የአዲሱ የጀርመን መንግሥት ውል  | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 30.11.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የአዲሱ የጀርመን መንግሥት ውል 

አዲሱን የጀርመን መንግሥት ለመመስረት የተስማሙት ፓርቲዎች የጥምረት ውል ላይ፣ የአፍሪቃ ስም የሰፈረው አራት ጊዜ ብቻ ነው። ይህ አፍሪቃ 15 ጊዜ ከተጠቀሰችበት የተሰናባቹ መንግሥት የአንጌላ ሜርክል  የክርስቲያን ዴምክራት ኅብረት ፓርቲና የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ  የጥምረት ውል ጋር ሲነጻጸር እጅግ አነስተኛ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:30

የአዲሱ የጀርመን መንግሥት ውል 

በቅርቡ ይመሰረታል ተብሎ የሚጠበቀው አዲሱ የጀርመን መንግሥት የሚያራምዳቸውን ፖሊሲዎች ከአንድ ሳምንት በፊት ይፋ ባደረገው የጥምረት ውል አስታውቋል። ጀርመን በአፍሪቃ የምትከተለው ፖሊሲም በዚሁ ውል ተጠቅሷል። የዛሬው ዝግጅታችን ውሉ ባካተታቸው ዋና ዋና ጉዳዮችና በቀጣዩ መንግሥት የአፍሪቃ ፖሊሲ ላይ ያተኩራል።ለዝግጅቱ ኂሩት መለሰ
በቅርቡ ይመሰረታል ተብሎ የሚጠበቀው የአዲሱ የጀርመን መንግሥት የጥምረት ውል ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ይፋ ተደርጓል። በዚህ ውል የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ኤስ ፔ ዴ ፣እህትማማቾቹን የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረትና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲዎች ካሸነፈበት ከዛሬ ሁለት ወሩ ምርጫ በኋላ ለሳምንታት በተካሄደ ድርድር ተጣምረው መንግሥት ለመመስረት ከተስማሙት ከአረንጓዴዎቹና ከነጻ ዴሞክራቶች ፓርቲ ጋር፣  ጀርመን ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት የምትመራበትን ፍኖተ ካርታ አቅርቧል። ከከዚህ ቀደሞቹ የጥምር መንግሥት ምስረታዎች በተለየ የምስረታ ሂደቱ ፍጥነት ለብዙዎች እፎይታን ያስገኘው አዲሱ መንግሥት ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ ከሚጠበቅባቸው ጉዳዮች ዋነኛው ጀርመንን የሚያሰጋውን አራተኛውን ዙር የኮሮና ወረርሽኝ መግታት ነው። በመንግሥት ምስረታው ድርድር መሀል ተሰናባቿ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ተደራዳሪዎቹን ፓርቲዎች በዚህ ጉዳይ ላይ አወያይተዋቸው ነበር። የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ መሪ የአሁኑ የጀርመን የገንዘብ ሚኒስትር ኦላፍ ሾልዝ አዲሱን የጀርመን መንግሥት ይመራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሥልጣን ሲይዙም የኮሮና ወረርሽኝ ቀውስን የሚከላከል ቡድን እንደሚያቋቁሙና ለጤና ባለሞያዎች እንደ ጉርሻ የሚሰጥ አንድ ነጥብ አንድ ሁለት ቢሊዮን ዩሮ እንደሚፈቅዱ ቃል ገብተዋል። ከወረርሽኙ ሌላ በውሉ፣ በቀደመው መንግሥት በጎርጎሮሳዊው 2038 ከባቢ አየርን የሚበክለውን የድንጋይ ከሰል በጀርመን መጠቀም እንዲቆም የተቀመጠውን የጊዜ ገደብ በስምንት ዓመት እንዲያጥር ተደርጓል።የትኛው ፓርቲ የትኛውን ስልጣን ይወስዳል የሚለውም የሰነድ አንዱ ትኩረት ነው። በዚሁ መሠረት ባለሀብቶችን የሚያበረታታው የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ኤፍ.ዴ.ፔ  የገንዘብ ሚኒስቴር ሃላፊነት ተሰጥቶታል።የፓርቲው መሪ ክርስቲያን ሊንድነር የገንዘብ ሚኒስትር ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። የኤኮኖሚ የተፈጥሮ ጥበቃንና የኃይል ሚኒስቴሮችን በአንድ የሚያጠቃልለው የአዲስ ልዕለ ሚኒስቴርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት መሪነት ደግሞ ለአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ነው የተሰጠው።ከፓርቲው መሪዎች አንዱ ሮበርት ሀቤክ የአካባቢ ጥበቃ

