የአዲሱ የቱኒዚያ ፕሬዚዳንት የቤት ሥራዎች | አፍሪቃ | DW | 19.10.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የአዲሱ የቱኒዚያ ፕሬዚዳንት የቤት ሥራዎች

ቱኒዚያዉያን አዲስ ፓርላማ ብቻ ሳይሆን ከአንድ ወር የምርጫ ፉክክር በኋላ ያለፈዉ እሁድ አዲስ ፕሬዝዳንትም መርጠዋል። ጡረተኛዉ የሕግ ጠበቃ ክአስ ሰይድ ሁለት ሦስተኛዉን ወይም 76 ነጥብ ዘጠኝ በማግኘት ነዉ የተመረጡት።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:46

ትኩረት በአፍሪቃ

ቱኒዚያዉያን አዲስ ፕሬዝዳንት መርጠዋል። እንደ ቱኒዚያ የምርጫ ኮሚሽን 90 በመቶ የፕሬዝዳንቱ መራጮች ምሁራን እና ከ18 እስከ 25 ዓመት ባለዉ የዕድሜ ክልል ያሉ ወጣቶች ናቸዉ። ዉጤቱ እንደተገለፀ አፍታም ሳይቆዩ በሺዎች የሚቆጠሩ የሀገሪቱ ዜጎችም አዲሱን ፕሬዝዳንት በመደገፍ በአደባባይ ወጥተዉ ደስታቸዉን ገልፀዋል።

ፕሬዝዳንቱ ከምርጫዉ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም  በሕገ-መንግሥቱ ማዕቀፍ ውስጥ አዲስ የለውጥ ፅንሰ-ሀሳብ ሲሉ ነበር ዉጤቱን የገለፁት። ፕሬዚዳንት ካአስ ሰኢድ «ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ያሻግሯታል» በሚል በብዙዎች ዘንድም ተስፋ ተጥሎባቸዋል። ያም ሆኖ በፖለቲካ ክፉኛ የተከፋፈለችዉና በርካታ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ችግር ያሉባት ቱኒዚያን መምራት በቀላሉ የሚታይ አይመስልም። ፕሬዝዳንቱ ከምርጫዉ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ «በሕገ-መንግሥቱ ማዕቀፍ ውስጥ አዲስ የለውጥ ፅንሰ-ሀሳብ» ሲሉ ነበር ዉጤቱን የገለፁት።

የሰሜን አፍሪቃዊቷ አገር ቱኒዚያ ፕሬዚዳንት ስትሾም በጎርጎሮሳዉያኑ 2011 ዓ/ም በሀገሪቱ ከተካሄደዉ አብዮት ወዲህ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነዉ። ቱኒዚያዉያን ከ2011 የፀደይ አብዮት ወዲህ ላለፉት 8 ዓመታት የነፃነት ጭላንጭል ማግኘታቸዉን ይገልፃሉ።

ቱኒዚያ ከተቀረዉ የዓረቡ ዓለም የተሻለ ነዉ የሚባል ሕገ-መንግሥት ያላት ሀገር በመሆኗ፤ የሀገሪቱ ሴቶች ከቀጠናዉ ሃገራት ጋር ሲነፃፀር እጅግ የተሻለ ነፃነት እንዳላቸዉ ይነገራል። በሀገሪቱ በመገናኛ ብዙሃን ዘንድም «የሰሜን አፍሪቃ ብርሃን» እየተባለች የምትጠራ ሲሆን ለአብዛኛዉ የሀገሬዉ ሰዉ አባባሉ ምቹ አይደለም። ቱኒዚያዉያን የታገሉለት አብዮት ለነፃነትና ለእኩልነት ቢሆንም ብዙ የተለወጠ ነገር የለም በሚል መንግሥታቸዉን አሁንም ይተቻሉ።

ሀገሪቱ ዘመናዊ ሕገ-መንግሥት አላት የሚለዉን አባባል ለነስሪን ጀላሊያ አይቀበሉትም። ነስሪን «አልባስዋ» የተባለዉ በፖለቲካዉ ዘርፍ ግልፅነትን ለማምጣት የሚሠራ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ዳይሬክተር ናቸዉ። እሳቸዉ እንደሚሉት ሕገ መንግሥቱ በሥራ ላይ እየዋለ አይደለም።

«እዉነት ነዉ አዲሱ የቱኒዚያ ሕገ-መንግሥት የሴቶችንና የወንዶች መብት እኩል እንዲከበር ይደነግጋል ነገር ግን እየተተገበረ አይደለም። እስካሁን የሕገ-መንግሥት ፍርድ ቤት የለንም። በዚህ ሳቢያ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉም ይሁን በፍትሃ ብሔር ሕጉ ላይ ከመጠነኛ ለዉጥ ዉጭ የጎላ መሻሻል የለም። ለምሳሌ ሴቶችን ከጥቃት የመታደግ ዓላማ ያለዉ ሕግ አለ። ነገር ግን ሕጉ ተግባራዊ የሚደረግበት በጀት እስካሁን ድረስ የለንም።»

የሀገሪቱ ሴቶች የዉርስ ሕግን በተመለከተም ነባሩ ሃይማኖታዊ የዉርስ ሕግ ስለሚጫነዉ አሁንም ተጠቃሚ አይደሉም ይላሉ ዳይሬክተሯ። ያም ሆኖ የተወሰነ ለዉጥ መኖሩን አልሸሸጉም። ለምሳሌ በፖለቲካዉ መስክ ሴቶች በምርጫ እኩል መሳተፍ ይችላሉ። በሀገሪቱ ፓርላማም 30 በመቶ ሴቶች መቀመጫ አላቸዉ። ችግሩ ግን አብዛኛዎቹ ከፍተኛ እጩዎች ወንዶች በመሆናቸዉ እስካሁን የሴቶች ቁጥር የሚፈለገዉን ያህል አይደለም።

በፖለቲካዉ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ጉዳዮችም ለሴቶች ለዉጥ ያስፈልጋል ይላሉ ነስሪን። «ሴቶች ቤተሰቦቻችንን እናጣለን በሚል ስጋትና የኢኮኖሚ ድጋፍ ማጣትን በመፍራት ፤ማጨስ ወይም መጠጣት ቢፈልጉና  የወንድ ጓደኛ ቢይዙ ተደብቀዉ ነዉ።» እንደ  ሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ ሊና ማዋጀዲን። የቱኒዚያ ማኅበረሰብ በዕለት ተዕለት ሕይወቱ ወግ አጥባቂ በመሆኑ በዋናነት ሴቶችንና  ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያንን የመሳሰሉ አነስተኛ ቁጥር ያላቸዉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እየጎዳ ቆይቷል።

ይህ በአብዮቱ ብዙም አልተለወጠም ትላለች የ25 ዓመቷ ሊና። «ሁሉንም ነገር በግልፅ እናወራለን። ድብቅ ነገር የለም። እናወራለን እናወራለን ነገር ግን ምንም ሥራ አልተሠራም።» ሊና ይህን ትበል እንጅ ወግ አጥባቂ እንደሆኑ የሚነገርላቸዉ ፕሬዚዳንት ሰኢድ፤ የሀገሪቱ ሕግ የሚደነግገዉን የሞት ቅጣት እንዲሁም የተመሳሳይ ፃታ አፍቃሪዎች ቅጣት እንዲቀጥል ይፈልጋሉ። ሀገሪቱን በፌዴራል ምክር ቤት የማስተዳደር ሀሳብ አላቸዉ።

በቱኒዚያ ለዉጥ ከመጣ ከስምንት ዓመታት በኋላም ብዙ የሀገሬዉ ሰዎች ተስፋዎቻቸዉ እዉን አለመሆኑን ይገልፃሉ። ከዚህ በተጨማሪ በሀገሪቱ ኢኮኖሚው እያሽቆለቆለ ነው፣ ብዙ የሥራ ዕድልም የለም ፣ የኑሮ ውድነትም ሌላዉ ፈተና ነዉ። በዕለት ተዕለት ሕይወትም  ብዙዎች ደህንነት አይሰማቸውም። ከሁሉም በላይ ብዙ ቱኒዚያውያን አዲሱ ፕሬዚዳንት በፖለቲካ የተከፋፈለችዉን ቱኒዚያ ወደ አንድነት እንዲያመጡ የሀገሪቱ ዜጎች ይጠብቃሉ። ይህ ሁሉ በፕሬዝዳንቱ ትከሻ የወደቀ ነዉ።

በሀገሪቱ በጎርጎሮሳዉያኑ ያለፈዉ ጥቅምት 6 ቀን 2019 ዓ/ም ከተደረገዉ የፓርላማ ምርጫ በኋላ መንግሥት ምስረታ አስቸጋሪ ሆኖ ነዉ የቆየዉ፡፡ ፓርላማዉም በቅራኔ በተሞሉ  ፓርቲዎች የተሞላ ነዉ። እናም ከአዲሱ ፕሬዝዳንት የመጀመሪያ ተግባራት መካከል  እነዚህን ፓርቲዎች ማስማማት አንዱ ይሆናል ነዉ የተባለዉ። እናም  የ61 ዓመቱ የህግ ጠበቃ ፕሬዝዳንት ካስ ሰኢድ ከፊታቸዉ የሚጠብቃቸዉ የቤት ሥራ ቀላል አይመስልም።

የከፋ ድህነት ገጠር በሚኖሩ ሴቶች 

በአየር ጠባይ ለዉጥ ሳቢያ በዕፅዋትና በዕንስሳት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች፤ እንዲሁም ግጭቶች በሚያመጧቸዉ ችግሮች ሴቶች የመጀመሪያዎቹ ተጎጅዎች ናቸዉ። በተፈጥሯዊና ሰዉ ሰራሽ ችግሮች ምክንያት በሚከሰት የምግብና ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች  የዋጋ ንረትና ረሀብም  እንዲሁ። ምክንያቱም የመላዉ ቤተሰብ ኃለፊነት በአብዛኛዉ በተለይም በአዳጊ ሃገራት በሴቶች ላይ የወደቀ በመሆኑ ነዉ። እናም ይህንን ጉዳት ለመቀነስ  የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብና የእርሻ ድርጅት ማለትም ፋኦ ዘገባ ያሳያል። እንደ ድርጅቱ ዘገባ በዓለም ላይ 850 ሚሊዮን ሰዎች በምግብ እጦት ይቸገራሉ። በአዳጊ ሃገራት ያሉ ሴቶችን ከወንዶች እኩል ዕድል ቢሰጣቸዉ ግን ይህንን አሃዝ  በ150 ሚሊዮን  መቀነስ ይቻል እንደነበር ያሳያል።

FAO, Food and Agriculture Organisation of the United Nations, Logo

በጀርመንኛ አጠራሩ «ቬልት ሁንጋ ሂልፈ» ከተባለዉ ድርጅት ፍሬዘር ፓተርሰን ።የምርት እድገትን ለመጨመር ሴቶች እኩል የሀብት ተጠቃሚ መሆን አለባቸዉ ይላሉ። «ሴቶች ከወንዶች እኩል የሀብት ተጠቃሚ ቢሆኑ፣ የትምህርት እድል ቢያገኙ ፣ የመሬት ባለቤቶች ቢሆኑ እንዲሁም የብድርና የገበያ ተደራሽነት ቢመቻችላቸዉ። የምርት እድገት ከ20 እስከ 30 በመቶ ሊጨምር ይችላል።»

በተለይም በገጠር የሚኖሩ ሴቶችን የመሬት ባለቤት በማድረግ፤ በትምህርት እንዲሁም በአነስተኛ የገንዘብ ተቋማት የብድር ተጠቃሚ በማድረግ ምርታማነትን መጨመር ይቻላል። ለዚህም ፒተርሰን ቤተሰቦቿንና 30 የሚሆኑ የመንደሯን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ያደረገችዉን የዩጋንዳዋን ቤቲ ኑዱጋን በማሳያነት ያቀርባሉ።

ቤቲ በዩጋንዳ ሉዌሮ ወረዳ ትኖር የነበረ ሲሆን፤ ባለቤቷ ከሞተ በኋላ ግን  ልጆቿን ይዛ ወላጆቿ ወደሚኖሩበት መንደር ነበር ያመራችዉ። «ይህ መሬት የሟቾቹ  ወላጆቼ ነበር። የቡና ችግኞችን እንዴት ማሳደግ እንዳለብኝ ካወቅሁ በኋላ ፤ይንን  የንግድ  ሥራ መሥራት ጀመርኩ።» ፋኦ በሰጣት ስልጠና ከወላጆቿ ባገኘችዉ አነስተኛ ማሳ ላይ በዩጋንዳ ትልቁ የዉጭ ምንዛሬ ማስገኛ  የሆነዉን የቡና ተክል ልማት ጀመረች። በዚህ የቡና ልማት ለ30 ሰዎች የሥራ ዕድል የከፈተች ሲሆን አብዛኛዎቹ ሴቶች ናቸዉ።

እንደ ፋኦ መረጃ በዓለም ላይ ከ2.5 ቢሊዮን በላይ ሰዎች በአነስተኛ የማሳ ምርት ላይ የተሰማሩ ሲሆን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ናቸዉ። ፓተርሰን እንደሚሉት አብዛኛዉ የምግብ ምርትም  የሚመረተዉ በሴቶች ነዉ። «በእስያና ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪቃ ሀገራት 50 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች  በእርሻ ስራ ላይ የተሰማሩ ናቸዉ። ምንም  እንኳ ከወንዶች ያነሰ የሀብት ባለቤት ቢሆኑም ፤በእነዚህ አካባቢዎች  ከ60 እስከ 80 በመቶ የሚሆነዉ ምግብ የሚመረተዉ  በሴቶች ነዉ።»

በአጠቃላይ በኢኮኖሚ ዝቅተኛ በሆኑ ሃገራት ሦስት አራተኛዉ የገጠር ሕዝብ በከፋ ድህነት የሚኖር ሲሆን በእነዚህ ቦታዎች የሴቶች የሀብት ባለቤትነት ዕድል አነስተኛ በመሆኑ በዚህ ችግር እጥፍ ተጎጅዎች መሆናቸዉን መረጃዎች ያሳያሉ።ለዚህም የአየር ንብረት ለዉጥ እንዲሁም ግጭት የሚወልደዉ የረሀብ አደጋ እና ስደት የሴቶችን ተጎጅነት የበለጠ ያደርገዋል።

ፀሐይ ጫኔ

ሽዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic