱ በተረጋጋ ሁኔታ ወደፊት ለመስፈንጠር በቂ ምክንያትና አንድ አጋዥ ሀይል ሊሆን እንደሚችል አመላካች ነዉ።»
የኢትዮጵያ  የሕዝብ የተወካዮች የምክር የአፈ ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳን መልቀቂያ ተቀብሎ በምትኩ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚልን ሾሟል።የአሳ ሀብት ሚንስቴርን በማጠፍም የግብርናና የዕንስሳት ሀብት ብሎ የተሰየመ ሲሆን   ከ16 ቱ አዳዲስ የካቢኔ አባላት ዉስጥም አራት ሴቶችም በሹመቱ መካተታቸዉን ለማወቅ ተችሏል።

 

ፀሐይ ጫኔ

ነጋሽ መሀመድ

 

Audios and videos on the topic