ሚኒስትር፣ የፓርቲው መሪ አናሌና ቤረቦክ ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሆኑ በፓርቲያቸው ተመርጠዋል።ቤርቦክ ይህ ስልጣን ከተሰጣቸው የመጀመሪያዋ ሴት የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይሆናሉ። ሶስቱ ፓርቲዎች የሚመሰርቱት በኤስ ፔ ዴው ቀይ፣ በነጻ ዴሞክራቶቹ ቢጫ እና በአረንጓዴዎቹ አረንጓዴ መለያ ቀለማት የትራፊክ መብራት የሚል ስያሜ የተሰጠው የዚህ ጥምረት ውል ባለ  177 ገጽ ነው። ውሉ በየደረጃው ባሉ የየፓርቲዎቹ አካላት ከተመረመረ በኋላ ሾልዝ ታኅሳስ መጀመሪያ ላይ በይፋ በሀገሪቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመራኄ መንግሥትነት ይመረጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። 
፣አዲሱን የጀርመን መንግሥት ለመመስረት የተስማሙት ፓርቲዎች የጥምረት ውል ላይ ፣የአፍሪቃ ስም የሰፈረው አራት ጊዜ ብቻ ነው። ይህ አፍሪቃ 15 ጊዜ ከተጠቀሰችበት የተሰናባቹ መንግሥት የአንጌላ ሜርክል  የክርስቲያን ዴምክራት ኅብረት ፓርቲና የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ  የጥምረት ውል ጋር ሲነጻጸር እጅግ አነስተኛ ነው። የጀርመንና የአፍሪቃ ግንኙነቶች አዋቂ ሮበርት ካፔል ያለፈውን ከአሁን ጋር በማነጻጸር ለዶቼቬለ በሰጡት አስተያየት በአሁኑ ውል፣ የጀርመን የአፍሪቃ ፖሊሲ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።ከዚያ ይልቅ ትኩረቱ ከጀርመን ጋር ይበልጥ በሚዛመዱ ጉዳዮች ላይ ሆኖ ነው የተገኘው።
«ከ2017 ዓመተ ምህረቱ የትልቁ የጀርመን ጥምረት ውል ጋር ሲነጻጸር በአሁኑ ውል የአፍሪቃ ፖሊሲ በተለይ በሁለተኛ ደረጃ የሚነሳ ነው። ስለዚህ ይህ ትኩረት የተሰጠውም አይደለም። ትኩረት የሚሰጣቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ። የዲጂታል ቴክኖሎጂን ማስፋፋት፣የአውሮጳ ጉዳይ ከጀርመን ጋር የሚዛመቱ ጉዳዮች ናቸው ትኩረት የሚሰጣቸው።» 
ያ ማለት ግን ጀርመን እስከዛሬ በገንዘብ የምትደግፋቸው አፍሪቃ ውስጥ የሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ይቆማሉ ማለት አይደለም።ይህ አፍሪቃውያንን ሊያሳስባቸው አይገባም የሚሉት ደግሞ የነጀርመን ነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ የልማት ፖሊሲ ጉዳዮች ፖለቲከኛ ክሪስቶፍ ሆፍማን ናቸው።
«ከአዲሱ የጥምረቱ ውል አፍሪቃውያን በአፍሪቃ ትኩረት የተሰጠው የጀርመን የልማት ትብብር በተወሰነ ደረጃ ሊቀጥል እንደሚችል መጠበቅ ይችላሉ።በተመድ የልማት ግብ መሰረት ከጀርመን አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ገቢ ዜሮ ነጥብ ሰባት በመቶውን ለአፍሪቃ ለማዋል ቃል ከተገባው አፍሪቃ ተጠቃሚ መሆኗ ይቀጥላል።ዜሮ ነጥብ ሁለት በመቶውም በልማት ወደ ኋላ ለቀሩት ይሰጣል።» 

ሆኖም ሆፍማን እንዳስረዱት ጀርመን እነዚህን የተመ የልማት ግቦች ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ያደረገችው በጎርጎሮሳዊው 2020 ዓም ነው። የጥምረቱ ውል የአፍሪቃ ፖሊሲ ፣ፍልሰትና ፣ልማትን አካቷል። በውሉ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ የልማት እርዳታ ተጠቅሷል። ወደፊት መንግስት የሚሆነው ጥምረት ለአካባቢ ጥበቃ የሚሰጣቸው የገንዘብ ድጋፎች ልማትን በማሳደግ ድሀውን ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንዲያደርግ ይፈለጋል።ሆፍማን እንደሚሉት አነስተኛ አቅም ያላቸው ገበሪዎች ለምሳሌ በዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ  እርዳታዎች ደን በማልማት እየተሳተፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል።ይሁንና ችግሩ የጥምረቱ ስምምነቱ ለነዚህ ጉዳዮች የሚሰጠውን የእርዳታ መጠን በግልጽ አለማስቀመጡ ጥያቄ አስነስቷል። በሌላ በኩል አንዳንድ የጀርመን የልማት ድርጅቶች በስምምነቱ ላይ የአፍሪቃ ስም ባይጠቀሰም ክፍለ ዓለሙን ሊጠቅሙ የሚችሉ ፖሊሲዎችን አካቷል ይላሉ። ይህን ከሚሉት አንዱ የጀርመን የልማት ፖሊሲ ዋና ሃላፊ ሽቴፋን ኤክሶ ክሪሸር ናቸው።
«መጪው መንግሥት የጤናን ጉዳይን እጅግ በተቀናጀ አሰራር ይበልጥ የማጠናከር ሃሳብ አለው። ከዚህ ሌላ፣ ብዝሀ ህይወት የተፈጥሮ ጥበቃ እና ሌሎች በርካታ ዘርፎች ለጤና አገልግሎት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።ይህንንም በበጎ ጎኑ ነው የማየው። ከዚህ በተጨማሪም መሰረታዊ ትምሕርትን ማጠናከርም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።ምክንያቱም ጀርመን በንጽጽር ሲታይ ባለፈው ጊዜ ይህን ጉዳይ ዘንግታዋለች።»
የተሰናባቹን የጀርመን መንግሥት የአፍሪቃ ፖሊሲን ስንመለከት አፍሪቃን የዘነጋ ከተባለው የመጪው የጀርመን መንግስት የአፍሪቃ ፖሊሲ ጋር የተራራቀ ነው።በተሰናባቹ መንግሥት ከአፍሪቃ ኅብረት ጋር የተጠናከረ ትብብር ነበር። ለአፍሪቃ አህጉራዊ ነጻ የግንድ ቀጣና ጀርመን ድጋፍ ስትሰጥ ቆይታለች። ቀውስ ውስጥ ለሚገኘው የሳህል አካባቢ ተጨማሪ እርዳታዎችን ስታቀርብም ነበር።በጀርመን አሳሳቢነት በቡድን ሀያ ጉባኤ አነሳሽነት የተጀመረው የጀርመን ባለሀብቶች በአፍሪቃ በመወረት የስራ እድል እንዲፈጥሩ አልሞ የተጀመረው ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ ብዙም ባይራመድም ቢያንስ አፍሪቃንና ጀርመንን የጋራ ተጠቃሚ ለማድረግ በሞከረ መርሃ ግብርነት ስሙ ይነሳል። እነዚህ በቅርቡ የሚሰናበተው የጀርመን መንግሥት ከአፍሪቃ ጋር የነበረውን ግንኙነት ይገልጻሉ ተብለው የሚነሱ ምሳሌዎች ናቸው። ታዲያ አዲሱ መንግሥት በአፍሪቃ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ላይ ትኩረት አለማድረጉ ቅር አሰኝቷል። ይሁንና የተለመደው ዓይነት አሰራር አፍሪቃ ከአሁን ወዲያ የምትፈልገው አይደለም ይላሉ የጀርመንና የአፍሪቃ ግንኙነቶች አዋቂ ሮበርት ካፔል ።

«በአፍሪቃ ክፍለ ዓለም በኩል በልማት ትብብሩ ረገድ የመሰላቸት ነገር አለ።የአፍሪቃ ሀገራት በየበኩላቸው የራሳቸውን የተለያዩ እርምጃዎች ተግባራዊ ያደርጋሉ።በዚህ የተነሳም የልማት ትብብር ላይ ያን ያህል መተማመን ትተዋል።በዚህ ሰነድ ላይም ይህ ጉዳይ ትኩረት አልተሰጠውም።»
ሆኖም በሜርክል ሲመራ የነበረው ተሰናባቹ የጀርመን መንግሥት ባለሀብቶች በአፍሪቃ እንዲወርቱ ለማበረታትና በአፍሪቃ የመወረት ስጋታቸውንም ለመቀነስ የተለያዩ አሰራሮችን ዘርግቶ ነበር። በዚህ ረገድ በአፍሪቃ መዋዕለ ንዋያቸውን ለሚያፈሱ የጀርመን ባለሀብቶች የሚሰጠው ድጋፍ እና ኩባንያዎቻቸውን ከስጋት ነጻ ያደርጋል የተባለ የተሻሻለ መከላከያ ማቅረብ ይጠቀሳሉ። አዲሱ መንግሥት ግን በነዚህን መሰል ጉዳዮች ላይ የማተኮር እቅድ የለውም።ይህም የጀርመን አፍሪቃ የንግድ ማኅበር ተጠሪ ክሪስቶፍ ካነንጊሰርን የመሳሰሉትን ሰዎች እጅግ አበሳጭቷል።
«በአዲሱ የጀርመን የጥምረት ውል አፍሪቃ በግልጽ ተረስታለች።ይህ በጣም የሚያሳዝን ነው። ሆኖም  በኔ እምነት ተራማጅ የሆነ ጥምረት ከአፍሪቃ ጋር ያለውን ግንኙነት ማስፋትና ዘመናዊም ማድረግ አለበት። በአውሮጳ ትብብር ውስጥም ከአፍሪቃ ጋር ስልታዊ ወዳጅነት መፍጠር ይገባል።»  
የጥምረት ውሉ አፍሪቃን ወደ ጎን ማለቱን በአዲሱ የጀርመን ፓርላማ ጠንካራ ተቃዋሚ የሚሆነው የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ ተችቷል። የፓርቲው የልማት ጉዳዮች ፖለቲከኛ ፎልክማር ክላይን ውሉ በፖሊሲው የጤናና የትምህርት ጉዳዮች መካተታቸው ትክክለኛ  መሆኑን አድንቀው ሆኖም ልማቱን ዘላቂ ማድረጉ ስራ በመፍጠርና አዳዲስ ምልከታዎችን በማስፋት ሊታገዝ እንደሚገባ አሳስበዋል።ለዚህም ነው በነዚህ ሃገሮች ውስጥ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ጠቃሚ ነው የምንለው ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ከዚህ ሌላ የወደፊቱ የጀርመን መንግሥት ውል የሲቪክ ማኅበረሰብ አባላትና የአፍሪቃ ሃገራት ጥያቄዎችንም አካቷል።የቀድሞዋን የጀርመን ቅኝ ግዛት ናሚብያን በሚመለከት የጀርመን መንግሥት ለታሪካዊና ፖለቲካዊ ግዴታ እውቅና እንዲሰጥ ተስማምቷል። እርቀ ሰላም ለማውረድም ቃል ገብቷል። 
ፍልሰትን በሚመለከትም ከከዚህ ቀደሙ መንግሥት በተለየ መንገድ በርካታ ዜጎቻቸው የተሻለ ህይወት ፍለጋ ወደ ጀርመንና አውሮጳ ከሚሰደዱባቸው ሃገራት ጋር ስምምነቶችን ማድረግ ይፈልጋል።እነዚህ ስምምነቶችም የልማት ትብብሮችን ይበልጥ ለማሳደግ የሚረዱና ከነዚህ ሃገራት የሚፈለጉ ሰራተኞችም በሕጋዊ መንገድ ወደ ጀርመን እንዲገቡ ይረዳሉ ተብሏል። አዲሱ ጥምር መንግሥት በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ያሰበውን ማሳካት መቻል አለመቻሉ እንግዲህ ወደፊት የሚታይ ይሆናል።  

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic